>

የሰላም ድርድሩን አስመለክቶ ከባልደርስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ...!

የሰላም ድርድሩን አስመለክቶ ከባልደርስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ…!

በህወሓትና በኦህዴድ/ብልፅግና መሃል ያለው የስልጣን ሽኩቻ እንጅ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት እንዳልሆነ ይታወቃል። በሶስተኛው ዙር ጦርነት ወቅት በኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በኩል የህወሓትን የመዋጋት አቅም ሙሉ በሙሉ እንዲንኮታኮት ማድረግ መቻሉ በገሃድ  ታይቷል። ይሁንና በሁለት ምክንያቶች ኦህዴድ/ብልጽግና በጦርነት ያገኘዉን ድል ያረጋገጠለትን የደቡብ አፍሪካ ስምምነት በናይሮቢ ስምምነት እየሻረዉ እንደሆነ የሰሞኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኦህዴድ/ብልጽግና የህዉሃት ወታደራዊ/ፖለቲካዊ አደረጃጀት እንዳይከሰም የሚፈለገባቸዉ ምክንያቶች ሁለት እንደሆኑ የታመናል። አንደኛዉ ከላይ እንደተጠቀሰዉ ከህዉሃት ጋር በነገድ ፖለቲካ አመለካከታቸዉ እና በአማራ ጥላቻቸዉ አንድ መሆናቸዉ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ደግሞ  የምዕራባዊያን ደጎሚዎቹን በተለየም የአሜሪካንን ተፅእኖ ለመቋቋም አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉ ነዉ።

ከህወሓት ጋር ከሚያመሳስለው የፀረ- አማራነት እና የፀረ ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አጀንዳ አንፃር አሁንም የኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ ከህዉሃት ጋር በናይሮቢ የተፈራረመዉ ስምምነት የአማራ ማህበረስብ  በህዉሃት በጉልበት የተቀማዉን ታሪካዊ አካባቢዎች  ለህዉሃት አሳለፎ ለመስጠት ያለመ መሆኑ እየተስተዋለ ነዉ። በዚህ አካሄድ ሰላምን ለዘለቄታዉ ማስፈን አይቻልም። ዘላቂ ሰላምን ማስገኜት የሚቻለዉ የትግራይን ህዝብ ስብአዊ ክብር የሚያስጠብቅ፣ የትግራይ ህዝብ ከአጎራባች የአማራ፣የአፋር፣ የኤርትራ ወንድማዊ እና አህታዊ ማህበረሰቦች ጋር በሰላም እና በፍቅር አብሮ ለመኖር የሚያስችል፣የእርዳታ አቅርቦት ሳይስተጓጎል የሚቀርብበት፣ በተቻለ ፍጥነት መሰረታዊ አገልግሎቶች የሚመለሱበት ሁኔታ ሲፈጠር ነዉ። ይህ እዉን ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግስት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ከህዉሃት ጋር የሚያደርገዉን የመሞዳምድ ፖለቲካ ሲተዉና የትግራይ ህዝብ የነገድ ፖለቲካ አራማጅ ከሆኑት ከኦህዴድ ብልጽግና እና ከህዉሃት የፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ የሆኑ፣ የህዉሃት የአማራ ጠልነት፣  የተስፋፊነት እና የዘረኝነት ልክፍት ያልታጣባችዉ፣ ህዉሃትን የሚጸየፉ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ ሲደግፍ እና እንዲበረቱ ተግቶ መስራት ሲችል ነዉ።

“ድመት መመንኮሷ ጠባዩዋን ላትረሳ” እንደተሰኘዉ የሃገራችን ብሄል፣ ህዉሃት የአሽባሪነት ተፈጥሮው ሊለቀዉ የማይችል እና ከዉልደት አስከ መጃጀት ድረስ የተጣባዉ ባህሪዉ ነው፡፡  በድረድሩ ተገኘ የተባለዉ ዉጤት ህዉሃትን ትጥቁን በማስፈታት ብቻ ሳይወሰን፣ ማናቸዉንም አይነት ወታደራዊ/ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን ማምከን የማይችል እና የማይፈለግ ከሆነ፣ ወደፊት አራተኛ ዙር ጦርነት ላለመቀስቀሱ ዋስትና ማግኘት አይቻልም። በሌላ በኩል ጦርነቱ በተኩስ አቁም ስምምነት ተቋጭቷል ቢባለም፣ወደፊት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀዉ ብሄራዊ ዉይይት በጦርነቱ ለደረሰዉ ጥፋት የሽግግር ጌዜ ፍትህ እንዲሰጥ፣አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ ተበዳዮች በተገቢዉ ሁኔታ እንዲካሱ ካላስቻለ፣ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚቻል አይሆንም። በተጨማሪም በህገ መንግስቱ ላይ ብሄራዊ ውይይት ተከፍቶ የህገ መንግስቱ ዋንኛ መገለጫ የሆነዉ የነገድ ፖለቲካን የሚመለከቱ አንቀጾች በሙሉ  እንዲሻሩ ሳይደረግ፣ ይህ ፖለቲካ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የፈለፈላቸዉ የማነነት እና የዉስጥ ወሰን ችገሮች ሳይፈቱ፣ የድርድሩም ሆነ የዉይይቱ ዉጤት ህዉሃትን  ከሽብርተኝነት ሊስት አስወጥቶ ህጋዊነትን በማላበስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ተጫዋች እንዲሆን በማድረግ የሚቋጭ ከሆነ፣ ለሃገራችን ስር የሰደዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት አይቻልም።

 

ድርድሩ ግልፅነትና አሳታፊነት የጎደለዉ በመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የደረሰባቸዉን የአማራ እና የአፋር ማህበረሰቦች ጥቅም ሳያማክልና ቁስላቸውን ሳያደርቅ ብሄራዊ መግባባት ብሎ ነገር የሚታሰብ አይሆንም፡፡

በመሆኑም፦

1. በድርድሩ የአማራና አፋር ማህበረሰቦችን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሂደቱ ተሳታፊ መሆን ሲገባቸዉ፣ይህ እንዲሆን አልተደረገም። ፓርቲያችን ባልደራስ ከህዝብ ጀርባ  የተደረገ፣ ተጎጅ ማሀበረሰቦችን ያላካተተ የጓዳ ድርድር እና ስምምነት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም  ያስገኛል የሚል እምነት የለዉም።

2. በደቡብ አፍሪካዉ ድርድር በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ያለዉ ልዩነት ህገመንገስቱን መሰረት በማድረግ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ሁኗል። ይህ የስምምነቱ አንቀጽ ህዉሃት ከህገመንግስቱ በፊት ከአማራዉ ታሪካዊ ይዞታዎች በሃይል ነጥቆ የያዛቸዉን ወልቃይት እና ራያን ወደ ትግራይ ክልል ማስመለሰን ግብ አድርጎ የተቀረጸ ነዉ። ይህ አንቀጽ ሌላ ዙር ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቀስና ሃገራችን የሚያስፈልጋትን ሰላም እንዳታገኝ የሚያረጋት በመሆኑ፣ ባልደራስ ይህን የስምምነቱን አንቀጽ አጥብቆ ይቃወማል።

3. በአማራ ክልል በገለልተኛ አካላት የተጠና ጥናት በፌደራል መንግስት እና በአማራ ክልላዊ አስተዳደር ተደጋጋሚ የክተት ጥሪ መነሻነት የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ሉአላዊነት አለመገሰስ፣ለህልዉናዉ መጠበቅ እና ለሰብአዊ ክብሩ መከበር ሲል ባካሄደዉ ተጋድሎ  ወደ 1 ትሪሊዬን የሚገመት የሀብት ዉድመት እንደደረሰበት አመላክቷል። በስምምነቱ ዉስጥ ለዚህ ጉዳት ፍትሃዊ ተጠያቂነት ሊኖር  እና ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታ ሊካተት ሲገባ አልተካተተም። ይሀን ስምምነት በኦህዴድ/ብልጽግና እና በህዉሃት መካከል ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስገደዱት የምእራቡ አለም እና በተለየም የአሜሪካ መንግስት በጦርነቱ ምክንያት ትግራይን ጨምሮ በአማራና እና በአፋር ክልሎች  ለደረሰዉ እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን እርዳታ እንዲሰጡ በስምምነቱ ዉስጥ ማሻሻያ እንዲካተት ሊደረግ እንደሚገባ ፓርቲያችን ባልደርስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡

4. በጦርነቱ የህይዎት መስዋእትነት ለከፈሉ የተዋጊ ቤተሰቦች፣ የኣካል ጉዳት ለደረሰባቸዉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የፋኖ፣ የአማራ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ፣ ለአፋር ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ  የደረሰባቸዉን ጉዳት የሚመጥን ካሳ እንዲመደብላቸው ፓርቲያችን ባልደራስ አበክሮ ያሳስባል፡፡

ባልደራስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ

ህዳር 5/2015 ዓ.ም

Filed in: Amharic