>

ባልደራስ በመግለጫው ስለ ወደፊት የትግል መስመር  አቅጣጫ አስቀመጠ....!

ባልደራስ በመግለጫው ስለ ወደፊት የትግል መስመር  አቅጣጫ አስቀመጠ….!

ሰለሞን አላምኔ


*.. ባልደራስ ከዚህ በኋላ በ“ፖለቲካል አክቲቪዝም” ላይ ማተኮር እንዴለለበት ተመላክቷል።

*…. ለጉራጌውም በክልል እንዲደራጅና ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሊከበርለት ይገባል…!!!

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከዚህ በኋላ በሚከተለው የትግል አቅጣጫ፤ የፖለቲካ አንቂነት (አክቲቪዝም) ላይ እንደማያተኩር እና ፓርቲው ቀጣይ ትኩረቱ “የፓርቲ ፖለቲካ እና አደረጃጀት ስራ” እንደሚሆን አስታውቋል።

የፓርቲው የወደፊት አቅጣጫ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈቱ የሚችሉበትን የፖሊሲ አማራጮች በማመንጨት፤ ወደ ህዝብ ሰርጸው የሚገቡበትን መደላደል በማመቻቸት ላይ የሚያተኩር ይሆናል” ።

በአሁኑ ጊዜ የኦህዴድ-ብልጽግና መንግስትን አፋዊ አቀራራብ ሳይሆን ተግባራዊ ክንውን፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ በሚገባ እየተገነዘበ እንደመጣ ይታመናል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ህዝብ የፖለቲካ መብቱን እና የኢኮኖሚ ጥቅሙ እየተጎዳ ስለመሆኑ የፖለቲካ አንቂ የሚፈልግ አይደለም። የኑሮ መክብድ እና የፖለቲካው መዝቀጥ በተጨባጭ አንቅቶታል። ባልደራስ ከዚህ በኋላ በ“ፖለቲካል አክቲቪዝም” ላይ ማተኮር እንዴለለበት ተመላክቷል።

ስለ አዲስ አበባ ወሰን መገፋት በተመለከተ ባልደራስ በመግለጫው የፓርቲያችንን መሪ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ ወጣት የባልደራስ አባላት የአላማ ፅናት ያላቸው አዲስ አበቤዎች ❝ አዲስ አበባን ከኦህዴድ ስልቀጣ ለማስጣል እንዲሁም የከተማው ህዝብ እንዲነቃ እና ለመብቱ እንዲቆም ❞ ላለፉት አመታት ያለመታከት በእንግልት በእስርና በድብደባ በታጀበ ትግል ከመታገል ጀምሮ የፖለቲካ አክትቪዝምን መሰረት ባደረገ የትግል ስልት እስከ አሁን ድረስ መስዋትነት ተከፍሏል እየተከፈለም ይገኛል።

በመሆኑም የከተማው ህዝብ በሙያ እና በሲቪክ ማህበሩ በመሰባሰብ ማህበራቱን ከፖለቲካ ሸፍጥ ራሱን ነፃ በማወጣት ጥቅሜን ይወክላሉ ለሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ድጋፉን በመስጠትና ተሳትፎውን በማጠናከር ሰላማዊ ትግል መንገድ የሆነውን «ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን» ሊያሰማ ይገባል ሲል ባልደራስ ጥሪ አቅርቧል።–

ባልደራስ የጉራጌ ህዝብ ጥያቄን በተመለከተ ያለውን አቋም አሳወቀ

መላኩ ቢረዳ

❝ የጉራጌ ማህበረሰብ በኢትዮጲያ አንድነት ላይ ባለው አቋም ቀድሞውንም በህወሃት ዘመን አሁንም ተረኛ በሆነው ፅንፈኛው የኦህዴድ-ብልፅግና አገዛዝ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጫና እየደረሰበት ይገኛል። ❞

ይሁንና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ኢትዮጲያ የሚኖራት አወቃቀር እንደ እንስሳት በበረት በየወገኑና በየዘሩ መካለል ሳይሆን እንደ ሰው በሀገርና በክፍለ-ሀገር መዋቀር እንዳለበት በፅኑ የሚያምንና የሚታገል ድርጅት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ በኢትዮጲያ ውስጥ  በዘርና በነገድ መሠረት ያደረገ አከላለል እስካለ ድረስ ለሲዳማ ህዝብ እንደተደረገው ሁሉ ለጉራጌውም በክልል እንዲደራጅና ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲል አቋሙን ይፋ አድርጓል።

ይህም ራሱ ኦህዴድ ብልፅግና የሚምልለትና የሚገዘትለት ህገ መንግስት የሚፈቅድ በመሆኑ ሀገር ወዳድ ለሆነው ለጉራጌ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ ለጠየቀው ጥያቄ ገዥው መንግስት እንዲያከብርለት እያሳሰበ ይህ መብትም ለወላይታ ማህበረሰብም ሊከበር ይገባል ሲል ባልደራስ በመግለጫው ይፍ አድርጓል።

Filed in: Amharic