>

አብን ህይወት ዘርተው እንደተቋም ባቆሙት የአማራው ልጆች ፥ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በማጣጣር ላይ ይገኛል! (ዘሪሁን ገሠሠ)

አብን ህይወት ዘርተው እንደተቋም ባቆሙት የአማራው ልጆች ፥ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት በማጣጣር ላይ ይገኛል!

ዘሪሁን ገሠሠ


ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መጋቢት 11/2014 ዓ.ም ያከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጠናቀቅና የሚፈለገው አጀንዳ ቀርቦ ውሳኔ ሳይተላለፍበት መበተኑን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ጉባኤውን ውድቅ በማድረግ  ድርጅቱ እስከ ሰኔ 18 ድረስ ባሉት ጊዜያት ድጋሜ ጉባኤ እንዲያካሂድና ሳይቋጭ ያደረው የሪፎርም አጀንዳም ቀርቦ እንዲወሰን አስገዳጅ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ሚያዚያ 21-22/2014 ዓ.ም በአርባምንጭ ተገናኝቶ የመከረው የድርጅቱ ማ/ኮሚቴ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ማቋቋሙን የተገለፀ ቢሆንም ሂደቱ ላይ በነበረው ከደንብና ከአሰራር ጋር የተያያዙ ግድፈቶች የተቋቋመው  ኮሚቴ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቀርቷል፡፡

የማ/ኮሚቴው በድጋሚ  ሰኔ 12 ቀን/2014 ዓ.ም ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አዲስ የሪፎርም ኮሚቴ አዋቀረ፡፡ ይህ ኮሚቴም  በማዕከላዊ ኮሚቴው የተሰጠው ሀላፊነት በአንድ ወር ጊዜ (30 ቀናት)  ውስጥ ማለትም እስከ ሀምሌ 18/2014 ዓ.ም ድረስ አጠቃላይ ድርጅታዊ ሪፎርም የሚከወንበትን ጉባኤ እንዲያዘጋጅ ነበር፡፡

ነገርግን ይህ ኮሚቴ ከአንድ ወር በላይ የሆነ ጊዜ ፈጅቶም ጠቅላላ ጉባኤ ማከናወን አልቻለም፡፡ ምርጫ ቦርድም ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ ማለትም ሰኔ 18/2014 ድረስ የወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ ባለመደረጉ የወሰደው እርምጃም ሆነ ተጨማሪ የወሰነው የመጨረሻ የጊዜ ገደብ የማስቀመጥ ውሳኔ የለም፡፡

በዚህ መካከል የአብን የጠቅላላ ጉባኤ አመቻች ነሀሴ 27/2014 ዓ.ም በድርጅቱ ይፋዊ ገፅ ባወጣው መግለጫ መሠረት  ፦ << ኮሚቴውም የተሰጠውን ሃላፊነት በተገቢው መንገድ የተወጣና ስራውን ያጠናቀቀ ሲሆን ድርጅታችን  ያጋጠመው የፋይናንስና ሎጀስቲክ ውስንነቶች እንደተስተካከሉ ጉባኤውን በአጭር ጊዜ ውስጥ የምናካሂድ መሆኑን እንገልፃለን>> በማለት ቀደም ብለው ላለፉት ጊዜያት ሲያከናውነው የነበረውን ተግባር ማጠናቀቁን አስታውቆ ነበር፡፡

ዛሬ  ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም ነው፡፡  የአመቻች ኮሚቴውም ሆነ የድርጅቱ ወቅታዊ አመራሮች ይህን ድርጅታዊ ጉባኤ የማካሄድ ሁኔታ በተመለከተ ቃላት አልተነፈሱም፡፡ ምርጫ ቦርድም እንደዚያው፡፡ አባላትና ደጋፊዎቹ እንዲሁም የአብንን ጠንክሮ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ መቀጠል ያለውን ፋይዳ የሚረዱ ሁሉ የጉባኤውን መካሄድ በጉጉት እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡

ያ ሚሊየኖችን ዳር እስከዳር ማነሳሳት የቻለ ፥ በአጭር ጊዜ አስደማሚ ስኬት ያስመዘገበውና ሚሊየኖች ተስፋ የሰነቁበት አብን እስካሁን ድርጅታዊ ተሀድሶም ሆነ ጉባኤ ማካሄድ አልቻለም፡፡ ከእለት ወደእለትም ከህመሙ ለመፈወስ የሚያስችል መድሀኒት የሚሠጠው አሰታማሚ ወዳጅ ዘመድ አጥቶ ወደሞት አፋፍ እየወረደ ማጣጣሩን ቀጥሏል!

እርግጥ ነው! የአብንን ስኬት ሁላችንም እንደተጋራነው ሁሉ ለአብን ውድቀትም መጠኑና ድግሪው ብሎም አይነቱ ቢለያይም ከደጋፊና አባላት ጀምሮ (እንደገለልተኛ ተቋም ቦርዱም ሳይቀር) እስከ ላይኛው የታሪክ አደራ ተረካቢው አመራር ድረስ ያለነው ሁላችንም የየድርሻችንን መጋራታችን አይቀሬ ነው፡፡

ሆኖም ግን በዋናነትና በከፍተኛ ደረጃ የአማራን ህዝብ ትግል የማጠናከርና ተቋሙንም በሂደት እየጠነከረ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር የትግል ቤት እንዲያደርጉ አደራ የተረከቡ ከፍተኛ አመራሮቹ በታሪክ ፣ በህዝቡና በህሊና ፍርድ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ እሙን ነው፡፡

አዎ! አብን ህይወት ዘርተው እንደተቋም ባቆሙት የአማራው ልጆች ፥ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት  በማጣጣር ላይ ይገኛል!

Filed in: Amharic