>
5:13 pm - Tuesday April 20, 1824

የማይታመኑ ብልጽግናዎች ተለዋዋጭና አደገኛ አቋም  (ግርማ ካሳ)

የማይታመኑ ብልጽግናዎች ተለዋዋጭና አደገኛ አቋም

ግርማ ካሳ


የህወሃትን የአዲስ አመት መግለጫ ተከትሎ፣ አቶ ታዬ ደንድዓ፣  ቅድመ ሁኔታን ያስቀመጠ ትዊተር ለጥፈዋል፡፡ አቶ ታዬ የብልጽግና  ፓርቲ በተለይም የቀድሞ ኦህዴድ አንጋፋ ከሚባሉ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ሲል ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመናጋገር ዝግጁ እንደሆነ ነበር የገለጸው፡፡ ለዚህም እነ አቶ ደመቀ መኮንን ያሉበት አንድ የተደራዳሪ ቡድን መሰየሙ ይታወሳል፡፡

ሆኖም አቶ ታዬ ደንድዓ  ከህወሃት ጋር ለመደራደር ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ አለበት ነው ያሉት፡፡ ህወሃት ትጥቅ መፍታት አለባይ የሚል፡፡  ሕወሃት ትጥቅ እንዲፈታ መጠየቅ ማለት ድርድር አንፈልግም፣ ጦርነቱ ይቀጥል ማለት ነው፡፡

አቶ ታዬም ይሄን ሲሉ  ምን አልባት በነ ዶር  አብይ እንዲጽፉ ተነግሯቸው ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡

ሕወሃት ትጥቅ እንድትፈታ ሕወሃትን  በጦርነት ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ያ ቢሆን ለሁሉም ተመራጭ እርሱ ነበር የሚሆነው፡፡  ግን ያ አልሆነም፡፡ የአብይ አገዛዝ ህወሃትን ትጥቅ ማስፈታት ሲችል ፣ ለሕወሃት እድሜ ለማስረዘም በሚል ብዙ እድሎችን አቃጥሏል፡፡ ያውም ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ እየነበረው፡፡

ከአንድ አመት በፊት ሕወሃትን በጦርነት የማሸነፍ አቅም ነበር፡፡ በተለይም ሕዝቡ በነቂስ ተነቃንቆ በነበረበት ወቅት፡፡ ነገር ግን ዶር አብይ አህመድ ጦርነቱ ሳያልቅ በችኮላ ውጊያው  እንዲቆም አደረገ፡፡

ያኔ ለሰላም በሚል ነበር ያንን ያደረገው፣ ግን  ብዙዎቻችን “ሰላም አይመጣም፣ ጦርነቱን በቀጠሮ ለመቀጠል የተደረገ ውሳኔ ነው” ነው በሚል አጥብቀን ተቃወምን፡፡

አሁን የብልጽግና መንግስት የህዝብ ድጋፍ የለውም፡፡ ቀላል የማይባሉ እንደውም ከብልጽግና ሕወሃት ትሻለናለች እያሉ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሕዝብ ድጋፍ ሳይኖር ውጤት ማስመዝገብ አይችልም፡፡

መከላከያና የአማራና አፋር ኃይሎች ግስጋሴያቸውን ወደ ትግራይ እንዳያደርጉና  ውጊያ እንዲያቆሙ ከተደረገ በኋላ ምን ሆነ ?

# በእቅድና ህግን  በማስከበር ስም፣  ብልጽግናዎች በአማራ ክልል፣  በፋኖ ላይ ጦርነትና ዘመቻ ከፈቱ ፡፡ በአማራ ክልል ያለው ኃይል እንዲዳከምና እንዲከፋፈል አደረጉ፡፡

# ህወሃት   ራሷን አጠናክራ እንድትመጣ ሁኔታዉ በአራት ኪሎ ተመቻቸላት፡፡፡

# ዶር አብይ ራሱ እንዳመነው፣ ብልጽግናዎች  አይሮፕላኖች ትግራይ በሱዳን በኩል ሲገቡ አይተው እንዳላዩ ነበር  የሆኑት፡፡ ምን አልባት በውስጥ ተስማምተውም ይሆናል አይሮፕላኖች እንዲገቡ አድርገውም ይሆናል፡፡

# በሱዳን በኩል ሳምሪ የተሰኙት ሲደራጁ፣ ሲታጠቁ፣ በዚያም በኩል ትንኩሳ ሲፈጽሙ፣ የአብይ መንግስት ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ እንኳን በሱዳን በኩል በአማራ ክልል ላይ የተከፈተውን ጥቃት አስመልክቶ ሱዳን አርፋ እንድትቀመጥ ያደረገው ነገር የለም፡፡ መግለጫዎች በማውጣት፣ የሱዳንን አምባሳደር ጠርቶ በማስጠንቀቅ  ለተባበሩት መንግስታት ሆነ በአፍሪካ ህብረት ሱዳን አርፋ እንድትቀመጥ ግፊት ለማድረግ አልሞከረም፡፡

ስለዚህ በአሁኑ ጦርነት ሕወሃትን የማሸነፍ አቅም በመከላከያ ዘንድ የለም፡፡ ከሁለት አመት በፊት በሶስት ሳምንት ውስጥ ነበር መቀሌ የተገባው፡፡ አሁን ይኸው ሁለት ሳምንት ሆነ ቆቦን ማስለቀቅ አልተቻለም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ሕወሃትን ማሸነፍ ካልተቻለ፣ ብቸኛ አማራጩ ድርድር ብቻ ነው፡፡

አቶ ታዬም ሆነ ብልጽግናዎች፣ እንደ እስስት ቃላቸውን መቀያየር ማቆም አለባቸው፡፡ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር መቅረብ አለባቸው፡፡ በመጨረሻ ሰዓት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የሰላምን በር መዝጋት ነው፡፡ የአማራና የአፋር ወጣቶች፣ እንዲሁም በዚያኛው በኩል የትግራይ ወጣቶች እንዲያልኩ፣ ሰሜኑ የአገራችን ክፍለ በጦርነት እንዲቀጠል መፈለግ ነው፡፡

Filed in: Amharic