>

ድርድር እና አንዱዓለም አራጌ...! (ሀብታሙ ምናለ)

ድርድር እና አንዱዓለም አራጌ…!

ሀብታሙ ምናለ

“አንዱዓለም ስትታገለው በነበረው ሕወሓት መጠርጠርህ ስትሰማ ምን ተሰማህ? እንዴት ተቋቋምከው”

.         ጠያቂው እኔ (

እነ አንዱዓለም አራጌ በዋቢሸበሌ ባዘጋጁት የኢዜማ የውስጥ ምርጫ ቅስቀሳ መዝጊያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝቼ ያቀረብኩለት ጥያቄ ነው፡፡ አንዱአለም ጥያቄውን ሳቀርብለት አንገቱን እየነቀነቀ ማስታወሻው ላይ ማስፈር ጀመረ፡፡

ከጥያቄው በኋላ አስከተልኩና፡- “የአዲስ አበባ ሕዝብ ከምርጫ 97 በኋላ በፖለቲካው የሰራው ትልቅ ውለታ እና ጀብድ ኢዜማን አምኖ አለመምረጡ ነው” – ፊቱ በሐዘን ሲዳምንም ይታየኛል፡፡ ምክንያቴን ሳስረዳው ባይረዳኝም ተረዳኝ፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም በእዚህ አቋሜ እንደጸናሁ ነኝ፡፡

አንዱአለም፣ ምላሽ ሲሰጥ ያለፈ ትህትና ስለሚያበዛ በጣም ከሚበሽቁበት መሀከል ነኝ፡፡ የእሱን ትህትናን መንቀፌ አይደለም፡፡ የእሱ ግን ትህትና የሃይማኖት አባቶችን ሁሉ የሚበልጥ ይመስለኛል፡፡ ለሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጠ በኋላ “ቤተሰቤ እኔ በአፍቃሪ ሕወሓትነት መጠርጠሬን ሲሰሙ በጣም አዝነዋል፤ አምርረህ የታገልከው፣  ያሰረህ ሕወሓት የዚህን ያህል አልጠላህም፣ ደግሞም አልበደለህም፤ የትግል አጋሮቼ የምትላቸው በዚህ ልክ ስምህን ማጥፋታቸው ያሳዝናል” ብለውኛል፡፡ ስሜቱ በጣም ይጎዳል አለ፡፡

“አንዱአለም ፈርቶ ፈረጠጠ፣አፍቃሪ ሕወሓት ነው” የምትል አጀንዳ የተከፈተችበት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተናጥል የተኩስ ስምምነት አድርጌያለሁ ብሎ ትግራይን ለቆ ሲወጣ፤ “በኋላቀርና አውዳሚ የጦርነት ዳፋ ተያያዝን እንጥፋ ወይንስ መፍትሄ እንሻ?” በማለት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ያቀረበውን ጽሁፍን መነሻ በማድረግ ነው፡፡

ይሄ ሁሉ እልቂት እንዳይከሰት ድርድር መደረግ ይገባል ብሎ ሃሳብ ቢያቀርብም ሰሚ ባለማግኘቱ ተፈጻሚ ሳይሆን የነበረው ሁሉ እንዳይሆን ሆነ፡፡ በመነሻ ጹሁፉ ለድርድሩ “በማዕከላዊ መንግሥትም ሆነ በሕወሓት በኩል ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉ ሀገሮች ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን ናቸው፤ ከሁሉም ጀርመን የተሻለ ጥንካሬዋን ጠብቃ ማደራደር ትችላለች፤ ደቡብ አፍሪካም የተሻለች አደራዳሪ ልትሆን ትችላለች፡፡ ከሀገሮች ይልቅ ተሰሚነት ያላቸውን ግለሰብ አደራዳሪዎች መፈለጉ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ፖል ካጋሜ ጥሩ ምርጫ ሊሆኑ ይችላሉ” ብሎ ቀድሞ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ በኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ በኩል በድምፅ ብልጫ ውድቅ በመደረጉ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ አንዱአለም ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ በደንብ ታይቶ ተተግበሮ ቢሆን የተሻለ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

“ትናንት የራሳቸው አቋም ኖሯቸው የማያውቀው ሰዎች “ብልፅግና በጦርነት ይፈታል!” ሲል አብረው፣ ፉከራና ሽለላውን ሲያቀልጡት ነበር፣ ዛሬም እንደ ሌላው ቀን ብልፅግና የሚለውን ሁሉ መልሰው ለማስተጋባት በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡

በእንዲህ አይነት ልምሻ የተመቱ አቋም የለሾች የተነሳ የኢትዮጵያ እናቶች የከፈሉትን የሰቆቃ ጥልቀት ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። ሀገራችን የወደቀችበትን ጥልቀትም አብረን እያየነው ነው፡፡ “ቀድመን አደጋውን እንከላከል፣ ከብዙ እልቂትና ውድመት በኋላም ቢሆን ችግሩ የሚፈታው በሰላም ነው፣ ቀድመን ሕይወትን እንታደግሞ፣ ውድመትን እንከላከል፣ ጥላቻንም እንቀንስ ሲባሉ ያለ ስም ስም ይለጥፋሉ፣ የብልፅግና ዙፋን ጠባቂዎች ሃሳቡ ከብልፅግና ካልመጣ  አንዱአለም ላይ እንደተደረገው ተቧድነው ይዘምታሉ፡፡ ዛሬ ደግሞ ትላንት ያወገዙትን ሃሳብ ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ እያወደሱ ይገኛሉ። እንዲህ አይነት ሰዎች በደርግም፣ በሕወሓትም ጊዜ ነበሩ በዘመናችን የተነሱት ኮርቻቸውን አሳምረው ጀርባቸውንም አጥፈው ለመጋለብ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።

Filed in: Amharic