>

የደርግ እና ብልጽግና ተመሳሳይ ፖሊሲና እርምጃ -የኢትዮጲያን የማፈራረስ ጅማሮ... !!! (ወንድወሰን ተክሉ)

ታሪክ እራሱን ሲደግም-!!!

የደርግ እና ብልጽግና ተመሳሳይ ፖሊሲና እርምጃ -የኢትዮጲያን የማፈራረስ ጅማሮ… !!!

* ወንድወሰን ተክሉ*

፠ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለወያኔ ለቆ የመውጣት እየፈጠረ ያለው ሀገራዊ ኪሳራ

የሁለቱን ኮሎኔሎችን ፍጹማዊ ተመሳሳይነትን -ማለትም በዋና አዛዥነት የሚመሩትን መከላከያ ሰራዊት አመራራቸውና በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ የተደቀነውን ሀገራዊ የህልውናን አደጋ ከመቀልበስ እርምጃቸው አንጻር ሲታዩ ሁለቱ – መንግስቱና አቢይ በአንድ ቅርጫት ውስጥ የሚገኙ ሆኖ ማየት ለብዙዎቻችን የማይዋጥ መመሳሰል ቢመስልም ሀቁ ግን አንድነታቸውን ያሳያል። በተለይም የሁለቱን ኮሎኔሎችን ፍጹማዊ አንድነትን የማይታያቸው ሰዎች መንግስቱ ሀገር ወዳድ ለሀገር ሉዓላዊ ግዛት ቀናኢ የሆነ እና ዘረኝነትን ተጠይፎ ሁሉንም በእኩል ረግጦና ቀጥቅጦ የገዛ አቢይን ደግሞ ለአንድ ተወለጄበታለሁ ለሚለው ጎሳ የበላይነት በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ዋጋ የሚሰራ ጸረ ኦርቶዶክስ ጸረ አማራ የሆነ ለሀገር ህልውና ደንታ ቢስ ነው በማለት ልዩነቱን ይገልጻሉ።

ሆኖም በአራት ስርወ መንግስታት ስር ከአራትሺህ ዓመታት በላይ ስትገዛ የኖረቺውና ግዛታዊ ሉዓላዊነታ እስከ 1983ድረስ ተከብሮላት የምናውቃትን ኢትዮጱያ የባሕር መውጫ በር የሆነውን ግዛቷን አጥታ ዛሬ ደግሞ አጠቃላይ ሀገራዊ ህልውናዋ በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀባት ሀገር የሆነቺው በዋነኝነት በመንግስቱ ኋይለማሪያም አመራርና ዛሬ ደግሞ በአቢይ አህመድ አመራር ስር የመሆኑን ሀቅ ዛሬ ለይ ሆኜ ለታሪክ ይቀመጥ ዘንድ የምጽፈው እውነታ ነው።

ዛሬ ኦገስት 7 ቀን 2022 ላይ ሆነን ወደ ሰሜናዊው የኢትዮጲያ ግዛት ስንመለከት -ኢትዮጲያን ሀገረ ኢትዮጱያ በማሰኘት ለሺህ ዘመናት ያህል የሀገረ መንግስት ግንባታን በመገንባትና ብሎም የዚህችን ሀገረ ጥንታዊ ታሪክ በመያዝ ወሳኙን የአንበሳ ድርሻ የያዘው የኢትዮጱያ ክፍል ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጱያ ተነጥሎ ያለበት ሁኔታ ላይ ያለን ሲሆን ይህ ማለት ከሰላሳ ዓመት በፊት የተገነጠለቺዋ ኤርትራና ከሁለት ዓመት በፊት ከመላው የኢትዮጱያ ግዛት በየብስ እና በአየር እንዳትገናኝ ተደርጋ እንደ የከብቶች በረት ተዘግታ ያለቺዋን የትግራይን ሁኔታ ማለቴ ነው።

ኮ/ል መንግስቱ ኋይለማሪያም በ1981 የካቲት ወር  ሽሬ ላይ ያለውን 604ኛ ኮር ግዙፍ ሰራዊት አስመትተው ትግራይን ሙሉ በሙሉ ጫካ ላይ ላለቺው ወያኔ ጥለው የወጡበት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ ዛሬ በተመሳሳይ ሁኔታ አቢይ እየተገበረው ያለ ሆኖ ስናገኘው በአጭሩና በቀላሉ  ታሪክ እራሱን ሲደግም ብለን ነው ታዝበን የምንተወው ወይንስ ይህ ግጥምጥሞሽና ተመሳሳይነታዊ አንድነት እንዴት ተፈጠረ እንዴትስ መስበርና ማስቆም አለብን ብለን ነው እራሳችንን መጠየቅ የምንችለው ??? ምላሹን ለእያንዳንዳችሁ በመተው በእኔ በኩል የታየኝን እውነታ ላጋራችሁ።

በ1980 ላይ የደርጉ ኢፌድሪ መንግስት ወንበዴውን የወያኔን ቡድን ከትግራይ ጠራርጎ ለማጥፋትና ወያኔን ከትግራይ ለማጽዳት 3ኛው አብዮታዊ ሰራዊት የተባለን አዲስ ክፍለ ጦር በማቌቌም ብ/ጄ ሙላቱ ነጋሽን በዋና አዛዥነት አስር አለቃ ለገሰ አስፋውን በትግራይ ራስ ገዝ ዋና አስተዳዳሪነት መድቦ ወታደራዊ ዘመቻን በየካቲት 1981 ላይ ዘመቻ አድዋ ዘመቻ አክሱምና ዘመቻ ሽሬ ብሎ የጀመረበት ዓመት ነበር። በወቅቱ የወያኔ ጦር ከ30-40ሺህ ያህል እንደነበረ የታወቀ ሲሆን ይህንን የወንበዴን ሰራዊት ከትግራይ ግዛት ጠራርጎ ለማጽዳት 3ኛው አብዮታዊ ሰራዊት በሰው ኋይል በመሳሪያ አቅርቦት በሎጀስቲክስ በፖለቲካና በሞራል በሚገባ ተገንብቶ የተዘጋጀ ሲሆን ወታደራዊው ዘመቻ በአድዋና በአክሱም እንደተጀመረ በድል መወጣት ችሎ ነበር።

ሆኖም ብዙም ሳይቆይ…,,,,, (ዝርዝር ውስጥ መግባት እጅግ ሰፊ ስለሚሆን አንባቢ ለመረጃ ያህል በኮ/ል ፍስሀ ደስት የደርግ ምክትልና የኢፌድሪ ምክትል ፕሬዚዳንት የተጻፈን አብዮቱና ትዝታዬን፣ በፋሲካ ሲደልል የተጻፈውን የሻምላ ትውልድ  በፍቅረስላሴ ወግደረስ የተጻፈውን እኛ እና አብዮቱ ትውልድን ያናወጠ ጦርነት በሻለቃ ንጋቱ የተጻፉትን እውነተኛ የታሪክ ምስክርነታዊ መጽሐፍቶችን እንዲያነብ በመጠቆም ላልፈው እወዳለሁ) ……. የሰራዊቱን ድል ሰብሮ የነጠቀ የአጸፋ መልሶ ማጥቃት እርምጃ  በወያኔ በኩል ስለተወሰደ ጦሩ በከባድ መስዋእትነት ያስለቀቃቸውን መሬቶች መልሶ እየለቀቀ ለመሸሽ ተገደደና መጨረሻ ላይ ሽሬ ላይ የሰፈረው ግዙፉ 604ኛ ኮር ሰራዊት ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ቻለ።

የሽንፈንቱ ዋና መንስኤና ቁልፍ ተጫዋች የወያኔ ብርቱ ተዋጊነት ሳይሆን በሁሉም መመዘኛ ከወያኔ ሰራዊትና አቅም በአምስት እጥፍ የሚበልጠውን የኢትዮጲያን መከላከያ ሰራዊት በሚያዙት ጄኔራሎች የትግራይን ራስ ገዝ በሚያስተዳድረው አስር አለቃ ለገሰ አስፋው እና እንዲሁም የእያንዳንዱን ወታደራዊ ዘመቻን እቅድና ፕላን በማውጣትና የተዘጋጀን እቅድ አጥንቶ ውሳኔ የመጨረሻውን የይሁንታን ውሳኔን በሚሰጡት ኮ/ል መንግስቱ  ጥፋት በሰራዊቱ ላይ የደረሰ ታላቅ ውድቀታዊ ሽንፈት ነበር።

ሽሬ እንደስላሴ ላይ ያለውን 604ኛ ኮር እንዳስመቱ ጄ/ል ሙላቱ ነጋሽና አስር አለቃ ለገሰ አስፋው ከመቀሌ ሻንጣቸውን ሸክፈው ለመውጣትና ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለወያኔ ጥለው ለመሸሽ እንዲፈቀድላቸው ለኮ/ል መንግስቱ ጠይቀው  ይሁንታን እንዳገኙ ልክ ባለፈው ዓመት አቢይ በትግራይ ያለውን ሰራዊት እያዝረከረከና በአስርሺህ ለሚቆጠሩት ሳይነግር ፈርጥጦ እንዳወጣ እነለገሰ በሂሊኮፕተር በመውጣት ሰራዊቱ የኢሰፓ ፓርቲ አመራሮች አባሎች ካድሬውና ደህንንቱን ክፍል መውጣታቸውን እንኴን ሳይናገሩ ጥለው በመውጣት ለወንበዴው የእሳት እራት አደረጉት።

ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለቀው በመውጣት ወልዲያ ላይ ከከተሙ ከትግራይ የወጡበትን እና ግዙፉ ሰራዊት ሽሬ ላይ የተደመሰሰበትን እነለገሰ ለፕሬዚዳንቱ መላው የትግራይ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቶ በመዝመት ጨፍጭፎ ነው የደመሰሰን በማለት ተናገሩ። ይህም አቢይ አህመድ ሰራዊቱን ከትግራይ ሲያስወጣ ቃል በቃል የተናገረው ሲሆን በአጋጣሚ የተጋጣጠመ ሆኖ ሳይሆን ሆን ተብሎ ለኢትዮጱያ ሕዝብ እየተነገረ ያለ  መልእክት መሆነን  ያሳያል።

ኮ/ል መንግስቱ ኋይለማሪያምም  ትግራይ የጠመኔ በጀት እንኴን የሌላት እስቲ ወንበዴው የትግራይን ሕዝብ ምን እንደሚቀልብ እናያለን በማለት በኤርትራ ያለውን ሁለተኛውን አብዮታዊ ሰራዊት በኤርትራ በኩል አንዳችም ነገር ወደ ትግራይ እንዳይገባ  ካሰማሩ በሃላ በጎንደርና በወሎ በኩል ከትግራይ የሸሸውን ሰራዊት በማስፈር  ትግራይን ልክ ዛሬ አቢይ በምድር የብስና በሰማይ ዘጋግቶ ሁሉንም ነገር አግዶ እንዳለው ደርግም ትግራይንና ወያኔን ለብቻ በመተው የምታመጡትን አያለው። የትግራይ ሕዝብ እራሱ ሲመረው ወንበዴውን እያነቀ ይሰጠናል በማለት ትግራይን ለወያኔ ሰጡ። ይህ የሆነው በመጋቢት 1981 ዓ ም ሲሆን በግንቦት 8 ቀን 1981 ኮ/ል መንግስቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ  በመጪው 1982 ዓ ም ወያኔ በዘመቻ ዋለልኝ ወሎ ላይ በዘመቻ ቴውድሮስ ደግሞ ጎንደር ላይ በመክፈት በሁለተኛ ዓመቱ ግንቦት 20 ቀን 1983 ላይ አዲስ እበባን ልትቆጣጠር ቻለች።

፠ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለትህነግ/ወያኔ አሳልፎ በመስጠት ትግራይን ወደ እስርቤትነት የመለወጡ በሁለቱ ኮሎኔሎች የተወሰነው ውሳኔና መዘዙ፦ ኮ/ል አቢይ አህመድ መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ሙሉ በሙሉ ሲያወጣ ልክ እንደ አቻው ኮ/ል መንግስቱ ኋይለማሪያም መላው የትግራይ ሕዝብ በመከላከያው ላይ ስለተነሳና መከላከያው በንጹሃን ላይ ለመተኮስ ስላልቻለ ትግራይን ከስህበት ማእከልነታ አውርደን ከበሻሻም ያነሰች አድርገናት ነው በማለት ገልጿል። ኮ/ል መንግስቱ የጠመኔ እንኴን በጀት የላቸውም እንዳለውና እስቲ ወያኔ ሕዝቡን ምን እንደሚመግብ እናያለን እንዳሉት አቢይም ትግራይን ከተቀረው ዓለም ጋር የማትገናኝ በማድረግ የስልክ የመብራት የውሃ የባንክ …. ወዘተ አገልግሎቶችን በማቃረጥ  የትግራይ ሕዝብ  ሲቸግረው በወያኔ ላይ ያምጻል ብሎ ገለጸ።

እሺ ውጤቱ ምንድነው??? ትግራይ ወያኔን እያነቀች ለደርግና ለአቢይ ሰጠች??? ትግራይ በተጣለባት ማእቀብና እገዳ ተሽመድምዳ እና ተንኮታኩታ በአማጺ ልጆቻ ላይ አመጸች?? ለማእከላዊ መንግስት እጅ ሰጠች?? ውጤቱ ምንድነው የሆነው???

በደርጉ  ኮ/ል መንግስቱ ኋይለማሪያም ዘመን በ1981 ላይ ወንበዴ ለተባለው ወያኔ ሙሉ በሙሉ የተተወቺው ትግራይ ወንበዴውን ለቤተመንግስት ያበቃ ጉልበት ኋይልና አቅም በመስጠት የደርግን መንግስት ውድቀት እንዳፋጠነቺው ሁሉ ዘንድሮ ደግሞ በሰኔ 2021 ለትህነግ ብቻ ተለቃ የተተወቺው ትግራይ ለንፋስ የተሰጠ ዱቄት ሆኗል የተባለውን ትህነግ ዳግም እንዲያንሰራራና ተጠናክሮ እስከ ደብረሲና ድረስ ያደረሰን መጠነ ሰፊ ውድመትን ያደረሰን ሃይል እውን ስታደርግ ነው የታየው እንጂ  ሁለቱ ኮሎኔሎች  ወያኔን በትግራይ አጥረን እናከስሙዋለን በሚል መሀይማዊ ስሌት ወያኔና ትግራይ ከሁሉም ነገር ተገልለውና ተነጥለው ሲክስሙ ፈጽሞ አልታየም። ግን ታሪክ እራሱን ይደግማል እንደሚባለው ኮ/ል አቢይ የኮ/ል መንግስቱን ዱካ እየተከተለ አቻነቱን እያሳየ ያለበትን ሁኔታ ልብ ይሏል።

፠ መደምደሚያ-

ትግራይን ነጥሎ ለወንበዴ ለተባለውና ዘንድሮ ደግሞ አማጺ ለተባለው ቡድን አስረክቦ ክፍለ ሀገሪቱን በሁሉም አኣጣጫ ከቦ የቁም እስር ማድረግ በ1980ዎቹ ላይ ወንበዴዎቹን ወደ ቤተመንግስት ያደረሰን የአጸፋ ተግባር የመፍጠሩን ያህል ዘንድሮ በአቢይ ዘመን የትግራይ ተነጥሎና ተገልሎ ለቁም እስር መዳረግ  እንደዚህ ጸሐፊ እምነት እንሰ 1980ዎቸ በተመሳሳይ ሁኔታ ወያኔ ለአራት ኪሎ የሚያበቃ ውጤት ይታያል ብሎ የማያምን ቢሆንም በአንጻሩም  የአቢይ መራሹ ቡድን የትግራይ ፖሊሲ ከሀገረ ኢትዮጲያ እራሷን የምትገነጥል ትግራይን እየፈጠረ ያለ ፖሊሲ ነው ብሎ የሚያምነው።

በዚህ በሳለፍነው ጦርነትና ለሰላሳ ዓመታት ባየነው የትህነግ አገዛዝ ምክንያት የትግራይን መገንጠል ለምን የሚል ኢትዮጲያዊ በዝቶ የማናይበት ደረጃ ላይ እንዳለን በሚገባ እረዳለሁ። ይህ ስሜት በተለይም በሀገረ ኢትዮጱያ ግዛታዊ አንድነት ተጠብቆ መቀጠል ላይ እማያወላውል አቌምና ስሜት ያለውን እና በኤርትራ መገንጠል ዛሬ ድረስ በውስጥ የሚያዝነውን የሕብረተሰብ ክፍል የትግራይን መገንጠል እንደ የኢትዮጱያ ችግር ተቆርጦ መሄድ አድርጎ በማየት ከፈለጉ ይሂዱ የሚሉ አመለካከቶች ሃይለኛ በሆኑበት በአሁኑ ዘመን በቃ ሂዱልኝ እያላቸው ካለው የአቢይ ፖሊሲ አኴያ ትግራይን አይናችን እያየ ሆን ብለንም ይሁን ባለማወቅ ከኢትዮጲያ የማስወጣቱን ስራ እንደመንግስት ሲሰራ በዝምታ እያየን ነው የሚል እይታዊ ግምገማ ነው ያለኝ።

የኤርትራን ከኢትዮጲያ መገንጠል ለሰላም ነው የተባለውን ያህል ያ ኤርትራን እንድትገነጠል ያደረጋትን ሰላም ግን ሁለታችንም እንዳላገኘን ሁሉ ዛሬም የትግራይ መገንጠል ወያኔን እንድንገላገልና በሰላም እንድንኖር ያስችለናል ብለው ለሚያስቡ የዋሆች የማስተላልፈው መልስ በትግራይ ተገንጥሎ መሄድ የተቀረው የኢትዮጱያ ክፍል ( ከትግራይ በኋላ በእርግጥ ኢትዮጲያ የሚባለው ስም በታላቌ ኦሮሚያ ስም የሚተካ መሆኑን በእርግጠኝነት ዛሬ ላይ ሆኜ የምናገረው ነው)  በሰላም የሚኖር ሳይሆን በቀጣይ በኦሮሚያ ሁሉን የመሰልቀጥ ዘመቻና በአልሰለቀጥም የአጸፋ እርምጃ የእርሰበርስ ጦርነት የሚነግሳባት ሀገር የመሆን እድሉ እጅግ ሰፊ መሆኑን ነው ልገልጽ የምፈልገው።

ምክንያቱም ፈጣሪ አንድ አድርጎ የፈጠረንን – ከ4500 ዓመታት በላይ በአራት ስርወ መንግስታት ስር የኖረን ሕዝብ ትናንት ኤርትራን ዛሬ ትግራይን ከኢትዮጲያነት ነጥሎና አለያይቶ  ማኖር ስለማይቻል ነው። በተለይ በተለይ የትግራይ መገንጠል  የኢትዮጱያን ግብዓተ መሬት የሚያውጅና ለአማራው ደግሞ ከተቀሩት ነገዶች የከፋ አደጋን የሚወልድ እንጂ ዛሬ ብዙዎች እንደሚገምቱት የትግራይ መነጠል ለተቀረው ኢትዮጲያ ህልውና ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር የሚችልን ሰላም ማምጣት የሚቻለው ነው የሚባል አይደለም።

Filed in: Amharic