>

የምጸት አዙሪት፤ እያነቡ እስክስታ - መሪና ተመሪ...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የምጸት አዙሪት፤ እያነቡ እስክስታ – መሪና ተመሪ…!

ያሬድ ሀይለማርያም


ቀዳማዊ ጏይለስላሴ ከሚወቀሱባቸው በርካታ ነገሮች አንዱ ከስልጣን መውረጃቸው ጥቂት ጊዜ በፊት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ድርቀ ያስከተለውን እረሀብ ሸሽገው የያዙበት መንገድ ነበር። ያም አልበቃ ብሎ ቤተመንግስቱ አካባቢና ሹማምንቱ ዙሪያ የነበረው የኑሮ ምቾት የተትረፈረፈበት ህይወት እና ቁራሽ ዳቦ በማጣት የሚሞተው ሰው ህይወት የቀሰቀሰው የፓለቲካ ቁጣ ሌሎች የብሶት ጥያቄዎችን አስከትሎ ስለመጣ እሳቸውን እግፈኞች እጅ ጣላቸው። ሽኝታቸውም በግፍ እና  በተዋረደ መንገድ እንዲሆን ምክንያት ሆነ። ይህ የመሪዎች ቅብጠትና የሕዝብ ሰቆቃ ምጸት ብሔራዊ በሽታ ሆኖ አሥርት አመታትን አስቆጠረ። የ1977ቱ ድርቅ አገሪቱን የከፋ ችግር ውስጥ ከቶ የአለም መወያያ በሆነበትና በወሎ ብዙ ሕዝብ በርሃብ እየረገፈ በነበረበት ወቅት ደርግ የ10ኛውን የአብዬት በዓል ብዙ ሚልዬን በጅቶ ያከብር ነበር። ደርግም ከሱ የባሱ ግፈኞች እጅ ወደቀ። ወያኔዎቹም ትላንት በውድ ውስኪ ሲራጩና ጮማ ሲቆርጡ፣ በዘረፉት ገንዘብ መዋኛ ያለው ቪላና ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሲገነቡ አገር በርሃብ፣ በስደትና በጭንቅ ቆየች። ያኔ ሲዘርፉና ውስኪ ሲራጩ  ትዝ ያላላቸውን የትግራይን ሕዝብ የምቾት ምንጭ የሆነው የሥልጣን ወንበራቸው ሲነቀነቅ ግን ሄደው እጉያው ስር ተወትፈው በለኮሱት እሳት አስፈጁት። ዛሬ ትግራይ ውስጥ የወረደው መከራ ሁሉ የወያኔ የግፍ መገለጫ ነው። በምድር ወያኔን የሚስተካከል ግፈኛና በወንጀል የተጨማለቀ ቡድን ያለ አይመስለኝም።

ይህ የመሪዎች መሞላቀቅ እና የሕዝብ ሰቆቃ የምጸት አዙሪት ዛሬም አለቀቀንም። ዛሬም ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በዚሁ አዙሪት ሲሽከረከሩና ተመሳሳይ ስህተት ሲደግሙ ሳይ ከአንዱ ውድቀት ሌላው ለምን እንደማይማር ይገርመኝ ጀመር። አዲስ አበባ በብዙ ሚሊዮን በሚገመት የመንግስት ድግሶች ስትምነሸነሽ ብዙ ሚሊዬኖች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ድረሱልን ይላሉ። በዚህ ሳምንት እንኳ ጠቅላይ ሚንስትሩ አገር በጭንቅ በተያዘችበት፣ ከፊሉ የአገር ሕዝብ በርሃብ፣ በህክምና እጦት እና የአየር መዛባት ባስከተለው ድርቅ በሚሰቃይበት በዚህ ወቅት እሳቸው በአዳዲስ ጎጆ ወጪ ሙሽሮች ተከበው አደባባይ ምረቃ በአይነቱ ለየት ያለ ኬክ ሲቆርሱና ፖርክ ሲመርቁ ማየት የአገሬን የቀጠለ የመሪና የተመሪ ምጸት ያሳየኛል። ጠቅላዩ በዚህ ምስል የሚታየውን ኬክ ሲቆርሱ የተባበሩት መንግስታት ኢትዬጲያ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ አስከፊ ድርቅ መመታቷን እና ሚሊዬኖች በጠኔ  የከፋ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን በዚህ መልክ ዘግቦታል።

“For a country with a long and devastating relationship with dry weather, it’s hard to conceive of the current crisis as being different to others. But as the UN recently reported, drought conditions are now the worst for 40 years, with some communities calling it “the unseen”. ለጥቆም እንዲህ ይላል “more than 20 million people are estimated to be suffering under the drought with a million people in dire need of food assistance.”

አገሬ የመሪና ተመሪ የምጸት አዙትሽ  መቆሚያው የት ይሆን?

ለሹመኞች ልቦና ስጥልን!

የዛሬዎቹንና መጪዎቹን ከወደቁት የሚማሩ መሪዎች አድርግልን!

ኢትዬጲያ ባርክ፣ ሕዝብህን አድን!

https://www.climatechangenews.com/2022/10/27/drought-is-hitting-ethiopia-harder-than-ever/

Filed in: Amharic