>

አድርባይነት...!!! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

አድርባይነት…!!!

ዶ/ር ታደሰ ብሩ

 ቆየት ያለች ጽሁፍ ብትሆንም ዛሬያችንን ቁልጭ አድርጋ ታሳያለች…!

1. ትርጓሜ

አድርባይነት ለገዛ ራስ ጥቅም እንጂ ለህሊና ዳኝነት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት ላላቸው የሥነ ምግባር መርሆዎች፣ ለሌሎች ሰዎች፣ ቡድኖች፣ ትውልድና ሀገር ግድየለሽ መሆን ነው። የግል ዝናውን፣ የግል ሀብቱን ወይም የግል ምቾቱን ለመጨመር ሲል ማድረግ የነበረበትን ማድረግ እየተቻለ ሳያደርግ የቀረ፤ ወይም ማድረግ ያልነበረበትን ያደረገ ሰው፣ ቡድን ወይም ድርጅት አድርባይ ይሰኛል።

አድርባይ የሆነ ሰው ወይ ድርጅት የሥነ ምግባር ልጓም የለውም፤ የሚናገረውን ሆኖ አይገኝም፤ ዋዣቂና ወላዋይ ነው፤ ለምንም ነገር መታመን አይችልም፤ ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ ማዶ ነው፤ ከፍ ያለ ዋጋ ላቀረበ ሁሉ ሊገዛ የሚችል ሸቀጥ ነው። አድርባይ ሰው ወይም ድርጅት ነገሮችን ሁሉ የሚመዝነው ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ ነው። አድርባይነት በመልካም ማኅበረሰብ የተጠላ፣ የተናቀ፣ የማይፈለግ ብቻ ሳይሆን በህገወጥነት የሚያስቀጣም ባህርይ ነው።

2. አድርባይነትን የት እንፈልገው?

1. ሥልጣን: ተጠያቂነት የጎደለው ሥልጣን ባለበት አድርባይነት ሊኖር እንደሚችል እንጠብቅ። ያልተገደበ ሥልጣን አድርባይነትን ያፋፋል።

2. ጥቅም: ጥቅም (በተለይም ገንዘብ) ባለበት ቦታ ሁሉ አድርባይነት የመኖሩ እድል ከፍተኛ ነው። አድርባዮች ያለአግባብ ሲበለጽጉ የዳር ተመልካቾች “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በማለት ሊቀላቀሏቸው ይችላሉ።

3. ሁኔታ: ሰዎች አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ወኔ ሊከዳቸው ይችላል። ለምሳሌ ሰቆቃ (ቶርቸር) የበዛበት ሰው ወይም ከገመተው በላይ ማባበያ የቀረበለት ሰው ህሊናው የሚያዘውን ብቻ የመፈፀም አቅም ሊያጣ ይችላል። “እኔ ባላደርገውም ሌላ ሰው ያደርገዋል” የሚለው ስሜትም ለአድርባይነት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው።

4. ጋርዮች: ለጋራ ጥቅም በኅብረት መሠራት በሚኖርበት ጊዜ አድርባዮች ከሥራው ድካም ተሸሽገው ከጥቅም ለመጋራት ግን ከሁሉ ቀድመው ይገኛሉ። አድርባዮች “ከጋራ ሀብት በጋራ ኃላፊነት ስሜት መጠቀም” የሚባል ነገር አያውቁም።

5. መረጃ: የመረጃ፣ የእውቀትና የግንዛቤ እጥረት ባለበት አድርባይነት ይፋፋል። ነገሮች ግልጽ ባልሆኑት፤ የትኛው ህግ በሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ያለየበት እና ብዥታ የበዛበት ሁኔታ ለአደርባይነት ምቹ ነው። አድርባዮች አውቀው መረጃን በማዛነፍ ለራሳቸው የተመቸ ሁኔታን ይፈጥራሉ።

6. ውድድር: የተፋፋመ ውድድር፣ ፉክክር ወይም ደግሞ ጦርነት ባለበት ሁኔታ ማጭበርበር፣ መዋሸት፣ ማታለል ተራ ነገር ይሆናል። ለማሸነፍ አሊያም ከሽንፈት ለመዳን ሰዎች በሌላ ጊዜ የማያደርጓቸውን መጥፎ ነገሮች ያደርጋሉ። የተከበሩ የሥነምግባር መርሆዎች ይጣሳሉ። አድርባዮች ውድድሮችን ተለማምጠውም ሆነ አጭበርብረው ይቀድማሉ።

7. ስኬት: ከመጠን ያለፈ ለስኬት መጓጓት ለአድርባይነት መንገድ ይከፍታል። ለምሳሌ ዝናን፣ መታወቅን ከመጠን በላይ መሻት። ለግል ስኬቱ ከመጠን በላይ የሚጨነቅ ሰው በሌላ ጊዜ ህሊናው የማይፈቅድለትን ሥራ ሊሠራ ይችላል።

3. “ወይን ለመኖር”

ለጥቅም ብሎ የኢሕአዴግ ድርጅቶች (ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴግ) ወይም አጋር ድርጅቶች (አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ) አባልነት ፎርም መሙላትና በህወሓት ፈቃድ ማደር “ወይን ለመኖር” የሚል ስላቃዊ ስያሚ ተሰጥቶታል። “ወይን ለመኖር” በአሁኑ ሰዓት አገራችን እያዋረደ ያለ የአድርባይነት ዓይነት ነው።

ሁሉን ጠቅላይ (totalitarian) አገዛዝን በማስፈን “ወይን ለመኖር” ለህወሓት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ ስልት ነው። የወይን ለመኖር ዓላማ ዜጎችን መቆጣጠር ነው። “ወይን ለመኖር” ኢትዮጵያዊያን የህወሓትን ኃይል በመጠን በላይ አግዝፈው፤ የራሳቸውን ደግሞ አንኳሰው እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። “ወይም ለመኖር” በርካታ ወገኖቻችን በብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደኢህዴግ፣ አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ… ውስጥ ገብተው እራሳቸውን እያዋረዱ፤ ወገናቸውን እያሳረዱ፣ አገራችውን ዘርፈው ለዘራፊው ህወሓት እንዲያስረክቡ እና ማኅበረሰባዊ ቀውስ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል።

4. ምን ይደረግ?

1. ከሁሉ አስቀድሞ ለራሳችን ክብር እንስጥ፤ ለጥቅም ወይም በፍርሃት ምክንያት የኢሕአዴግ አባልነት ፎርም በመሙላት ባርነትን አንቀበል።

2. ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለዜጎች ነፃነት መሠረት መጣል የሚቻለው አድርባይነትና አድርባዮችን በመታገል መሆኑን እንቀበል። አገር በአድርባዮች እንደማትገነባ ማወቅ።

3. በማናቸውም ምክንያት ራሳቸውን ኢሕአዴግ ውስጥ ያገኙ የሕዝብ ወገኖች እዚያው ውስጥ ሆኖ ኢሕአዴንግ የማፍረስ ሥራ እንዲሠሩ ማበረታታት። የኢሕአዴግ መዋቅር ራሱ ኢሕአዴን ለማዳከሚያነት መጠቀም።

4. “ወይን ለመኖር” የኢትዮጵያን ሕዝብ ያዋረደ፤ ለትውልድ የሚተርፍ የስነልቦና ኪሳራ ያደረሰ ማኅበራዊ በሽታ እንደሆነ እውቅና ተሰጥቶት ጥንቃቄ ማድረግ።

Filed in: Amharic