>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1166

የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድ አኳያ ያላት ፖሊሲ በወፍ በረር ሲቃኝ ምን ይመስላል ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድ አኳያ ያላት ፖሊሲ በወፍ በረር ሲቃኝ ምን ይመስላል ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com

‹‹ በጦር ሜዳ ውስጥ ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ ወይም ሲሸሹ በወያኔ የጦር አዛዦች ሲረሸኑ ወይም ሲገደሉ በአይኔ ተመልክቼአለሁ ›› ( የወያኔ መሪዎች የፈጸሙትን ግፍ በአይኑ የተመለከተ አንድ ሰው የሰጠው ምስክርነት ቃል )

‹‹ ዓለም ሙሉ ትኩረቱን ለዩክሬን በሰጠበት በዚህ ግዜ በኢትዮጵያ የዘር ፍጅት ወንጀል እየተፈጸመ ነው ፡፡ ›› ( ዋሽንግተን ፖስት )

‹‹ የኢትዮጵያ እድል ወይም እጣ ፈንታ የሚወሰነው በመንግስት ስልጣን ውስጥ በተሸሸጉና ከመንግስት ስልጣን እርከን ውጭ በሚገኙ  አክራሪ ጎሰኞች፣ ፋሺስት ጎሰኞች፣ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች እጅ ስር ነው፡፡ ›› ( ግርማ ብርሃኑ ዘሃበሻ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ እንደጻፉት )

‹‹ ዶክተር አቢይ ከአለም  የሚፈልጉትን እገዛ ማግኘት አለመቻላቸውን ለመረዳት ከፈለጉ ፣ የራሳቸውን ድርጊት ብቻ መመርመር ይገባቸዋል፡፡ ›› ( ሚካኤል ሩቢን (Michael Rubin ) ( የአሜሪካ ስራ ፈጠራ ተቋም )

‹‹ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2019 አካባቢ በትግራይ ወያኔ የበላይነት ይመራ የነበረው መንግስት ከወደቀ በኋላ ዶክተር ሌላ የፖለቲካ መሳሪያ ( በአሮጌ የወይን ጠጅ ጠርሙስ አዲስ የወይን ጠጅ እንዲሉ፣ብልጽግና የሚል ስያሜ የተሰጠው ፓርቲ ) መስርተዋል፡፡ በዚህ አዲስ ስያሜ በተሰጠው ፓርቲ ውስጥ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት አባል ለመሆን ፍላጎት ባለማሳደሩ አባል አይደለም፡፡ ›› ( ጆን ሊ አንደርሰን (Jon Lee Anderson )

‹‹ ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ከጎሳ አክራሪነት ወይም ከከረረ የጎሳ ልዩነት፣ ኢላማ የተደረጉ ሰዎች እንዳይገደሉባት፣ ከዝርፊያና ምልጃ የጸዳች ሀገር እንድትሆን፣ ከመጥፎ አገዛዝ እንድትገላገል፣ በህግ የበላይነት የሚመራ እውነተኛ ዲሞክራት መንግስት ለማንበር፣ ጠንካራ የዲሞክራቲክ ተቋማትን ለማቆም፣ ይረዳቸው ዘንድ ጉብዝና፣ ጥበብ፣ ሞራልና ስነምግባር እንዲያድርባቸው ጸሎቴን አድርሼ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በአሳዛኝ ሁኔታ የዚህ ውጤት ወይም ፍሬ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ወድቋል፡፡ ›› ( ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ቦርከና ድረገጽ ሰኔ 23 2022 ( እ.ኤ.አ. )

ውድ አንባቢዎች ሆይ ኢትዮጵያ የገጠማትን መዋቅራዊ ችግር፣መከራ፣ተቋማዊ ውድቀት እንድትመረምሩ ከወዲሁ አስታውሳለሁ፡፡ ውድ አንባብያን ምእራባውያን ለምንድን ነው ሳተላይት መንግስት በኢትዮጵያ ለማቆም የሚፈልጉት የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መመርመር ያለባችሁ ይመስለኛል፡፡ ለምንድን ነው የምእራብ ሀይሎች የኤርትራ ከባድ መሳሪያዎች፣ ታንኮች ወደ የዒትዮጵያ ደንበር መጠጋታቸውን በየግዜው አጉልተው የሚያሳዩን ይህ ኤርትራ በሰሜኑ ጦርነት ተሳታፊ መሆናቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነውን  ይህን ጥያቄ ያነሳሁት ምእራባውያን እጅግ በሰፋ ሁኔታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባታቸው ነው፡፡ ይህ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝና የኢምፔሪያሊስትን ባህሪ የሚያሳየን ነው፡፡ ምእራባውያን ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ ቢኖራቸው ኖሮ በኢትዮጵያ ስር ሰዶ መከራ የሚያሳየንን የጎሳ ፖለቲካ ርእዮት ለመክላት የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ የኤርትራ ጦር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ወይም ጦርነት ላይ ለመካፈል የጦር መሳሪያ ማስጠጋቱን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል ማውጣታቸው ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም እንጂ ለኢትዮጵያ አስበው አይደለም፡፡ ምናልባትም ለእነርሱ ወዳጅ ለሚሉት ወያኔ መረጃ ለመስጠት ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ነው በእኔ የግል አስተያየት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ማናቸውም የውጭ ሀይል (ኤርትራንም ይጨምራል ) ለኢትዮጵያ የሚበጃት ነው ብዬ የማስብ ተላላ ሰው አይደለሁም፡፡

በነገራችን ላይ ምእራባውያን ሳተላይት በመጠቀም የማይፈልጉት ሀይል የጦር መሳሪያ ክምችትና የጦር ሀይል የት እንደሚገኝ ለሚፈልጉት ( ለሚደግፉት) ሀይል ማሳየት ልማዳቸው ነው፡፡ ምእራባውያን በብዙ የአፍሪካ ሀገራትና ሌሎች ደካማ የአለም ሀገራት ውስጥ በሳተላይት ምስል በደገፍ የማይፈልጓቸው  መንግስታትን ለተቋሚዎቻቸው እንዲጋለጡ ወይም እንዲጠቁ መረጃ መስጠት ከጀመሩ አመታት ነጉደዋል፡፡ ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. አገዛዝ የነበረው የወታደራዊው መንግስት የጦር ሀይል የሳተላይት መረጃ በግዜው የተገንጣይ ሀይሎች ለነበሩት ወያኔና ሻቢያ ይደርስ እንደነበር በአንዳንድ የጥናት ውጤቶቻቸው ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የምእራቡ ሀይል እንደ ሩሲያና ዩክሬን የመሳሰሉትን ሀገራት አይዳፈርም፡፡ የሩሲያና ዩክሬን ታንኮች፣ እና ሮኬቶች የት እንደሚገኙ የሚያደሳዩ የሳተላይት ምስሎችን ይፋ አያደርጉም፡፡ በኢትዮጵያ አኳያም ( በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ) የወያኔ ወታደራዊ ሀይል እና የጦር መሳሪያ ክምችት የት እንደሚገኝ የሳተላይት ምስል አያሳዩም፡፡ በሌላ አነጋገር ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለሚያስጠብቅላቸው ሀገራት ወይም የተቃዋሚ ሀይል ያደላሉ፣ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ እንደ ሩሲያ የመሰሉ ሃያል ሀገራትን ደግሞ ያከብራሉ፡፡ አይዳፈሩም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወያኔን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መደገፍ በኢትዮጵያ ፕሮክሲ ጦርነት እንዲከሰት ደጋፊ መሆናቸውን ነው፡፡

ምእራባውያን በሚያሰሙት ንግግር የተሸነፉ ይመስለኛል

 

ውድ አንባብያን ብዙ ያልተነገረላቸውን ታሪኮች በተመለከተ ተስፋ እንዳይቆርጡ አስታውሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን የጎሳ አጥር ሳይገድባቸው፣ የእምነትና መደብ ልዩነትን በማለፍ ለዘመናት አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደግ፣ መልካም፣ እርስበርሱ የሚደጋገፍ ከመሆኑ ባሻግር አብረው ተስማምተው፣ ተከባብረው ህይወታቸውን እየመሩ ለዘመናት ቆይተዋል፡፡  እኔ እራሴ ቋሚ ምስክር ነኝ፡፡በኢትዮጵያ ምድር ሌባ በመንገድ ላይ ያገኘውን ሞባይል ሊነጥቅ ይችላል፡፡ የተደራጁ ሌቦችም አልፎ አልፎ የግለሰቦችን ንብረት ሊዘርፉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በናይሮቢ፣ አቡጃ እና ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ እንደሚከሰተው የዝርፊያ አይነት በኢትዮጵያ ምድር የለም፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ግን በተጠቀሱት ከተሞች የሚካሄደው አይን ያወጣ ዝርፊያ አይነት ላለመከሰቱ ማስረጃ ማቅረብ አይቻለንም ወይም ለወደፊቱ ያሰጋናል፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ጥንታዊነት እና ስልጣኔ የበቀለባት ሀገር መሆኗ፣ የሃይማኖት እና ሞራል ልጓም በአብዝሃው ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ የሰረጸበት በመሆኑ ምክንያት በኢትዮጵያ ምድር የሩዋንዳውን አይነት የዘር ፍጅት በከፍተኛ ደረጃ አልተፈጸመም፡፡ ይህም ማለት ግን ከእብድ ውሻ የከፉ አረመኔዎች ሰውን በመቱ አልፈጁትም ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከፍተኛ ወንጀሎች ተፈጽመዋል ሰዎች በማንነታው ምክንያት በክፉዎች ጥይት ወድቀዋል፡፡ ከሩዋንዳው ጋር ልዩነቱ የቁጥር ብቻ ነው፡፡ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ኢትዮጵያውያን ፈሪሃ እግዛብሔር ያደረባቸው ሰዎች በመሆናቸው የሩዋንዳው አይነት ከፍተኛ የዘር ፍጅት አልተፈጸመም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የተለያዩ ስያሜዎች ያላቸው ታጣቂ ቡድኖች ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያ ፈጸሙ እንጂ አንደኛው ኢትዮጵያዊ ሌላውን ኢትዮጵያዊ በማንነቱ ያጠቃበት ግዜ ውስን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አርስበርሱ ጎራ ለይቶ ቢፋለም ኖሮ የምንወዳት ሀገራችን ላትኖር ትችል ነበር፡፡ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ለሁላችንም የጋራ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ባትኖር ኖሮ ጫማ ጠራጊዎች፣ ገበሬዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ገንዘብ በማዋጣት የታላቁን የአባይ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ገንዘብ አያዋጡም ነበር፡፡ በአለም ላይ ዝናን ያተረፈው፣ በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ የፊትአውራሪነት ስፍራ የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳይቀር ህልውናው የተመሰረተው በኢትዮጵያ መኖር ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌለች አየር መንገዱም የለም፡፡

እነኚህን ሁለት ምሳሌዎች ያነሳሁት የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም የማይፈነቀል ድንጋይ አለመኖሩን ለመጠቆም ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞቸ፣ የምእራባውያን የዜና አውታች፣ ምሁራን ( ሁሉም አይደሉም )፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ ውሳኔ ሰጭዎች፣ መንግስታት፣ በብይነ መንግስታቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ክፍሎች ብዙውን ግዜ ከኢትዮጵያ አንድነት ተጻራሪ የሆነ አቋም ሲያራምዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአጭሩ የተከፋፈለችና የተዳከመች ኢትዮጵያን ማየት የዘውትር ህልምና ተግባራቸው ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2020 በወያኔ ምክንያት የተቀሰቀሰው የርስበርስ ጦርነት ( እስከአሁን ድረስ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የርሰበርስ ጦርነቱን የጀመረው የወያ ቡድን ነው) ተከትሎ ኢትዮጵያ ብዙ መልክ ባላቸው ችግሮች ተዘፍቃለች፡፡ ሰብዓዊ መብት ጥሰቱም ተባብሶ ቀጥሏል ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ አክተሮች ቁጥርና መሰረታቸው ወይም አይነታቸው ብዙ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች በአንድ ጎራ ብቻ ውስጥ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል በትግራይ ያለው ታጣቂ ቡድን የትግራይ ተወላጆችን  ብዙ ግዜ በሰብዓዊ ጋሻነት ይጠቀምባቸዋል፡፡ በወለጋ ምድር ለዘመናት በኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ በማንነታቸው ላያ ያተኮሩ ግድያዎች የሚፈጽሙ ቡድኖች ስም እንዲሁ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህ ከባድ ስህተት ነው፡፡ ለአፍሪካ መልካም አርዓያ ያልሆነ አደገኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች የተለያዩ አካላቶች መሆናቸው ቢታወቅም የምእራቡ አለም ግን በአብዛኛው መውቀስ የሚፈልገው የኢትዮጵያንና ኤርትራ መንግስታትን ነው፡፡ የትግራይ ሀይሎች የፈጸሙትን ወንጀል ሁሉ ማንሳት አይፈልግሙ፡፡ ካነሱም አገም ጠቀም በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚበጃት አይደለም፡፡ በጸሃፊው አስተያየት በኢትዮጵያ ምድር ( ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምእራብ እስከ ምስራቅ ) ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂዎች ሁሉ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ወያኔን የመሰለ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ ድርጅት መሪዎችና ፈጻሚዎች በፍትህ አደባባይ መቆም አለባቸው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በወለጋም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም ትእዛዝ የሰጡ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ያልተከላከሉ የመንግስት አካላትም ቢሆኑ በፍትህ አደባባይ መቆም አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

በእኔ የግል ምርመራ መሰረት ወይም ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የዜና ዘገባዎች በቃረምኩት መሰረት በኢትዮጵያ ምድር የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች፣ የሰዎች ደህንነት፣ በህይወት የመኖር መብት፣ ያለምንም ስጋት ከአንዱ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ሌላኛው የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት፣ኢትዮጵያዊ ዜጎች ለዘመናት በሰፈሩበት አካባቢ የመኖር መብታቸው፣ መሰረታዊ የሲቪል መብቶች፣ የዜግነት መብት፣ አስተዳደራዊ አገልግሎቶች የማግኘት መብት ወዘተ ወዘተ እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡፡

አነኚህና ሌሎች የመንግስት ችግሮች የሚመነጩት ከስርዓቱ ነው፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መስከረም 26 2022  ጆን ሊ አንደርሰንስ (Jon Lee Anderson’s Op-ed ) የተባለ እውቅ የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ‹‹ የአለም ሰላም ኖቤል አሸናፊው ›› ኢትዮጵያን ወደ የርስበርስ ጦርነት ቋያ ሊወስዳት ይችላልን በሚል መጠይቅ ባቀረበው ዘለግ ያለ ጽሁፉ ላይ ‹‹ ኢትዮጵያ የገጠማትን ስርዓታዊና መዋቅራዊ ችግሮች ››( the systemic and structural hurdles Ethiopia faces )  አብራርቷል፡፡ ይህ ያፈጠጠ ችግር  ‹‹ በመኖሪያ ቤታችን የተቀመጠ ዝሆን ›› ቢሆንም አብዝሃው ( አብዛኛዎቹ) ኢትዮጵያዊ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበራት ወዘተ ወዘተ ኢትዮጵያ ለገጠማት ፈተና መፍትሔ ለማምጣት ወይም አገዛዙን ለመጠየቅ አልቻሉም፡፡ ( በጣም ጥቂቶች በአደባባይ በመውጣት ኢትዮጵያ ስለገጠማት የታሪክ ፈተና ተናግረዋል፡፡ መፍትሔ 

የሚሉትንም ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ ) በነገራችን ላይ በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር የተበተኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያን ሰንጎ ለያዛት የምጣኔ ሀብት ድቀት በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በህጋዊ መንገድ ገንዘብ በመላክ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት  የሚጥሩት ምን ያህሉ ናቸው ? እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡ 

እውቁ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለውጭ ምንዛሪ ክምችት የሚያደርጉት አበርክቶ ይህን ያህል ጮቤ የሚያስረግጥ አይደለም፡፡ በአጭሩ የቁጥራቸውን ብዛት ያህል ኢትዮጵያ ለገጠማት አሳሳቢ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሔ አላገኙላትም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ፕሮፌሰር አክሎግ እንደጻፉት ከሆነ  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት መሃከል ናይጄሪያ 19.2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ጋና 4.5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣ ኬንያ 3.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ሴኒጋል 2.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ዚምባብዌ 2.0 ቢሊዮን ዶላር በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቻቸው በህጋዊ መንገድ ከተለካ ገንዘብ የውጭ ምንዛሪያቸውን ክምችት ሊጨምሩ ችለዋል፡፡ በነገራችን ላይ እነኚህ የተጠቀሱት አምስት ሀገራት ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት ሁሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቻቸው ሁሉ ለማግኘት የቻሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ በውጭ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ለዘመድ አዝማዶቹ ዶላር በሚልክበት ግዜ ( ሁሉንም ማለቴ አይደለም በጥቁር ገበያ ውስጥ እጃቸውን የዶሉትን ማለቴ ነው ) የኢትዮጵያ ሀገራችን ኢኮኖሚ እንዴት አፈር ድሜ እንደሚግጥ ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በህገወጥ የገንዘብ ልውውጥ ጥቂቶች ሰማየ ሰማያት ላይ ደረሱ ቢባልም በዚህ አይነት ዘዴ ያለፈላት ሀገር ወይም ህዝብ ያለ አይለስለኝም፡፡

የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ 

የጎሳ ፌዴራሊዝም ከኢትዮጵያ ህዝብ አኳያ ውድቀትን እንጂ እድገትን አላመጣም፡፡ ከዛሬ ሰላሳ አመት በፊት በስልጣን ኮርቻ ላይ ቁጢጥ ብለው የነበሩት እና ዛሬ ላይ መቀመጫቸውን በትግራይ ክልል ያደረጉት የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው ሲሉ ኢትዮጵያን በጎሳ ክልሎች ማጠራቸው በአደባባይ የሚታይ መራር እውነት ነው፡፡ ( ወይም ኢትዮጵያን ወደ ከፊል ራስ ገዝ ክልሎች መከፋፈላቸው ጎምዛዛ እውነት ነው) ፡፡ ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር አክሎግ አንድ ታላቅ የምእራቡ አለም ባለስልጣንን ጠቅሰው እንደጻፉት ‹‹ ለወደፊቱ በጎሳዎች መሃከል ችግር ሊፈጥር የሚችል ዘር ተዘራ ›› ነበር ያሉት፡፡ (“seed the future with ethnic problems,” ) የተለያዩ ክልሎችን መፍጠር ለሀገሪቱ ዜጎች ስጋትን እንጂ ደስታን አልተፈጠረም፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተወሰኑ ቡድኖች ወይም የጎሳ ተወካዮች ብቻ በበላይነት ስለተቆጣጠሩት ዴሞክራሲን ማንበር የሚቻል አይደለም፡፡ በየአካባቢው ውስጣዊ ድንበር እየተፈጠረ መምጣቱ፣ የኢኮኖሚ ሁኔታው ( ቀውሱ) አዙሮ የሚደፋ በመሆኑ፣ ሰዎች ባህላዊ ድንበራችን ተጥሷል እያሉ ማመናቸው፣ ብዙዎች ከስልጣን መገፋታቸው፣ ወይም ስልጣን በጥቂቶች ስር ብቻ መውደቁ፣ ወዘተ ወዘተ የሀገሪቱን መጻኢ እድል አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች ወይም ጦርነት ለንጹሃን ዜጎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑ፣ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ በጎሳ ታጣቂዎች መገደላቸው፣ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የሩዋንዳው ፕሬዜዳንት ፖል ካጋሚ እንዳሉት ‹‹ ብሔር ተኮር ፖለቲካ ለአፍሪካ መቃብሯን እንደገቷን አፋጥኖ አያውቅም ፡፡›› ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በሰከነ መንፈስ፣ በውይይት ቁጭ ብለን በመወያየት ከጎሳ ፌዴራሊዝም እንዴት መላቀቅ እንዳለብን እንወያይ፣ እንነጋገር፡፡

በህይወት የመኖር መብትና  ዛፍ መትከል

በእኔ የግል አስተያየት መሰረት በህይወት የመኖር መብት መጠበቅ ከማናቸውም ስራዎች በፊት መከበር አለብት ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ቀጣይነት ባለው የልማት እድገትም አምናለሁ፡፡ ስለሆነም 18 ቢሊዮን 

የባህር ዛፍ ችግኞችን መትከል ለዘለቄታዊ ልማት የሚበጅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ልማት የሰዎችን ሁለንተናዊ እድገት እና ህይወትን የሚያሻሽል፣ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ መሆን አለበት፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያዊ ዜጎችንና በኢትዮጵያ ምድር የሚኖሩትን ሁሉ ህይወት የሚያሻሽል መሆን አለበት፡፡ የአንድ መንግስት ዋነኛ ሃላፊነት በሚያስተዳድረው ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወትና ደህንነት መጠበቅ እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት የተሳካለት አይመስለኝም፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በትክክለኛው መንገድ ላይ እገኛለሁ ብሎ ያምናል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና በመንግስት ፖሊሲ፣ ፕሮግራምና አሰራር ላይ ክፍተት ይታያል፡፡ በሲውድን ኦስሎ በተዘጋጀው የኖቤል ደማቅ ስነስርዓት ሽልማት ላይ ቀርበው ‹‹ የዓለም ሎሬት የሰላም ሽልማት ›› የተቀበሉት ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ በአደረጉት ንግግር ‹‹ ሰላምን ከማግኘታችን በፊት የፍቅርን ዘር መዝራት አለብን፣ ይቅርታ ማድረግ፣ በሰዎች ልብ ውስጥና አይምሮ ውስጥ እርቅ መውረድ አለበት ›› ብለው ንግግር አሰምተው ነበር፡፡ ይህ ንግግራቸው አንድ የመጸሐፍ ቅዱስ ጥቅስን አስታወሰኝ፡፡ ይሄውም ‹‹ የዘራሐውን ታጭዳለህ የሚል ነው፡፡ ( You reap what you sow.” ) የጎሳ ግጭቶች እንዲስፋፉ ዋነኛው መግፍኤ ምክንያት የሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ስለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ጎሳን መሰረት ያደረገ የትምህርት ስረዓት ለነገ ሀገር ገንቢ ህጻናት የሚያስተምረው ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን ነው፡፡ ‹‹ የ100 አመት እድፍ… እያሉ ህጻናት እንዲዘምሩ ማድረግ ምን ማለት ነው ? ይህ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንቅልፍ ሊነሳቸው ይገባል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንክሮ እና በትኩረት መከታተል የሚገባን ቁምነገር ቢኖር የሀብት ክፍፍል ፍትሃዊነት ገቢራዊ ወይም ገቢራዊ ስላለመሆኑ ነው፡፡ በጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት የየጎሳው ኤሊቶችና የፖለቲካው ፊትአውራሪዎችና ተከታዮቻቸው፣ እንዲሁም ደጋፊ ነጋዴዎችና ጥቂቶች የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚና ሀብት ሰብሳቢዎች ሲሆኑ ብዙሃኑ ግን በድህነት የሚማቅቅ ይሆናል፡፡ ሌብነት፣ ጉቦ ወዘተ ወዘተ ይስፋፋል፡፡ በአጭሩ ለጥቂቶች ሲሳይ ለብዙሃኑ ገሃነብን ያመጣል፡፡

ኢትዮጵያ ወያኔ በተከለባት የጎሳ ፌዴራሊዝም መርዝ ምክንያት ክፉኛ እየደማች ስለመሆኑ ምስክሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ በወያኔ ዘመን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መዘረፉን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ተቋማት፤ባህልና ዜግነትን፣ ብሔራዊ አንድነትንም  ሸርሽሯል፡፡ በነገራችን ላይ ትላንትም ሆነ ዛሬ ሆን ተብሎ የሚከወን የጎሳ ፖለቲከኞች ሴራ ነው፡፡ ይህ የውስጥ ችግራችን እንዳለ ሆኖ እንደ አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገራት የሚያሳድሩብን ተጽእኖ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

የአሜሪካ መሪዎች እንደ የቅኝ ገዢዎች ( ወይም ኢምፔሪያል ) መሪ ( አለቃ ) ለመሆን ይቃጣቸዋል፡፡ እነርሱ እራሳቸውን የአለም መሪ ( በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን በተመለከተ አዛዥ ናዛዥ ነን ባዮች ናቸው፡፡ ) አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ፡፡ በታወቁ የመገናኛ ብዙሃናቸው አመሃኝነት እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ እያሰደሩ ነው የሚሉና የመሳሰሉትን የሀሰት ዜናዎችን ሳይቀር ያሰራጫሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቦና የተረዱ አልመሰለኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን አንድ የውጭ ሀገር መንግስት ጠብ ያለሽ በዳቦ በማለት በቀጥታ ኢትዮጵያውያንን ለመውረር ቢሞክር የኢትዮጵያውያን ምላሽ ምን እንደሆነ ለማወቅ የአድዋን ታሪክ ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ እነርሱ ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ አመታት ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ስለመሆኗ ማንሳት አይፈልጉም ወይም ሆን ብለው ትተውታል፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ሀገር ›› ስለመሆኗ መናገርም አይፈልጉም፡፡ (They ignore Ethiopia’s long and distinguished status as an independent country and as “the Motherland of Africa.” )

ኢትዮጵያ የድሆች ድሃ ሀገር ስለመሆኗ ምንም ክርክር የሚያስነሳ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ 

ከድህነት ለመውጣትና በእድገት ጎዳና ላይ ለመራመድ  የውጭ ሀገር ካፒታል ማግኘት አለባት፡፡ ይህ የውጭ ካፒታል የማግኘት የፖሊሲ ጥያቄ ምን ያህል ዋጋ ተከፍሎ ነው የሚገኘው ?፣ ለማን ጥቅም ተብሎ ነው የውጭ ካፒታል የሚጠየቀው ? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች የመለሰ መሆን አለበት፡፡ ሳማንታ ፓወርም (Samantha Power ) ሆኑ አንቶኒ ብሊንከን (Anthony Blinken ) ወይም ማይክ ሀመር ( Mike Hammer ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ወሳኝ አይደሉም፡፡ ወነኛው መሰረታዊ መርህ ሁለቱም ሀገራት መከባበር አለባቸው ፡፡ በሁለቱም ሀገራት መሃከል መተማመንን እና በራስ መተማመንን  የሚፈጥር የጋራ መከባበር አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያን አለማክበር ተስፋ ያስቆርጣታል፡፡ አሜሪካን ኢትዮጵያን የማታከብር ከሆነ የኢትዮጵያ መሪዎች የአሜሪካንን የሚሊታሪ እርዳተና ምጣኔ ሀብት እርዳታ ብቻ በማየት ወዳጅነት የሚፈጥሩ አይመስለኝም፡፡ በአጭሩ ፊት የነሳቻቸውን አሜሪካንን በመተው ወደ ሌሎች ወዳጅ ሀገራትን ፍለጋ በመሄድ ለአሜሪካ ጀርባቸውን ይሰጣሉ፡፡ አንድረሰን የተባለው በኒውዮርክር ጋዜጣ የሚሰራው አንድረሰን በቅርቡ በጻፈው ዘለግ ያለ ጽሁፍ ላይ ‹‹ የተባበረችው አሜሪካ ፓሬዜዴንት የሆኑት አዛውንተ ባይደን ከብስክሊሊት ላይ በወደቃቸው ምክንያት ማዘናቸውን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አውግተውኝ ነበር ብሏል ) በእኔ አስተያየት በእድሜአቸው ምክንያት ነው የወደቁት ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የቀድሞው የተባበሩት አሜሪካ ፕሬዜዴንት የነበሩት ኦባማ በአነቃቂ ንግግራቸው የታወቁ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዛኛውን ቃል የገቡትን ነገሮች አልፈጸሙም፡፡ ከፈጸሙት ተግባራት ያልፈጸሙት ይበዛል፡፡

እዚህ ላይ ለኢትዮጵያ መንግስት በተመሳሳይ መንገድ ያለችኝን አጭር መልእክት ሳቀርብ በታላቅ አክብሮት ይሆናል በጎሳ ማንነታቸው ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደው የርስበርስ ጦርነት ምክንያት ለተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሀዘኑን መግለጽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የሰው ህይወት ከመቀጠፉ ባሻግር በማህበራዊና ምጣኔ ሀብት ላይ የሚደርሰው ኪሳራ እንዲህ በቀላሉ የሚታወቅ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው ጦርነት በዋነኛነት  የኢትዮጵያን መንግስት የሚወቅሱት አንዳንድ የምእራብ ሀገራት ምሁራን አስተያየት እውነትነት የጎደለው ይመስለኛል፡፡ ከተባበረችው አሜሪካ ጋር በሚመሳሰል መልኩ የብይነ መንገስታቱ የሰብዓዊ መብት ካውንስል እና የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የሚያወጡት ሚዛኑን የሳተ ሪፖርትም ቢሆን ለአንዱ ወገን ያደላ መሆኑ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም ሆኑ ኤክስፐርቶቻቸው በሰብዓዊ መብቶች አለም አቀፍ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ቆመው የሀገሪቱን እውነተኛ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ስእሎችን ለአለም ይፋ ቢያደርጉ መልካም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቦታዎች ላይ የተፈጸመ ነው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ጥናታቸውን ቢያከናውኑ ከታሪክ እና ህሊና ተጠያቂነት ይድኑ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ እዚች ላይ አንባቢውን ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ሁሉ መጠየቅ አለባቸው የሚለው የግል አቋሜ መሆኑን ነው፡፡ አንደኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ ግለሰብ ወይም ቡድን፣ ወይም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም ያዘዘ ባለስልጣን ተጠይቆ ሌላው ለምን ? ዝም ይባላል የመልእክቴ ዋነኛ ትኩረት ነው፡፡ በወያኔ ቡድን አባላት በአፋር፣ አማራ የተለያዩ አከባቢዎች የተፈጸሙ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎች፣ የሲቪል ወገኖችን መግደል፣ ዝርፊያ ወዘተ ወዘተ በምእራባውያን የዜና አውታች፣ ምሀራኖቻቸውና መንግስቶቻቸው  በበቂ ሁኔታ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ እንደው ዝም ብለው ላይ ላዩን ብቻ ይናገራሉ፡፡ ለምን ህሊና የፈጠረባችሁ ጠይቁ፡፡ በምእራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ምድር በሚኖሩ የአማራ ማንነት ላይ የሚወርደው መአት በምራቡ አለም ከእነጭራሹ ተነስቶ አይታወቅም፡፡ ለምን ? እስቲ መልሱን በተመለከተ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡

 

እንደ መደምደሚያ

  1. ጦርነቱን ማን ነበር የጀመረው ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ፣ የጦር ወንጀልና አሸባሪነት ድርጊት ማን ነው የፈጸመው ለሚለውም መሰረታዊ ጥያቄ ከምእራባውያን አኳያ ግልጽ የሆነ መረዳት ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለተፈጸሙት ወንጀሎች ሁሉ ተጠያቂውን ለማምጣት ምእራባውያን በሰውነትና ህሊና ሚዛን ላይ መቀመጥ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
  2. የምእራብ ሀገራት አሰላሳዮች፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች መሪዎች፣ የፖሊሲ አውጭዎችና አሰፈጻዎች፣ አሰላሳዮችና ተመራማሪዎች ሀገሮቻቸው ገለልተኛ አቋም እንዲይዙ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ የአንድን ሀገር ህልውና መፈታተን የተገንጣይ ሀይሎችን መደገፍ ቢያንስ በታሪክ ያስጠይቃል
  3. እንደ አንድ የኢትዮጵያ አንድነት እንደሚያሳስበው ዜጋ፣ የወደፊት ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እንደሚያስጨንቀው፣ የማናቸውም ኢትዮጵያውያን ( የጎሳ፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ገደብ ሳይደረግ ) ሰብዓዊ መብቶች እና የሰው ደህንነት በኢትዮጵያ  እንዲከበሩ እንደሚጥር ሰው የሰሜኑ ጦርነት በፍጥነት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢኮኖሚያዋ በአፍጢሙ በተደፋባት ሀገር ጦርነት የሚደገፍ አይደለም፡፡ በፍጥነት እውነተኛ የሰላም ንግግር ሁሉንም የሚመለከታቸውን ኢትዮጵያውያን የሚወክሉ የመንግስት ሃላፊዎች ለንግግር መቀመጥ አለባቸው፡፡
  4. የኢትዮጵያ መንግስት የጦርነቱን መሰረታዊ ምክንያት ማጥናት አለበት
  5. የኢትዮጵያ መንግስት ሲቪሎችን የገደሉ ሀይሎች አባላትን ተጠያቂ ማድረግ አለበት
  6. አሁን ያለው ህገመንግስት የሚሻሻልበት የሰለጠነ መንገድ እንዲፈለግ የሚለው ሌላው የግል አስተያየቴ ነው
  7. በመጨረሻም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የተባበረችው አሜሪካ መንግስት፣የብይነ መንግስታቱ ጸጥታው ምክር ቤት፣ የብይነ መንግስታቱ ወኪሎች ለወያኔ በማዳላት በኢትዮጵያ ምድር እረዥም ግዜ የሚፈጅ ጦርነት እንዲደረግ ነዳጅ ማርከፍከፋችሁን ታቆሙ ዘንድ በመማጸን ልሰናበት፡፡

መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም.

Filed in: Amharic