>
5:13 pm - Friday April 19, 0458

የትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ ድንቅ ስብእና...!  (ዮሀንስ ሞላ)

የትዝታው ንጉስ ማህሙድ አህመድ ድንቅ ስብእና…!

ዮሀንስ ሞላ

ከምኑም ከምኑም፣ ከድምጹም፣ ከለዛውም፣ በድምጹ ካዝናናን እና ካስቆዘመን፣ ካስተማረን እና ካጫወተን፣ ከመከረን እና ካስደሰተን፣ ከሁሉም ከሁሉም ሰውነቱን፣ የልቡን ግዝፈት፣ ርህራሄውን ስወደው።

ዐይኑ ላይ ያለውን ብርሀን ስወደው።

ለሙያ አጋሮቹ ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ስወደው።

ለሰው የሚራራበትንና የሚንሰፈሰፍበትን ሁኔታ ስወደው።

ከሁሉም ከሀሉም ትናንትን ብቻ ሳይሆን ነገንም ባለመርሳት ውስጥ በትህትና አካሄዱን ስወደው።

ስለሞት ባለው ፍልስፍና እና አረዳድ የተነሳ፣ ሕይወትን በአግባቡ የመኖሩን ነገር ስወደው።

ራስ አጠባበቁን እና ራስ አከባበሩን ስወደው።

አንድ ጊዜ ቨርጂንያ የእግር ጉዞ ሽርሽር ሲል ተያይተን ሰላም ስለው እጅ አነሳሱ፣ ለሰማይ ለምድር የከበደ፣ የሚወደድ እና የሚከበር ትልቅ ሰው፣ በስስት የሚታይ ማህሙድ አህመድ ሳይሆን፣ የድሮ አስተማሪውን ያገኘ ትሁት ተማሪ ያህል በፍጹም አክብሮት እና ትህትና ነበር።

ደንቆኝ ደንቆኝ አልበቃ አለኝ። ዐይኑ ላይ ያየሁት ደስታ ትዝ ብሎኝ፣ ሌላ ቀን በማይመች ሁኔታ መንገድ ቀይሬ ሰላም አልኩት። በተመሳሳይ ትህትና እና ስስት፣ ተሽቆጥቁጦ አክብሮ ሰላምታውን መለሰ። አንድ ሁለት ጊዜ ዝግጅቶች ላይ በቅርበት የማውራት ዕድሉን አግኝቼ ነበር። በቃ ማህሙድ ማህሙድ ነው። ጽኑ ነው። አይለዋወጥም። ባለበት ቦታ ብርሀን ይኖራል። ርህራሄ ይኖራል። ፍቅር ይኖራል። ሙቀት ይኖራል።

የሙያ አጋሮቹ ዜና እረፍት ሲሰማ አኳኋኑ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ የማይለዋወጥ ነው። ድሮ እንኳን ዜና እረፍት ሲዘገብ እሱ ሲንሰፈሰፍ ያለው ሁኔታ፣ የትዝታ ሙዚቃዎቹን ያህል አይረሳም።

ለባልደረቦቹ በቅርበት የሚያደርገውን እና የማያደርገውን ባላውቅም፣ በሚታየው ልክ ግን የሙያ ታማኝነት (professional integrity) ያለውና ፈሪሀ እግዚአብሔር የሞላባት እንደሆነ መናገር ይቻላል።

የእውነት ብዙ ነገር ብል ደስ ይለኝ ነበር። ግን አንዳንዴ ስለአንዳንድ ሰው ብዙ ማለት አይቻልም። ቃላት ይለግማሉ። ስሙ ራሱ የሚያስተዋውቀው ነገር ያለው ብራንድ ነውና ሁሌም ተከብሮ ተወዶ ይኑርልን።

“ሸጋው የአገሬ ልጅ ሚዛኑ ሚዛኑ

እስኪ ሰዎች ሁሉ ባንተ ይመዘኑ”

ዕድሜና ጤና ይስጥልን።

Filed in: Amharic