>

የእስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤት በፖሊስ መፈተሹን ምንጮች ተናገሩ...! (ጋሻ መልቲ ሚድያ)

የእስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤት በፖሊስ መፈተሹን ምንጮች ተናገሩ…!

ጋሻ መልቲ ሚድያ


የቀድሞው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤት በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች መፈተሹን በፓርቲው አመራርነት ውስጥ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ያሉበት የማይታወቀው የአቶ እስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤት በፖሊስ የተፈተሸው ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም. መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ከሚኖሩበት የባለቤታቸው እናት መኖሪያ ቤት ውስጥ ባሳለፍነው ቅዳሜ የተደገረው ፍተሻ ዓላማው ምን እንደሆነ እና በፍተሻው በኤግዚቢትነት የተወሰዱ ነገሮች ስለመኖራቸው ከሚመለከተው አካል መረጃ ማግኘት አልተቻለም።

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፌደራል ፖሊስ አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በተመሳሳይ ይህንን በተመለከተም በፍተሻው ወቅት በቦታው የነበሩ የአቶ እስክንድር ቤተሰቦችን በስልክ ለማነጋጋር ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ነገር ግን በአደባባይ ሳይታዩ ወራት ያለፉት አቶ እስክንድር በመኖሪያ ቤታቸው ተደብቀው ይገኛሉ የሚሉ መረጃዎች መዘዋወራቸውን ተከትሎ የተደረገ ፍተሻ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው ምንጫችን አክለዋል።

የቀድሞ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ከፓርቲው መሪነት እና አባልነት መልቀቃቸው ከነገረ በኋላ በአደባባይ አልታዩም።

አቶ እስክንድር ነጋ የጻፉት ነው የተባለ ደብዳቤ በፓርቲያቸው የማሕበራዊ መገናኛ ገጾች በተለጠፈ  ጽሑፍ ከፓርቲው መሪነት እና አባልነት መልቀቃቸውን አመልክተዋል።

በዚሁ ደብዳቤ ላይ አቶ እስክንድር መንግሥት እያደረሰብኝ ነው ባሉት ”አምባገናነዊ ጫና” ሳቢያ ለዚህ ውሳኔ መብቃታቸውን አመላክተዋል።

ከሰሜን አሜሪካ ቆይታቸው በኋላ በአደባባይ ያልታዩት የአቶ እስክንድር ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት አቶ እስክንድር፤ በህትመት መገናኛ ብዙሃን ተሳትፏቸው በመቀጠልም በመሰረቱት የፖለቲካ ፓርቲ ይታወቃሉ።

Filed in: Amharic