ታዴዎስ ታንቱ ለነሐሴ 11 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው
በሁለተኛው ተከሳሽ ፍለጋ ጉዳይ ፖሊስ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ አዘዘ
በአምስት ተደራራቢ የሽብር ክሶች ከተሰው በእስር ላይ የሚገኙት አዛዎንቱ ጋዜጠኛ ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጸረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። የክስ መቃወሚያቸውንም አቅርበዋል። ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ከሳሽ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስተያየት እንዲሰጥበት ለነሐሴ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱንም ጠበቃቸው አቶ አዲሱ ጌታነህ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው በሌለበት ዶሴው እንዲቀጥል ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል። በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፖሊስ በተከሳሹ የእደና ሁኔታ ላይ በቀጣዩ ቀጠሮ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲያቀርብ አዝዟል።
ከዚህ ቀደም ፖሊስ ጌጥዬ ያለውን በአድራሻው ፈልጎ እንዳጣው መግለጹ እና በተገኘበት ሁሉ አድኖ እንዲያቀርብ በድጋሜ መታዘዙ ይታወሳል።
ጋሽ ታዴዎስ ታንቱ በግፍ ከታሰሩ የፊታችን ነሐሴ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ሦስት ወር ይሆናቸዋል።
©ኢትዮ ሪፈረንስ