>

የከሸፈ ድርድር አሸናፊው ያለየው ጦርነት...! Dw

የከሸፈ ድርድር አሸናፊው ያለየው ጦርነት…!

Dw


ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን አዉስትሬሊያ፣ኔዘርላድስና ዴንማርክ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተፋላሚ ኃይላት በአፍሪቃ ሕብረት መሪነት በሚደረገዉ ድርድር እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።ምዕራባዉያኑ መንግስታት በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ኤርትራ መካፈሏን አዉግዘዋል።ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ አማራጭ እንደማይሆን ተፋላሚ ኃይላት እንዲገነዘቡት አሳስበዋልም

የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ያደርጉታል ተብሎ የነበረዉ ድርድር ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል።ድርድሩ ለመሰረዙ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት በግልፅ ያሳወቁት ነገር የለም።ስለጉዳዩ በቅርብ እናዉቃለን የሚሉ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ግን ድርድሩ የተሰረዘዉ «በሎጂስትክስ ችግር» ምክንያት ነዉ።በአደራዳሪነት ከተመረጡት ሶስት ሽማግሌዎች የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸዉ «በቀጠሮ መደራረብ ምክንያት» ቢያንስ በመጀመሪያዉ ዙር ድርድር ላይ መገኘት እንደማይችሉ ድርድሩ ከመሰረዙ በፊት አስታዉቀዉ ነበር።ድርድሩ እንዲደረግ ከፍተኛ ግፊት የሚያደርጉት የአፍሪቃ ሕብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ሌሎቹ አደራዳሪዎችና ተደራዳሪዎችም ስለጉዳዩ ግልፅ ማብራሪያ አለመስጠታቸዉ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።

ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን አዉስትሬሊያ፣ኔዘርላድስና ዴንማርክ ባለፈዉ ሮብ በጋራ ባወጡት መግለጫ ተፋላሚ ኃይላት በአፍሪቃ ሕብረት መሪነት በሚደረገዉ ድርድር እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።ምዕራባዉያኑ መንግስታት በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ኤርትራ መካፈሏን አዉግዘዋል።ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ አማራጭ እንደማይሆን ተፋላሚ ኃይላት እንዲገነዘቡት አሳስበዋልም።ተፋላሚ ኃይላት ግን ቢያንስ እስካሁን ጥሪና ጥያቄዉን ከቁብ የቆጠሩት አይመስልም።እንዲያዉም ስለድርድር በሚወራበት ባሁኑ ወቅት በተለይ ኢትዮጵያና ኤርትራን በሚያዋስነዉ ድንበር የገጠሙት ጦርነት መፋፋሙ ተዘግቧል።ሕወሓት መላዉ የትግራይ ሕዝብ ለጦርነቱ እንዲከት ባለፈዉ ዕሁድ በድጋሚ ጠይቋልም።ድርድር ሲጠበቅና ሲጠየቅ ዉጊያዉ መቀጠሉ ተፋላሚ ኃይላት ጠባቸዉን በድርድር ለመፍታት «አይፈልጉም» የሚል ሥጋትና ጥርጣሬ አጭሯል።

የድርድሩ ተስፋ ለጊዜዉም ቢሆን መጨናጎሎና ምክንያቱ መድበስበሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች ድርድርን እንደ ልዩነት መፍቻ ይጠቀሙበታል ወይ የሚል ጥያቄም ማስነሳቱ አልቀረም።እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያ  እሁለት ተገምሰዉ የነበሩ የአፍሪቃ መንግስታትን አደራድራ አንድ ማሕበር እንዲመሰርቱ ረድታለች።ሱዳኖችንና ናጄሪያ (ቢያፍራዎችን) ሽምግላለች።የቻዶች ዉዝግብ፣ የፖሊሳሪዮ በፖሊሳርዮ በኩል የአልጄሪያና የሞሮኮ ጠብ እንዲረግብ እንደመደራደሪያ ማዕከል አገልግላለች።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ግን የራሳቸዉን ጠብ፣ግጭት፣ ልዩነታቸዉን በድርድር ያስወገዱበት ጊዜ የለም።ካለም አይታወቅም።

ነጋሽ መሐመድ

Filed in: Amharic