>

ፍርሃትን ያሸነፈ፤ ሞትንም የናቀ ትውልድ እንፈጥራለን! (አቶ ስንታየሁ ቸኮል)

ፍርሃትን ያሸነፈ፤ ሞትንም የናቀ ትውልድ እንፈጥራለን!

አቶ ስንታየሁ ቸኮል


ዓላማችን አልተፈታም፤ የብረት ካቴናዉ ግን ለጊዜውም ቢሆን ከእጃችን ተፈቷል። ዓላማችንን የማሰርም ሆነ የመፍታት  ሥልጣን የእኛ ብቻ ነው። ረብጣ ገንዘብ የለንም፤ ጠላታችን ግን ፍርሃት እንጂ ድህነት አይደለም።

“ሥጋን እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍራቸው፤ የተሸነፈ መገለጡ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና” ተብሎ ተጽፏል።

. . .ግፍን ተጠየፈዉ እንጅ ግፈኛዉን  አትፍራዉ፤ ሰዉን ለመበደል አትነሳ፤ የራስህን ጥቅም በሌላዉ ወገንህ ላይ በክፋት እርኩሰት ለመጫን የሕይወቱን የመኖር ፍላጎት ጉልበት አለኝ ብለህ  ለማስፈጸም  እስካልተነሳህ ድረስ እውነት ካንተ ጋር ናት። ይሄን አንግበህ ከባዱን ዳገት ለመውጣት በጽናት እስከተነሳህ ድረስ አንተ አትሸነፍም። ሊያሸንፉ የተነሱት ሁሉ ይወድቃሉ፤ ግፈኞች ናቸውና።

ምክንያቱም ሥጋን የሚገድል ገዢ እንጂ ህሊናህን የሚያሸንፍ ሃይል  ሊኖር አይችልም ነው አመክንዮው።

እርግጥ ነው ፍርሃት የሰዎች ተፈጥሯዊ ማንነት ቢሆንም ለክብራቸው ግን ፍርሃት የዘላለም እስር ቤት አይደለም። ለወገኖቼ  የምመክረዉ  ለነፃነትህ፣ ለክብርህ፣ ለማንነትህ አንገትህን አትስበር፤ ቅድሚ ፍርሃትን ተዋግተህ አሸንፍ የሚል ነው። ፍርሃትን ብቻ ሳይሆን ጥልማሞት ሞትንም ቢሆን ልንፈራው አይገባም። ሞትን የናቀ ትውልድ ምንጊዜም ድል አድራጊ ነው።

እውነትን ያነገበ ዓላማ ለጊዜዉ በውሸት ቢከበብም ተስፋው ግን አይጨልምም።  ወደፊት ብቻ ተመልከት፤ ዳገቱ ጉልበት ያዝላል አሰልቺ ፈተና አለዉ።

ያንተን ዋጋ ለማርከስ፥ ዛሬ በሌላዉ ያለመኖር የራሱን መኖር ለማረጋገጥ በአድርባይነት እና  በንዋይ ፍቅር የግል ፍትሆቱ የኮደኮደው  ስንኩል እምቧለሌ ቢከብህም፤ ይሄ አመለካከት የማታ ማታ መሸነፉ ግን አይቀርም። ተስፋችን ነገ እንጂ ዛሬ አይደለም! ስንኩላኑ ከሰፊው የታሪክ ማህደርህ ውስጥ ከግርጌ ማስታወሻነት የዘለለ ቦታ የላቸውም። ይህም ቢሆን ሚናቸው አንገት በሚያስደፋ ነውር እንጂ ደረት በሚያስነፋ ጀብዱ አይጠቀስም፤ ታሪክ ደግሞ አይዋሽም!

ሕግ በጉልበተኞች ሰደፍ መደለቁ እስካልቆመ ድረስ መከራዉ ከባድ ነው። የሕይወትህ ውጣዉረድ  መራራ ነው። ቤተሰብህ አሳዳጆች ይበዙበታል።

የጲላጦስ ፍርድ ስቀሉት እንጅ ልቀቁት አይደለም፤ የቄሳርን ፍርድና ግብር ስትቃወም እስከ ቀራኒዮ ሕይወትህ ይጎሳቆላል። እውነትን ግን ገድለው መቅበር አልቻሉም።  ቢቀብሩትም ትንሳኤ አለው።

ከሰዋዊ ክብራችን አውርደው ፍትህን ከጫማቸው ስር ያደረጉ ዘመን አመጣሽ ገዢዎች ትላንት በአፍ ጢማቸው ተደፍተዋል። ዛሬም ይወድቃሉ። የጽናት መንፈሳችን እንደማይሰበር፤ ተስፋችን እንደጨው እንደማይሟሟ አረጋግጥላቸዋለሁ። ፍትሃ ነገሥቱ፣ ድርሳናቱ የጀርባ ታሪካችን ሽንፈትን አይናገርምና። እየወደቅን እንነሳለን፤ እየገደሉን እንበዛለን። ምክንያቱም እኛ  ለነፃነት ሲሉ ጨዉ በአፋቸዉ የማይሟሟ፤ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ሥጋቸውን ለአሞራ ሰጥተዉ ያለፉ የነፍጠኞች ልጆች ነን።  ባርነትን የማያውቅ ነፃ ሆኖ ተፈጥሮ በነፃነት የኖረ የነፃ ሕዝብ አባል ነን።

ሰዉ በማንነቱ በጅምላ ተገድሎ፤ በነሲብ የሚቀበርባት  ኢትዮጵያ ሳትሆን፥ ፍትህ ያለአድሎ የሚሰፍንባትን ሀገር በተራዘመ ትግላችን በክንዳችን እናረጋግጣለን። ለነጻነቱ የሚወድቅ  ትውልድ  ደጁ ላይ ቆሟል።

በመጨረሻም

ባልደራስ ሕዝባዊ ዓላማን የሰነቀ ተቋም ነው በድርጅታችን ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮች ካሉ በጥሞና በመገምገም በውስጥ ድርጅታዊ  የዲሞክራሲ ባህል ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን በቅርቡ ለሚኖረን ታላቅ ጉባኤ አጥብቀን እንሰራለን ባልደራስ ተጠናክሮ ይወጣል።

በተደጋጋሚ በግፍ ስንታሰር  ከፍትሕ ጎን በመቆም ከጎናችን የተሰለፋችሁ መገናኛ ብዙሃን፣ የመብት አቀንቃኞች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማት፣    የመብቶች ጥበቃ ድርጅቶች ብሎም ሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦች በልዑል እግዚአብሄር ስም ምስጋናችን ይድረሳችሁ!

 

Filed in: Amharic