>

በጉራጌ ዞን የተለያዩ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ ተደረገ...,! (አ.ሚ.ማ)

በጉራጌ ዞን የተለያዩ ከተሞች የስራ ማቆም አድማ ተደረገ…,!

አ.ሚ.ማ

 


ነሃሴ 3/2014 ከክልል እንሁን ጥያቄ ጋር በተያያዘ በዞኑ መቀመጫ በወልቂጤ ከተማ የስራ ማቆም አድማ መመታቱ ተሰምቷል።

ከወልቂጤ ከተማ በተጨማሪም “ጉብሬ ጉንችሬ” እንዲሁም  “እምድብር” ከተሞች ላይም የስራ ማቆም አድማ መመታቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ ከተማዎች ባንኮች ፣ የተለያዩ መ/ቤቶች፣ የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንደቆመ የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረዉናል።

የእዣ ወረዳና የአገና ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞችም የህዝቡ ጥያቄ ይመለስ በሚል ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ መሆናቸውን በስልክ ሀሳባቸውን የሰጡን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄው ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑንና ለጠየቀው ህጋዊ የሆነ ጥያቄ ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጠው፣የ”ጉራጌ ክልል” አደረጃጀትም ተግባራዊ እንዲሆንለት በተለያየ መንገድ እየጠየቀ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ነግረዉናል፡፡

የአካባቢ ነዋሪዎች መንግስት በሰላማዊ እና ህጋዊ መንገድ እየተጠየቀ ላለው የክልልነት ጥያቄ ህጋዊ መልስ እንዲሠጥ ነው የስራ ማቆም አድማ ዋነኛ አላማዉ ሲሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰአትም በወልቂጤ ከተማ የመከላከያ፣ የፌደራል እንዲሁም የክልሉ ልዩ ሀይሎች በብዛት መግባታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ጠቁመዋል፡፡

ከስራ ማቆም አድማው በተጨማሪ በጉንችሬ እና በጉብሬ ሰላማዊ ሰልፎች እየተደረጉ ይገኛሉም ተብሏል።

እስካሁን የተፈጠረ የጸጥታ ችግር አለመኖሩን የተናገሩት ነዋሪዎቹ የመንግም ሆነ የግል ሰራተኞች ስራ አለመግባታቸውን ነዉ የሚናገሩት፡፡

በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለሁለት ተከፍለው በሁለት አዲስ ክልሎች ለመደራጀት በየምክር ቤቶቻቸው ወስነው ውሳኔውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸዉን ከዚህ ቀደም ማስታወቃቸዉ ይታወሳል፡፡

በጋራ በአዲስ ክልል እንደራጃለን ብለው በምክር ቤት ውሳኔ አሳልፈው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄውን ካቀረቡት መካከል ግን የጉራጌ ዞን እንደሌለበት መጠቀሱ ይታወቃል።

ከሰሞኑ ዞኑ ከአጎራባቾቹ ስልጤ ፣ ከምባታ ጠምባሮ ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ጋር ነበር በአንድ ክልል ይደራጃል ብሎ መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ የነበረው።

ነገር ግን የዞኑ ም/ቤት እስከ ዛሬ ድረስ በጉዳዩ ላይ አልተወያየም፤ አዲሱን አደረጃጀት አላፀደቀም ፤ ከዚህ በፊት ዞኑ እንደገለፀው የክልልነት ጥያቄን ለፌዴሬሽን ም/ቤት አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ነው።

መንግስት በአሁኑ ሰዓት ዞኑን በክልል ለማደራጀት እንደሚቸገር በመግለፅ ከአጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳ ጋር ክልል እንዲሆን ሀሳብ እያቅረበ መሆኑም ተሰምቷል ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም ነው የዘገበው።

Filed in: Amharic