>

በእነ ልደቱና ታምራት የቀረበው እጅግ አደገኛ ፀረ አማራ ትርክት...? (ጌታቸው ሽፈራው)

በእነ ልደቱና ታምራት የቀረበው እጅግ አደገኛ ፀረ አማራ ትርክት…?

ጌታቸው ሽፈራው

ትህነግ ሰሞኑን በልደቱ አያሌውና ታምራት ላይኔ በኩል በዚህ ወቅት ራሱ ማለት የማይደፍረውን ፀረ አማራ ትርክት እያሰራጨ ነው። እኔ ስናገረው አማራ የበለጠ ስለሚያመር አማራ ናቸው በሚባሉት በኩል ላሰራጭ ብሎ አሰራጭቶታል። ጠቅለል ሲል፦

1) ልደቱ በ TMH ጦርነት ይብቃ በሚል፣ እንዲሁም ታምራት የትህነጉ  ስታሊን ባቋቋመው ዛራ የሚባል ሚዲያ “ይድረስ ለአማራ ህዝብ” የሚል አማራን የሰደቡበት፣ የወነጀሉበት፣ የፈረጁበት ፅሁፍ ለቀዋል። የሁለቱም ፅሁፍ የአማራ ህዝብ በሻዕቢያ ፕሮፖጋንዳ፣ በጭፍን ጥላቻ፣ በድንቁርና፣ በክህደት ትግራይን ወርሮ ወንጀል እየፈፀመነ ነው ብሎ የሀሰት ትርክት የሚያስቀምጥ ነው። አማራን የሁሉም ወንጀል ባለቤት አድርገውታል።

2) የሁለቱም ፅሁፍ  ከትህነግ ስትራቴጅ የተነደፈ ነው። ትህነግ የእነዚህን ሁለት ግለሰቦች ፅሁፍ የፈለገው ለኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም። ለውጭ ወዳጆቹም “ይሄው የአማራ ልሂቃንም ይህን ሁሉ ወንጀል የሚፈፅመው አማራ ነው ብለው አምነዋል” ብሎ ተርጉሞ በህዝብ ላይ የሀሰት ምስክር አድርጎ  እያቀበለ ነው። እንደ ድሮው የፀጥታ ኃይሉን፣ ልሂቃንን ብቻ አይደለም መፈረጅ የተፈለገው። አሁን በሀሰት ትርክት ወንጀለኛ ማድረግ የተፈለገው መላ አማራን ነው። ትህነግ በ1968 ከፃፈው ፀረ አማራ ማንፌስቶ በላይ የእነ ልደቱ የሰሞኑ  ትርክት እጅግ አደገኛ ነው። መስከረም አበራ በቅርቡ የልደቱን ፅሁፍ ስትተች “የህወሓትን መነፀር አድርጎ ነው የፃፈው” ብላለች። እውነታው ከዚህ ከፍ ይላል። በትህነግ እጅ ከተፃፈ ስትራቴጅ የተቀዳና ተሻሽሎ የቀረበ ነው።

3) የልደቱና የታምራት ፅሁፍ አዲስ ፀረ አማራ ትርክት ማስረፅ ላይ ብቻ ያተኮረ  አይደለም። የነበረ ትርክትም ይቀይራል። አማራ በራያ፣ በጠለምት፣ በአበርገሌ ተወርሮ ባለበት፣ ጦርነቱን ትህነግ በጀመረበት የሻዕቢያ ወረራ አድርገው አስቀምጠውታል። አማራ ህልውናውን ለማዳን የሚያደርገውን ጦርነት የውጭ ወረራ አደረጉት። አማራ ራሱን በሚከላከልበት ጦርነት ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ትግራይን የሚያጠቃ ወንጀለኛ አደረጉት። ወራሪውን ትህነግ በውጭ  ጠላት የተጠቃ፣ እየተጠቃ ያለውን አማራ ከውጭ ኃይል ጋር ሆኖ ወገኑን የሚያጠቃ ባንዳ አደረጉት። ከውጭ ጠላት ጋር ሆኖ በአማራው ላይ የዘመተውን ትህነግን አረመኔ ታጣቂ የውጭ ወረራን የሚከላከል አርበኛ፣ ወገኑ ተወርሮ የሚከላከለውን አማራን የሻዕቢያ ቅጥረኛ አደረጉት። ይህ ሆን ተብሎ በትህነግ የተቀረፀላቸው የሀሰት ትርክት ነው።

4) የሁለቱም ፅሁፍ አላማ ጭንቅ ውስጥ የገባውን ትህነግን ማዳን ነበር። ከሁለት አመት በፊት ትህነግ ጫካ እያለ እነ ልደቱና ታምራት “አገር ወደድ ኢትዮጵያዋያን” የሚል ህቡዕ ቡድን አዋቅረው በወቅቱ በአማራ ክልል ስር የነበሩት ራያ፣ ወልቃይት፣ ጠለምትና አበርገሌ ላይ የውጭ ሰላም አስከባሪ ይስፈር፣ ትህነግ በወልቃይት ኮሪደር ይሰጠው ብለዋል። ይህን ሰነድ አማራዎች ነን ብለው ለውጭ ተቋማት ተርጉመው ሰጥተዋል። ነገሮች ካለፉ በኋላ ልደቱ  360 ላይ ቀርቦ ሰነዱ የእኛ ነው ብሏል። ስለህቡዕው ቡድን አባላት ስም እየጠራ ተናግሯል። ያኔ በህቡዕ ቡድን አማራን ወንጅለዋል። ዛሬ በግልፅ መጥተዋል። አሁንም የመጡት ትህነግ ጭንቅ ላይ ሲሆን ነው። አማራ እስከ ሸዋ ሲወረር ትንፍሽ አላሉም።

5) ለሁለቱም ይህ ጦርነት ለትግራይ እንጅ ለአማራም ለኢትዮጵያም የህልውና ጉዳይ አይደለም። የተጨፈጨፈው አማራ፣ አፋር ይህ ጦርነት አያገባህም፣ ምንክን ነካብህ ተብሏል። ትህነግ ግን ትክክል ነው፣ አርበኛ ነው ተብሏል።

6) ሁለቱም ጦርነት እንዲበቃ አይፈልጉም። በህወሓት የበላይነት እንዲጠናቀቅ እናግዘው ብለዋል። ታምራት ላይኔ የትግራይ ልጆች በጀግንነት እየታገሉ ያሉት ለአገር ለሉአላዊነት ነው ብሏል። ልደቱ መላው አገር ወዳድ ከህወሓት ጋር ይቁምና ሻዕቢያን እንውጋው ብሎ ጥሪ አቅርቧል። ሁለቱም ኢትዮጵያ በኤርትራ የተወረረች አስመስለው በኤርትራ ላይ እንነሳ ብለዋል። የተወረ*ረው አማራና አፋር፣ ወራሪው ትህነግ ሆኖ ተወራሪውን ትህነግ ወ**ራ*ሪው ሻዕቢያና አማራ ተደርጎ ተፅፏል።

7) ሁለቱም አማራን በጥላቻ ተነሳስቶ ትግራይን የወረረ አስመስለው አማራውን ከጥላቻ ውጣ፣ ህወሓትን አትጥላው ይላሉ። የቆየ ቂም እንተው እያሉ ይመክራሉ። ህወሓት ወዳጅህ ነው ይሉና ተመልሰው  ሻዕቢያ የምን ጊዜም ጠላትህ ነው እያሉ ሊሰብኩት ይሞክራሉ።

8) ሁለቱም እርግማናቸውም ምክር የሚሉትም  ለአማራ ብቻ ነው። የትግራይን ህዝብ ቀርቶ ትህነግን አይወቅሱም። በዚህ ወቅት በበርካታ አቅጣጫ በትህነግ የተወረረውን አማራ የሁሉም ወንጀል ባለ እዳ አድርገውታል።

በአጭሩ ያቀረብኩት የሁለቱ ተላላኪዎች ፅሁፍ ይዘት እንዴት በተደራጀ መልኩ በአማራ ላይ አደገኛ ትርክት ለመትከል እንደተፈለገ ለመግለፅ ብቻ ነው። ልደቱ አያሌውና ታምራት ላይኔ በአማራ ህዝብ ላይ ያወረዱትን የስድብ መአት፣ የወንጀል አይነት፣ የሀሰት ትርክት ብዛት ስሜታችሁን ዋጥ አድርጋችሁ  በትህነግ ሚዲያዎች ያስተላለፉትን ፅሁፋቸውን ብታዩት የተቀናጀውን የትህነግ አላማ በደንብ ትረዱታላችሁ!

የሆነ ሆኖ የትህነግ ተላላኪዎች ስለጮሁ የሚድን ወ*ራ*ሪ የለም።  በህዝባችን ብርታት እናሸንፋለን!

Filed in: Amharic