>

የአርሲው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ወደ ለየለት የዘር ጦርነት ሊያመራ ይችላል...!

የአርሲው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ወደ ለየለት የዘር ጦርነት ሊያመራ ይችላል…!

 ግርማ ካሳ

የኦነግ ታጣቂዎች በነቀምቴ መግባታቸውን ተከትሎ፣ “የነቀምቴው ውጊያ  ይቆያል የሚል ግመት የለኝም፡፡  መከላከያ ወደዚያ ተሰማርቶ ከተማዋን ያፀዳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡  ኦነጎች ሃይል ሲመጣ የሚሸሹ ናቸው” ብዬ ነበር፡፡ እንዳልኩት ፣ ያው በቂ ጥበቃ እንደሌላ ስለተነገራቸው የመጡ እንደመሆኑ፣  ባንክ ዘርፈው፣ ከእስር ቤት እስረኞችን አስፈትተው ሌሎች ጥፋቶች ከመፈጸማቸው በፊት መከላከያ እየመጣ እንደሆነ ሲያውቁ ሸሽተው ሄደዋል፡፡

ይህ በወለጋ ነው፡፡ በምስራቁ የአገሪቷ ክፍል በአርሲ ሌላ የኦነግ አንጃ የሽብር ተግባራት ፈጽሟል፡፡ በአርሲ ዞን፣  ጀጁ ወረዳ፣  የ6 ወር ህፃንን ጨምሮ 9 የአማራ ተወላጆች በኦነግ ታጣቂ ቡድን በግፍ ተገድለዋል:: በዚህ ጥቃትም የ8 ወር ህፃን ልጅን ጨምሮ 9 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቡድኑ ምሽቱን ሙሉ በአካባቢው ጥቃት ሲፈፅም አምሽቷል። ይሄ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ መንግስት አለ በተባለበት አገር ነው፡፡ እነ ዶር አብይ አህመድም ሆነ አቶ ሺመልስ አብዲሳ ሁሉ ነገር ሃሪፍ ነው ብለው ነጋ ጠባ የስንዴ ማሳ በማየት ጊዚያቸውን እያጠፉ ነው፡፡

የጀጁ ወረዳ፣ ዋና ከተባው አርቦዬ ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ከምስራቅ ሸዋ ቦሰት ወረዳ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ በወረዳው  ከግማሽ በላይ ነዋሪው አማራ ነው፡፡ ከጀጁ ወረዳ በስተምስራቅ፣ ብዙ ሳይርቅ የነ ወ/ሮ አዳነች አበቤ፣ ዶር አለሙ ስሜ ከተማ አቦምሳ ትገኛለች፡፡ በአርሲ ዞን አንድ አራተኛው ነዋሪ አማራ ሲሆን፣ ከሸዋ የመጡ፣ እዚያ ባሉ ጽንፈኞች፣ “አማራ” የሚባሉ ኦሮሞዎችም፣ ብዙ ናቸው፡፡ አርሲ ዞን ከምስራቅ ሸዋ ጋር በሚያዋስኑ እንደ ጀጁ፣ ስሬ፣ ዶዶታና መርቲ ባሉ ወረዳዎች አማራው በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠርም ገበሬ ሆኖ በስፋት የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ በቶሎ ሰላምና መረጋጋት ካልመጣና በዚያ ያሉ ጽንፈኞች አደብ ካልገዙ፣ አማራዉም ራሱን መከላከል ስላለበት ጉዳዮ ወደ ከፋ የዘር ጦርነት ሊያመራም ይችላል፡፡

ኦነጎች ፊት ለፊት ውጊያ አያውቁም፡፡ ጥንካሪያቸውን የሚያሳዩት ሕጻናት፣ እናቶችና አረጋዉያን ላይ፣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነው፡፡ Cowards ናቸው፡፡ ጀግና የሆኑ ይመስል መሳሪያ ታጥቀው የሚያሳይ ፎቶና ቪዲዮ ይለቃሉ፡፡ ግን ወረራ ፈጽመው ጥቃት የሚያደርጉት ኃይል እንደሌለ ሲያውቁ፣ ባልታጠቂ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነው፡፡ ተጨባጭ ጥያቄ ኖሯቸው የሚንቀሳቀሱ አይደለም፡፡ ተራ ሽፍቶች፣ አሸባሪዎች ናቸው፡፡ ለዓላማ ፣ ለህዝብ የቆሙ ቢሆኑ ኖሮ፣ ተደራጅተው፣ ነጻ መሬቶች ይዘው፣ ፊት ለፊት በአስተማማኝ ሁኔታ ነጻ መሬቶቻቸውን አስጠብቀው፣ በትክክል አላማቸውን አሳወቀው፣ መሪዎቻቸው በትክክል ታውቀው ቢያንስ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ማስደረግ ይችሉ ነበር፡፡ ግን ሰዎቹ ከመግደል፣ ከመዝረፍ፣ ከማሸበር ባለፈ የተጨበጠ የፖለቲካ አጀንዳን የላቸውም፡፡

ደግሞ ራሳቸውን ከህወሃት ጋር እኩል አድርገው ለምን እኛ ተረሳን ይላሉ ፡፡ ህወሃት እኮ ቢያንስ ፊት ለፊት የሚዋጋ፣ በተወሰነ መልኩ ዲሲፕሊን ያለው፣ ይሄ ያ እንዲሟሉ እፈልጋለሁ ብሎ አላማዉን አስቀምጦ የነበረ ነው፡፡ መከላከያ ሲመጣ የሚፈረጥጥ፣ መከላከያ ሲሄድ ጀግና ነኝ ብሎ የሚፎክር አይደለም፡፡ ኦነጎች ስንጥር ያህል ከሕወሃት ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም፡፡ ኦነጎች የፌዴራል መንግስቱ እጅግ በጣም ደካማ ስለሆነ፣ የቤት ልጆች ናቸው ብሎ ስለሚታገሳችው እንጂ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድራሻቸውን ማጥፋት ይቻላል፡፡

በነገራችን ሌላ የኦነግ አንጃ ያልኩት ፣ የተለያዩ ኦነጎች ስላሉ፡፡ ኦነግ አንድ አይደለም፡፡ አርሲና ከሚሴ አካባቢ ያሉ ከነ ጃል መሮ ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡  አርሲ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ሸዋ አካባቢ የሚንቀሳቀሱት ከሚሴ ካሉት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ ብዙዎች ከዘር አክራሪነት በተጨማሪም የኃይማኖት አክራሪነትን የተላበሱ ናቸው፡፡ በነ አጣዬ አላህ ኦ አክበር እያሉ ሽብር ሲፈጥሩ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ እነዚህ ኦነጎች፣ በአርሲ ፣ ባሌ ክርስቲያን የሆኑ ኦሮሞዎችን  “አማራ” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡

በወለጋ፣ በስሜን ሸዋና በምእራብ ሸዋ ያሉት፣የነ ጃል መሮ ኦነጎች ናቸው፡፡ በጉጂም ራሱን የቻለ የኦነግ አንጃ አለ፡፡ የጉጂው ኦነግ ግን ከወለጋው ኦነግ ጋር በቅርበት የሚሰራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉም የኦነግ አንጃዎች ደግሞ በየ አካባቢያቸው የብልጽግና መንግስት መዋቅር ውስጥ አሉበት፡፡ እነርሱን የሚደግፉ፣ የሚረዱ፣ የሚያስታጥቁ የኦሮሞ ክልልና የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎችም ፣ ቀን ቀን ብልጽግና፣ ማታ ማታ ኦነግ ሆነው የሚሰሩ ናቸው፡፡

የአብይ አህመድ መንግስት ሰዎች እንቅፋት ሲመታቸው ጁንታው ነው ይሄን ያደረገው ብሎ የመከሰስ፣ በአገሪቱ ላለው ችግር ሁሉ ጣጣቸውን የሚያሳዩት ሕወሃት ላይ ነበር፡፡ እነርሱ ደግፈው፣ አደራጀተው እዚህ ደረጃ ያደርሱት ኦነግ ለሚሰራው ወንጀል፣ ኦነኝ ሳይሆን የሚከሱት የነበረው ሕወሃት ነበር፡፡ ለምን ኦነጎች የቤት ልጆች ስለሆኑ በሌላው እንዲጠሉባቸው ስለማይፈልጉ፡፡ እውነታው ግ ን ሌላ ነው፤፡ ኦነጎች እዚህ ደረጃ የደረሱት በሕወሃት ምክን ያት አይደለም፡፡ ሕወሃት እዚህ ውስጥ የለበትም፡፡ ኦነጎች በኦሮሞ ብልጽግናዎች ስለሚደገፉ ነው፡፡

Filed in: Amharic