>
5:33 pm - Wednesday December 5, 4542

ስንት ሰው ሲሞት ነው ድምጻችሁን የምታሰሙት ...?  (መ/ር ታሪኩ አበራ)

ስንት ሰው ሲሞት ነው ድምጻችሁን የምታሰሙት …? 

መ/ር ታሪኩ አበራ 


“ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን።” ምሳ 24፥11

† ይድረስ ለኦርቶዶክስ ሰባክያን †

ላለፋት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ  እጅግ ለአዕምሮ የሚከብድ  ከፍተኛ እልቂት፣ደም መፋሰስ እና መፈናቀል ሲፈጸም እንደቆየና አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ  ሁላችን የምናየው የአደባባይ ምሥጢር ነው።በዋነኝነት የጥቃቱ ዒላማ ሆነው ከፍተኛ ሰቆቃና ዘግናኝ እልቂት እየተፈጸመባቸው ያሉት ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው።ምንም እንኳ ብሔር ተኮር ጥቃት ተፈጸመ እየተባለ በመንግሥት ሚዲያ  ለጥቃቱ የዳቦ ስም ቢሰጠውም የጥቃቱ ዋና ዓላማ ኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳውያን ናቸው።አብዛኞቹ ጥቃቶች ደግሞ  በመንግሥታዊ መዋቅር ሁሉ የታገዙ ናቸው።

እጅግ የሚያሳዝነው ግን የኦርቶዶክስ ሰባክያን ይህንን ዘግናኝ ኢሰብአዊ ድርጊት በዓይናቸው እያዩና በጆሯቸው እየሰሙ  አጥብቀው ሲቃወሙ፣ ሲያወግዙ፣ለግፉዐን ድምጽ ሆነው ፍትሕ ሲጠይቁ  አይታዩም።

መጽሐፍ ቅዱስን ከብሉይ ኪዳን መጀመሪያ እስከ አዲስ ኪዳን መደምደሚያ ድረስ ስንመለከተው በዘመናት መካከል ሁሉ እግዚአብሔር  የጠራቸው አገልጋዮች ለተበደሉ ሰዎች ሲሟገቱ፣ለተገፉ ሰዎች ፍትሕ ሲጠይቁ፣አማጸኞችና ደም አፍሳሾችን ሳይፈሩና ሳያፍሩ ፊትለፊት በመጋፈጥ ሲገስጹ እንደነበረ ነው።የዛሬ ሰባክያን ነን ባዮች ግን ለስሙ መጽሐፍ ቅዱስን ተሸክመው እየዋሉ ክርስቲያኖች በየቦታው እንደ ከብት ሲታረዱ፣ድማቸው ከምድር አፈር ጋር በግፍ ሲቀላቀል እያዩ ድምጻቸውን አያሰሙም፣አብያተ ክርስቲያናት እንደ ችቦ ሲነዱ እያዩና እየሰሙ ለምን ብለው አይሞግቱም፣በኦርቶዶክሳዊነታቸው ምክንያት ብዙዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ከሥራ ገበታቸው ሲታገዱ፣ከመኖሪያ ቤታቸው ተወርውረው ሜዳ ላይ ሲጣሉ እየተመለከቱ  ይህ ፍጹም አውሬነት ነው ብለው በቃለ እግዚአብሔር ሲገስጹና መንግሥትን ሲቃወሙ አይታዩም።

አብዛኛው ሰባክያን ለሆዳቸው ያደሩ ስግብግቦች፣ርካሽ ዝናን ናፋቂ አስመሳዮች፣ለክርስቶስ ወንጌል ሳይሆን ድቃቂ ሳንቲም ለመለቃቀም የሚሯሯጡ ነጋዴዎች  ስለሆኑ ስንፍናቸውን ለመሸፈን እኛ ወንጌል ሰባኪነን እንጂ ፓለቲካኛ አይደለንም እያሉ በዘቀጠ አዕምሯቸው አሳፋሪ ንግግራቸውን ሲነዙ ይታያሉ።ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ አገልጋዮች ብቻ አልፈው አልፈው ድምጻቸውን ያሰማሉ።

ለመሆኑ ስለ ሰዎች  ሰብአዊ መብትና ክብር መጮኽ ምኑ ላይ ነው ፓለቲካ መባሉ? ነቢዩ ኤልያስ የደሃው የናቡቴን ደም  በግፍ ያፈሰሱትን አክአብና ኤልዛቤትን ሲቃወም የነበረው ፓለቲከኛ ስለሆነ ነው? አይደለም እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለሆነ ነው ።የዛሬ ሰባክያን ግን አስመሳይ ነጋዴዎች ስለሆኑ ሕዝቡን የሚፈልጉት ሸቀጣቸውን ሊያራግፋበት፣በየክልሉ ለአገልግሎት እየጋበዙ ኪሱን  እንዲሞሉለት፣ በሥጋዊ ቅንጦት እንዲንከባከቡት ስለሚፈልግ ብቻ ነው።

የእግዚአብሔር ቃል ግን እንዲህ ይላል ፦

“ፍርድን፡ፈልጉ፥የተገፋውን፡አድኑ፥ለድኻ፡አደጉ፡ፍረዱለት፡ስለ፡መበለቲቱም፡ተሟገቱ።” ኢሳ 1፥17

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተሰግስገው ስለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መከራና ስቃይ መንግሥትን ፊትለፊት ወጥተው መቃወም አሸማቋቸው ለመንግሥት ለማጨብጨብ ግን በየሚዲያው እንደ ከብት ሲጋፋ የሚውሉት ወራዳ ሰባክያን ደግሞ እጅግ አሳፋሪዎች ናቸው።በዘር ከረጢት ውስጥ ተቋጥረው ለክርስቶስ መለየት ያቃታቸው የአዕምሮ ልምሾዎች ናቸው።

አንዳንድ ሰባክያን ደግሞ  አውሮፓና አሜሪካ በነጻነት ሃገር ተቀምጠው ለሕዝበ ክርስቲያን ድምጽ መሆን አቅቷቸው በየስርቻው ተሸጉጠው ወገቧን እንደ ተመታች ድመት ሲሽመደመዱ የሚውሉ ማፈሪያዎች ደግሞ አሉ እነዚህ ደግሞ ሐሞታቸው የፈሰሰ፣የእግዚአብሔር መንፈስ የራቃቸው ማፈሪያ ምናምንቴዎች ናቸው።የወገናቸው ስቃይና ሞት የማይሰማቸው በድኖች።

አብርሃም አምስቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞርን ፊትለፊት ወጥቶ ሲዋጋና ሲቃወም የነበረው ፓለቲከኛ ስለሆነ ሳይሆን የድሆች መከራ የሚሰማው አባት ስለነበረ ነው፣ዮፍታሔ ልጁን ለመስዋዕት ለማቅረብ እስከ መሳል የደረሰው ለተገፋ ሰዎች ፊትለፊት ወጥቶ ለመታገል የቆረጠ የእግዚአብሔር ሰው ስለሆነ ነው፣ጌዴዎን ለወገኖቹ በኃይልና በድፍረት የታገለው የድሆች ደም እረፍት ስለነሳው ነው፣ሙሴ ፈርዖንን ፊትለፊት ሲገስጽ የነበረው የእስራኤላውያን ስቃይና መከራ ልቡን ስላደከመው ነው።የዛሬ አስመሳይ ሰባክያንና አባቶች ግን  ስለእነዚህ ቀደምት አባቶች በየመድረኩ እንደ ቁራ ስትጮኹ ትውላላቹ እንደነዚህ አባቶች ግን በየቦታው ደሙ ስለሚፈሰው ምስኪን ሕዝብ አንድም ቀን በድፍረት ቆማቹ ግፈኛውን መንግሥት ስትቃወሙ አትታዩም።ስማችሁን ወይም ግብራችሁን ለውጡ።ወንጌልን ለሥጋዊ ጥቅም መሸቃቀጫ አታድርጉ፣ትውልድና ታሪክ ሁሌም ሲወቅሳችሁ ይኖራል።

Filed in: Amharic