>

አንገቱ  ተቀልቶ እንዲገደል የተወሰነበት ኢትዮጵያዊ ወጣት  ተማጽኖ  ‼  (ነቢዩ ሲራክ )

የማለዳ ወግ…

አንገቱ  ተቀልቶ እንዲገደል የተወሰነበት ኢትዮጵያዊ ወጣት  ተማጽኖ  ‼

ነቢዩ ሲራክ 


*  ሞትን መቀበል ያልቻለው ታዳጊ ክልትም …

* ከሞት ፍርደኛው ታዳጊ ወጣት አለሙ ጋር አዎጋን ‼

* የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጉዳዩን ይከታተልለት 

 

በሞት ፍርደኞች መካከል….

 

ከዛሬ ሶስት አመት በፊት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ ተሰደደ ። ሲሰደድ የሰማውን ሳያይ ፣ ያሰበው ተሰናክሎበት ዛሬ ወህኒ የሞት ተራ ጠባቂ ሆኗል።  በግድያ የመጨረሻ ሞት ፍርድ አንገቱን ተቀልቶ እንዲገደል ውሳኔ ከተላለፈበት ታዳጊ አለሙ መኮንን ተሾመ ጋር ዛሬ ማለዳ ለሶስተኛ ጊዜ ለግማሽ ሰዓት ያህል በስልክ ተጨዋዎትን ።

ከሽሜሲ የሞት ፍርደኞች ማጎሪያ ወህኒ ውስጥ ተራ በተራ አንገታቸው በሰይፍ እየተቀላ ከሚገደሉት መካከል አንዱ ነው ኢትዮጵያዊው የ23 ዓመት ታዳጊ አለሙ መኮንን ጋር ዛሬ ማለዳ በስልክ ተገኝተን ብዙ አዎጋን ። የሰው ልጆች ነንና ሁላችንም ሟች ነን ። ያም ቢሆን የምንሞትበትን ቀን ፣ ሰአት እና ቦታ ግን አናውቀውም። በሳውዲ ጅዳ የነፍስ ማጥፋት ከባድ ወንጄል ፈጽመሃል የተባለው ታደጊ አለሙ መኮንን ነፍስ አጥፍተሃል ተብሎ ተወስኖበታልና በሰላ በሰይፍ አንገቱ ተቀልቶ እንደሚሞት ተነግሮታል። እናም ሞትን ባይፈራውም  ” ያለ በቂ ምስክር  አንገቴን በሰይፍ ልቀላ ? ” በማለት  የድረሱልኝ ድምጹን ያሰማል።

የአለሙ ክልትምና መጨረሻ 

ዛሬም ማለዳ ከታዳጊ አለሙ ጋር ለግማሽ ሰአት በነበረን የስልክ ቆይታ የፍርድ ሂደቱን አጫውቶኝ ሲቀጥል ስለእውነት ብለህ ነፍሴ እንዲተርፍ እርዳኝ የሚል አደራን የእንባ ሳግ እየተናነቀኝ አጫውቶኛል …አንገቱን እንዲቀላ የተወሰነበት ከታዳጊ አለሙ ጋር ዛሬ ማለዳ በነበረን ሰፊ ቆይታ ገና በ20 አመት እድሜው፣ የ7ኛ ክፍል ትምህርቱን ጣጥሎ በሶማሌ ቦሳሶ ጅቡቲ ቀይ ባህርን በጭንቅ ተሻግሮ ፣ በየመን በርሃ አድርጎ ሳውዲ ስላደረሰው የሀገር ቤቱ ድህነትና የተሻለ ኑሮ ፍለጋውን አለሙ ሲያስረዳ ልብ ይሰብራል  🙁

ህገ ወጡ ስደትና ስለጉዞው ፣ ሳውዲ ጅዳ በገባ በ5 ወሩ በመጠጥ ሽያጭ ጥርጣሬ በፖሊሶች ተይዞ  ስለተፈጸመበት ድብደባ ፣ በግድያው ላይ የነበሩት ምስክሮች በሀሰት አንመሰክርም ስለማለታቸው፣ የሟች አባት ልጄን ገድሏል ብሎ በመማሉ ብቻ ያለ በቂ ምስክር ስለተላለፈበት ፍርድ በዝርዝር አውግቶኛል ። ታዳጊ አለሙ ነፍስ አጥፍተው መረጃ ቀርቦባቸው ፣ ምስክር ተቆጥሮባቸውና የሰው ነፍስ በግፍ ማጥፋታቸውን አምነው አንገታቸውን ለመቀላት አዘጋጅተው የሞት ተራቸውን  ከሚጠብቁ  መካከል ሆኖ ሞቱን መቀበል አልቻለም።

ታዳጊው ኢትዮጵያዊ  አለሙ መኮንን ወገኖቹ ሁላችንም  ድምጹን እናሰማለት ዘንድ ይጣራል። አለሙ በወህኒው  የግድግዳ የስልክ መስመር ባቀበለኝ ተማጽኖ መንግስት ጉዳዩ እንዲያታይ ያደርግ ዘንድ ይሻል።  ሲቀጥልም እንዲህ ይላል  ” አየህ ነብዩ በሀሰት ነፍስ አንገቴ በሰይፍ እንዲቀላ ውሳኔ ተላልፏል … በየትኛውም ጊዜና ሰአት አንድ መንጋ ፖሊሶች በወህኒው መጥተው ሊወስዱኝና አንገቴን ቀልተው በግፍ  ሊገድሉኝ ይችላሉና ወገኖቸና መንግስት ይድረሱልኝ ”  … ብሏል

ተገፊው ወንድም ላይ ሸሪአው በአግባቡ ይፈጸም

የሳውዲ አረቢያን የሸሪአ ህግ ኖሬበት ብቻ ሳይሆን በክፋት ታስሬና ተዳኝቸበት ፍትሃዊነቱን አውቀዋለሁ። በሸሪአው ህግ የሰው ነፍስ ያጠፋ፣ የገደለ ጉዳዩ በፍትሃዊነት ተመርምሮ ጥፋተኛ ይገደል ይላልና ይህን መቃዎም አይቻለኝም። ነገር  ግን ሸሪአው ከሚፈቅደው ውጭ መረጃና ምስክር ሳይቀርብ በታዳጊ አለሙ መኮንን ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ አግባብ አይደለም። ነፍስ ያላጠፋው ታዳጊ ወጣት አለሙ የነፍስ ማጥፋት ወንጄለ መፈጸማቸውን አምነው አንገታቸው በሰይፍ የሚቀላ ከ60 በላይ የሚሞቱበትን ቀን ከሚጠብቁት መካከል ታዳጊው በወህኒ የግድግዳ ስልክ  በግፍ ልገደል ነው ድምጼን አሰማ ብሎ ያቀረበልኝ ተማጽኖ ልብ ያደማል ፣ ልብ ይሰብራል 🙁  ዛሬም ተማጽኖው ይድረሳችሁ ። የዜጎች ጉዳይ የሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጉዳዩን በድጋሜ እንዲታይ ያደርግ  ዘንድ አደራ እላለሁ  ‼

ልደታ በእለተ ቀኗ ትማለድልህ ፣ ፈጣሪ ይድረስልህ ‼

ነሃሴ 1 ቀን 2014 ዓም

Filed in: Amharic