>

ህግ በማስከበር ስም እነ ዘመነ ካሴን ማሳደዱ ይብቃ...!!!  (አቶ ክርስቲያን ታደለ)

ህግ በማስከበር ስም እነ ዘመነ ካሴን ማሳደዱ ይብቃ…!!!

 አቶ ክርስቲያን ታደለ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የፓርላማ ስብሰባ ጭምር የወንድሞቻችን ጉዳይ ተነስቶ በአዳራሽም ከአዳራሽ ውጭም ብዙ የሀሳብ ልውውጦች አድርገናል። የፌዴራል መንግስት የፖለቲካ እና የፀጥታ አመራሮች ጉዳዩ በሰላም እንዲቋጭ ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው፤ አላቸውም። መሰረታዊ ጉዳይ በክልሉ በኩል ማለቅ የነበረባቸው አንዳንድ ጉዳዮች አለመቋጨታቸው ነው። የአማራ ክልል መንግስት ባለፈው የክልሉ ምክርቤት ስብሰባ ወቅት የምሕረት አዋጅ አውጆ እነዘመነን ጨምሮ የሚሳደዱ ወንድሞች ወደ ሰላም እንዲገቡ የሚደረገውን ጥረት በባለቤትነት እንዲመራ ንግግር አድርገን የነበረ ቢሆንም ሳይፈፀም ምክርቤቱም ለእረፍት ተበትኗል።

ጉዳዩ እስካሁን ድረስ እልባት ያላገኘው በክልሉ መንግስት በኩል ባሉ መጎረባበጦች ምክንያት ብቻ መሆኑን መግለጽ እፈልጋለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጭምር የመንግስታቸው ምርጫ ሰላም ብቻ መሆኑን አስረግጠው የተናገሩ በመሆኑ፤ በክልሉ በኩል ጉዳዩ ከግል ስሜት ከፍ ባለ መንግስታዊ ትክሻ እንዲያዝ ሁሉም በጎ ጫና እንዲያሳርፍ ማሳሰብ እወዳለሁ። እነዘመነን ጨምሮ መንግስት ሕግ ማስከበር እያለ በሚጠራው ዘመቻ የሚሳደዱ ልጆች የሰላም የመፍትሔ አማራጩን እንደሚቀበሉትም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ከዚህ አንፃር እንደአንድ የሕዝብ እንደራሴና የወገኖቹ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ዜጋ የማደርገውን ጥረት ያልተገባ ስም የምትሰጡ እና እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማኮላሸት የምትታትሩ ወገኖች እውነታውን በመረዳት በጎ ሚና እንድትወጡም መልእክቴን አስተላልፋለሁ። የክልሉ አመራሮችን ባልተገባ ሁኔታ ወደ ማሳደድ ዘመቻ እንዲገቡ የወተወታችሁና አብራችሁ መክራችሁ ውሳኔ ያሳለፋችሁ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም በእናንተ የጥፋት ምክር እስካሁን ከሕግ ውጭ የተገደሉ ወንድሞቻችን ጥፋት ይበቃልና ከመሰል ስምሪታችሁ ትታቀቡ ዘንድ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ።

በዚሁ አጋጣሚ የግፍ እስረኞች እንዲፈቱ ያቀረብነውን ውትወታ ተቀብላችሁ በከፊል ስለፈፀማችሁ በየደረጃው ያላችሁ የፖለቲካና የፀጥታ አመራሮችን እያመሰገንሁ፤ ዛሬም ድረስ ባልተገባ ሁኔታ በእስር የሚንገላቱ ወገኖችንም ከእስር ትፈቱ ዘንድ የተለመደውን ውትወታ አቀርብላችኋለሁ።

Filed in: Amharic