>

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ወልቃይት ምን አሉ? (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስለ ወልቃይት ምን አሉ?

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር


🔴  “ወልቃይትን በሚመለከት የሚነገሩ ሽረባዎች፣ ሴራዎች፣ conspiracies ብዙ እሰማለሁ። የኢትዮጵያ መንግስት በእነዚህ ሽረባዎች ውስጥ እጁ የለበትም። የወልቃይት ህዝብ እንዲገነዘብ የምንፈልገው፤ የሚወራው፣ የሚናፈሰው አሉባልታ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት እጁ የለበትም።”

🔴  “እኛ ደቡብ አፍሪካ የሄድንው ወልቃይት ወደ አማራ ይሁን ወደ ትግራይ ይሁን የሚለውን ለመወሰን አይደለም። የፕሪቶሪያው ‘ሰሚትም’ ይኸን ለመወሰን ስልጣን የለውም። ምን አገባው እና ነው የኢትዮጵያን መሬት እዚያ ሂድ እዚህ ሂድ የሚለው? እኛ እዚያ የሄድንው እንዴት ሰላም አምጥተን በንግግር ችግሮቻችንን እንፍታ ለማለት ነው። ለምን ወልቃይት ተስቦ እዚያ ውስጥ እንደሚገባ አላውቅም።”

🔴  “ወልቃይት ብቻ አይደለም፤ ሰሜን ሸዋ ላይ ኦሮሚያ እና አማራ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ሲዳማ እና ወላይታ፤ ብላቴ ላይ ጥያቄ አላቸው። እሱም ደቡብ አፍሪካ ይሂድ? ቦታው አይደለም። የተስማማነው በኢትዮጵያ ህግ እና ስርዓት ይፈጸም ነው።”

🔴  “ከህገ መንግስት በፊት ነው የተወሰደው፤ በጉልበት ነው የተወሰደው” ላሉት፤ የእኔ ፍላጎት ያ ስህተት እንዳይደገም ነው። ዛሬ እኔ በጉልበት፤ ነገ ታገሰ በጉልበት ከሆነ ዘላቂ ሰላም አያመጣም። ወልቃይት ብንፈልግም ባንፈልግም የተወላገደ አማርኛ፣ የተወላገደ ትግርኛ የሚናገር፤ የሁለቱ ህዝቦች ድልድይ የሆነ ህዝብ ነው። ሁለቱንም ቋንቋ የሚናገር የተጋባ የተዋለደ ህዝብ ነው። ‘ወልቃይቴነቱን ነው አትንኩብኝ’ ያለው እንጂ ከእንግዲህ በኋላ ትግራይ ከሚባል ጋራ አልገናኝም፤ አልነጋገርም አላለም። ቢልም አይችልም።”

🔴  “ይህን በህግ እና በስርዓት ብንፈጽም ለወልቃይት ይጠቅማል። ለአማራ ይጠቅማል። ለትግራይ ይጠቅማል።  የሚጎዳው ነገር የለም። በህግ እና ስርዓት እንፈጽም የሚለውን ነገር ከብዙ ተንኮል ጋር ማያያዝም አስፈላጊ አይደለም። እዚያ አካባቢ ጥያቄ ረዘም ላለ ጊዜ ነበረ። ከዚህ ቀደም ኮሚሽን ያቋቋምነው ለዚያ ብለን ነው። አሁንም ያኔም የነበረን አቋም በህግ አግባብ በምክክር በውይይት ይፈታ የሚል ነው።”

🔴 “ከአማራ ወገን ላለፉት 30 ዓመታት ብዙ ወልቃይቴዎች ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱ ኖረዋል። እነሱ በሌሉበት ህዝበ ውሳኔ ቢባል፤ የተመናመነ ህዝብ ነው እና እንጎዳለን። በትግራይ በኩል አሁን በተፈጠረው ግጭት ብዙ ሰው ወጥቷል። ስለወጣ አሁን ባለው ቢወሰድ አማራ ክልል አድቫንቴንጅ ይወስዳል የሚሉ ስሞታዎች ይሰማሉ። ወልቃይቴ፤ ወልቃይቴ ነው፤ ይታወቃል። ከአድዋም የሄደ፤ ከደብረ ማርቆስም የሄደ ሰው ሊኖር ይችላል። ግን ወልቃይቴ ይታወቃል። አትላንታም ይኑር፣ አውስትራሊያም ይኑር፣ ጅማም ይኑር፤ ስለዚያ ቦታ ሀሳብ እንዲሰጥ ዕድል ካልተሰጠው በስተቀረ ዘላቂ ሰላም አያመጣም።”

🔴 “ጉዳዩ ወደዚያ ስለሄደ፣ ወደዚህ ስለመጣ ሳይሆን፤ ያ ህዝብ የራሱን ዕጣ ፈንታ እንዲወስን፤ ዲሞክራሲያዊ ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው መፍትሔ የሚመጣው። እነዚያን ችግሮች በሚቀርፍ መንገድ እንደሚሰራ ተስፋ አደርጋለሁ። ጊዜ የወሰድነው፤ ጊዜ የጠበቅነው ለዚያ ነው።“

🔴 “ከህገ መንግስት በፊት ህወሓት በግድ ስለወሰደ አሁን እኛ ደግሞ በግድ ወስደን፤ እዚያ ዘመኑን በሙሉ ወታደር ልናቆም አንችልም። በስምምነት ካልሆነ በወታደር ነው የሚሆነው። በወታደር ከሆነ ዘላቂ አይሆንም። ጊዜ ይፈታዋል። አሁን ያለን ሰዎች ስናረጅ፣ ስንደክም፤ ልክ አሁን የተፈጠረው ይፈጠራል።“

[በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ። ይህ ዘገባ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]

* * ለተጨማሪ፦ https://ethiopiainsider.com/2022/8639/

Filed in: Amharic