“ነፃ !” የተባለው ጋዜጠኛ ተመስገን …!
ታሪኩ ደሳለኝ
ተመስገን ደሳለኝ ሲታሠርም ነፃ እንደሆነ አውቃለሁ። የታሰረውም ፍትህ ለማስከበረ ሳይሆን፤ የፖለቲካ ውሰኔ ለመሆኑ ከአስተሳሠሩ ጀምሮ እንደ አድር-ባይ ካድሬ አቋም ሲቀያየር የነበረውን የክሱን ሂደት የተከታተለ ሁሉ አብዝቶ የተረዳው እውነታ ነው።
ይህም ሆኖ፣ የፍርድ ሂደቱን በተመለከተ ችሎቱ ላይ ከሚከናወኑት ነገሮች ውጪ ላለፋት አምስት ወራት የራሴን ሃሳብ ሳልጨምር ሂደቱን ብቻ አስተላልፌለሁ።
ከአምስት ወራት በኋላ ጥቅምት 11/2015 የጋዜጠኛ ተመስገንን የፍርድ ሂደት ሲመለከት የቆየው ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች ችሎት ተመስገንን በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ በወ/መ/ስ/ስ/ቁ 141 መሠረት መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ እንዲሰናበት በመወሰኑ ሙሉ በሙሉ ነፃ ተብሏል። 3ኛውን ክስን በተመለከተ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 113(2) መሠረት በመለወጥ የጥላቻ ንግግርን እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 ላይ እንዲከላከል አዝዟል፡፡
አሁን ይከላከል በተባለበት አንቀጽ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ከገንዘብ ቅጣት ያለፈ የሚያሳስር አለመሆኑ በአንቀጹ ላይ በግልጽ ተቀምጧል።
በመጨረሻም፣ የዚህ ፍርድ ቤት ውሳኔ በብሔር መቀስ ተቆራርጠው ይንሻፈፉ ዘንድ የተፈረደባቸውም ሆኑ ኤዲት ለተዳረገ ክስ የተሰዉት የጋዜጠኛ ተመስገን እውነታዎች ወደ ክብራቸው ለመመለሳቸው በቸኛ ምስክር ሆኗል።
እደግመዋለሁ ጋዜጠኛው ወንድሜ፦ ከታሰረ ጀምሮ ይሰሙ የነበሩት እነዚያ አሳዛኝ ስሁት ፍረጃዎች፣ እነዚያ ከአውዱ የተገነጠሉ የፌስቡክ ውንጀላዎች፣ እነዚያ የተጻፈውን ጥለው ያልተጻፈውን ያንጠለጠሉ አደንቋሪ መዝሙሮች… ሙሉ በሙሉ የውሸት ክስ መሆናቸውን በይፋ ላረጋገጠው ፍርድ ቤት የአክብሮት ባርኔጣዬን አነሳለሁ።
አሁንም እደግመዋለሁ፦ ተመስገን ደሳለኝ እንዲከላከል የተወሰነው በእስር በማያስቀጣ አንቀጽ ነው። ወይም በቀላል አማርኛ፣ መከላከያን በተመለከተ ምንም አይነት ምስጢር አለማውጣቱንም ሆነ ሠራዊቱ ሥርአት አልበኛ እንዲሆን የሚያደርግ ጽሑፍ አለመጻፉን ፍርድ ቤቱ በማረጋገጡ የዐቃቢ ሕግ ክስ ውድቅ ሆኖ በነፃ እንዲሰናበት ተወስኗል።
መራራው ሀቅ ይኸው ነው።