>

የሰላም ድርድሩን አስመልክቶ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የተሰጠ መግለጫ:-

የሰላም ድርድሩን አስመልክቶ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የተሰጠ መግለጫ:-

“የአማራ ህዝብ ጥያቄ አማራን በጨቋኝነት በፈረጀዉ የህገ-መንግስት ማዕቀፍ አይፈታም” 

    የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) 

ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር

 

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) ላለፋት ሁለት ዓመታት በትግራይ ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በተደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት በሀገራችን የደረሰዉ ቁሳዊ እና ሰብአዊ ውድመት አሳዛኝ እና የሚያስቆጭ ክስተት መሆኑን ይረዳል።

በተለይም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት እድል ለሁለት ዓመታት ተዘግቶ ግብታዊነት እና ጀብደኝነት ባጠቃቸው ጥቂት ፖለቲከኞች ምክንያት ሀገሪቱ ውድ ዋጋ መክፈሏ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ እንገነዘባለን።

ከዚህ አኳያ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) ሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች (ብልፅግና እና ህወሃት) ለሁለት ዓመታት ከቆየ ጦርነት በኋላ የተኩስ አቁም እና የዘላቂ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን በበጎ ይመለከተዋል።

የሰላም ጥያቄ የአማራ ህዝብ ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን አደረጃጀታችን ሁለቱ የፖለቲካ ኃይሎች ወደዚህ የሰላም ማዕቀፍ እንዲመጡ ጥረት ላደረጉ ቀጠናዊ እና ዓለማቀፋዊ ተቋማትም ልዩ አክብሮት እና ምስጋና ያቀርባል።

ይሁን እንጅ አደረጃጀታችን በነቢብም ሆነ በገቢር በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው በአማራ ልጆች ተሳትፎ ብቻ መሆኑ እየታወቀ  የጦርነቱን የግፍ ፅዋ የተጋተው እና የስምምነቱ ውጤቶችም በቀጥታ የሚመለከቱት የአማራ ህዝብ በቀጥታ የድርድሩ ተሳታፊ የሚሆንበት መደላድል ሳይፈጠር በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገዉ ስምምነት መሠረታዊ ይዘት የአማራን ህዝብ ጥቅም እና መብት የሚያስከብር አመሆኑን ተረድተናል።

በተለይም ህወሃት እና ኦነግ ከ1983 ዓ.ም በፊት በኤርትራ ሰንዓፈ ያደረጉትን ስምምነት እና ህወሃት መዋቅራዊ ቅርፅ ያስያዘዉን “የአማራ ጨቋኝነት” ስሁት ትርክት መነሻ አድርጎ የተቀረፀውን የኢፌድሪ ህገ መንግስት የሚያፀና ስምምነት መደረጉ በእጅጉ አሳስቦናል።

በመግቢያው ላይ የአማራን ጭቆና ለመቀልበስ እንደተዘጋጀ ራሱን በሚገልፀው ህገ-መንግስት ማዕቀፍ የሚፈታ የአማራ ችግር  እንደሌለም በፅኑ እናምናለን።

የአማራ ህዝብን ጥያቄ በህገ መንግስቱ መሠረት እንፈታለን ማለትም ጥያቄዉን ከማወሳሰብ ያለፈ ውጤት እንደሌለው እንገነዘባለን።

ይልቁንም ይህንን ህገ-መንግስት ለማሻሻል በታገሉ እና መስዋዕትነት በከፈሉ በርካታ የአማራ ልጆች ተጋድሎ ላይ መቀለድ እንደሆነ እንረዳለን።

በመሆኑም:-

1/  መስዋዕትነት እየከፈልንለት ያለ ዓላማችን እንደመሆኑ መጠን የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የአማራ ህዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የሚኖረንን ሁለንተናዊ ሚና አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እያረጋገጥን ህዝቡም በቀጣይ በምናደርጋቸዉ የትግል ጥሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በቁርጠኝነት እንዲሳተፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

2/ ሕገ-መንግስት ማሻሻል፣ የማንነት እና የውክልና ጥያቄን ጨምሮ ቁልፍ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት ከህገ-መንግስት ማዕቀፍ ባሻገር (Extra-Constitutional Dialogue) መሆኑ ታውቆ  ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ሲባል የብልፅግና መንግስት ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አዲስ ስልት እንዲቀይስ እንጠይቃለን።

3/ የአማራ ህዝብ መብቱን ማስከበር እና ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነት ማግኘት የሚችለው ራሱን በሚገባ ሲያደራጅ ብቻ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንፃር ከእዚህ በፊት በተለያዩ የአማራ አደረጃጃቶች የምናውቃቸው ወንድሞቻችን ያነሱትን የድርድር ውክልና በተመለከተ በመርህ ደረጃ የምንደግፈው ሲሆን ህዝቡም በእነኝህ እና በሌሎች በአማራ ህዝብ ጉዳይ ላይ በሚሰሩ ጠንካራ አደረጃጀቶች ተሳትፎ እንዲያደርግ ለመላዉ የአማራ ህዝብ ጥሪ እናቀርባለን::

አዲስ ትውልድ! አዲስ አስተሳሰብ! አዲስ ተስፋ!

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ)

ባሕርዳር-ኢትዮጵያ

ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም

Filed in: Amharic