ከሰላም ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ ገደል ነው…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ጦርነት ሳይጀመር በፊት ነገሮች ወደ ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ ገና በጠዋቱ ምልክቶች ሲታዩና የጦርነት አታሞ ሲመታ፣ ጦርነቱም ሲጀመር፣ ጦርነትም እየተካሄደ በነበረበት ወቅትም ይሁን ተፋላሚ ወገኖች ለሰላም ድርድር ፈቃደኝነታቸውን ገልጸው ተኩስ ባቆሙበት እና ለሰላማዊ ድርድር ፍላጎት ባሳዩበት ወቅት ሁሉ ድምጼን ለሰላም እና ለሰላም ብቻ ማሰማቴ ትክክለኛውን መንገድ መምረጤን ከማረጋገጡም በላይ ትልቅ የህሊና እረፍት ይሰጠኛል። ጦርነቱ በሰላም ብቻ እንዲፈታ ያለመታከት በመወትወቴ ኩራት ይሰማኛል። አሁንም ጽኑ እምነቴ ነው። ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይህ ግጭት በሰላማዊ መንገድ ብቻ ሊፈታ እንደሚችልና እንደሚገባም፤ ሌላው አማራጭ የማንወጣው የእልቂት ገደል እንደሆነ ሳሳስብ፣ ስጽፍም፣ ስናገርም ቆይቻለሁ።
አንዳንዶች እንደ ጅል ይቆጥሩኝ ነበር። ግራ የተጋቡ ደግሞ ያሬድ ምነካው ይሉኝ ነበር። እንዴት ከህውሃት ጋር የሰላም ድርድር ይደረግ ትላላችሁ በሚል የሰላም ጥሪ ባደረግን ሰዎች ላይ ያልወረደብን የስድብ ናዳና እርግማን የለም። እብደቱ የጠናባቸው ካድሬዎችም ለሦስት አሥርት አመታት ስንታገለው ከቆየነው ከወያኔ ጋር ሊያዛምዱን ጥረዋል። ‘የጁንታም ተባባሪ’ ብለውናል። የሰላም ድምጽ ግን ሁሌም፣ ሁሌም፣ ሁሌም ያሸንፋል።
ዛሬ ከዚህ ሁሉ እልቂት፣ የእርስ በርስ ደም መፋሰስ እና የሀገር ሃብት ውድመት በኋላም ቢሆን ሁለቱም ወገኖች በተመሳሳይ ወቅት በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት በሰላም ለመነጋገርና ግጭቱን በድርድር ለመፍታት በመፍቀዳቸው እጅግ ደስ ብሎኛል። ድርድሩ ይሳካል፣ አይሳካም የሚለውን በሂደት የሚታይ ይሆናል። በእርግጥ የፌደራል መንግስቱ የተናጠል ተኩስ ከማቆም ጀምሮ ለሰላም ያለውን ፍላጎት ደጋግሞ ማሳየቱን አደንቃለሁ። ዘግይቶም ቢሆን ህውሃትም ሰላም እፈልጋለሁ ማለቱ ከልብ እስከሆነ ድረስ እሰየው የሚያሰኝ ነው። ሁለቱም ወገኖች ለሰላማዊ ድርድር ፈቃደኞች እና ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው እጅግ የሚደገፍ ትልቅ ውሳኔ ነው። ሁለቱንም ወገኖች ለዚህ ውሳኔያቸው እያመሰገንኩ ድርድሩም የተሳካ እንዲሆን ደግሞ ከልቤ እመኛለሁ! የሕዝባችን ስቃይ መቆም አለበት።
ከሰላም ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ ገደል ነው!
በሰላም እንጸናለን፣ በጦርነት ግን እንፈርሳለ
ሰላም ለኢትዮጵያ!!