>

የሸገር ከተማጉዳይ:- ከተሞቹም በአንድ ከንቲባ ይመራሉ....! (ዋዜማ ሬድዮ)

የሸገር ከተማጉዳይ:-

ከተሞቹም በአንድ ከንቲባ ይመራሉ….!

ዋዜማ ሬድዮ/ሚዲያ


በአዲስ አበባ ዙርያ ያሉ የፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞን ስር የነበሩ ሰበታ ፣ ቡራዩ ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ ፣ ሱሉልታ እና ገላን ከተሞችን በአንድ ያቀፈ “ሸገር ከተማ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የከተማ አስተዳደር  ሊቋቋም መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች።

በጨፌ ኦሮምያ በቀረበ ሀሳብ መሰረት የተሰናዳው የከተማው መዋቅር የተጠናቀቀ ሲሆን የከተማ ማቋቋሚያው የህግ ሰነድ በጨፌው ሲጸድቅ ወደ ስራ እንደሚገባም ሰምተናል።

በአዲሱ የሸገር ከተማ ውስጥ የሚካተቱት አምስቱ ከተሞች እያንዳንዳቸው የከተማ ስያሜ የሚኖራቸው ሲሆን በስራቸው የተዋቀሩ ክፍለ ከተሞች ይኖራቸዋል ። ከተሞቹ በሙሉ የሚመሩት በአንድ ከንቲባ እንደሚሆንም ዋዜማ ከኦሮምያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ሰምታለች።

አምስቱ ከተሞችም በጥቅሉ 12 ክፍለ ከተማ ይኖራቸዋል። ቡራዩ እና ሰበታ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ክፍለ ከተማ ሲኖራቸው ; ገላን ፣ ለገጣፎ ፣ ለገዳዲ እና ሱሉልታ ደግሞ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ክፍለ ከተሞች እንደሚኖራቸው ዋዜማ  የከተሞቹን ምስረታ ከሚያትተው ሰነድ ተመልክታለች።

ለአብነትም ገላን ከተማ ኮዬ ፈጬ እና ገላን የተባሉ ክፍለ ከተሞች ይኖሩታል። ይህ ከተማ የዱከምን የተወሰነ ክፍል ወስዶ የሚዋቀር እንደሆነ ሰምተናል። ሰበታ ደግሞ ገላን ትልቁ ፣ ሰበታና ፉሪ የተባሉ ክፍለ ከተሞች ይኖሩታል። ቀሪ ሶስት ከተሞችም እንዲሁ በክፍላ ከተሞች ይዋቀራሉ። ክፍለ ከተሞቹ እና ከተሞቹ በስራ አስፈጻሚ እና መሰል አመራሮች የሚተዳደሩ ሲሆን ፣ አምስቱ ከተሞች ግን “ሸገር ከተማ”  በሚል ለተሰየመው ከተማ በሚሾመው ከንቲባ የሚተዳደሩ ይሆናል።

አዲሱ መዋቅር ያስፈለገው ነባሩ የፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞን አስተዳደር የከተሞቹን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ባለመቻሉ እንደሆነ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣን ለዋዜማ ተናግረዋል።

“ አምስቱ ከተሞች በፊንፊኔ ዙርያ ልዩ ዞን ስር ይሁኑ እንጂ በህግ ራስ ገዝ በመሆናቸውና በአንድ የሚያዛቸው ለመኖሩ በከተሞቹ መካከል ያለውን እድገት ያልተመጣጠነ አድርጎታል። የከተሞቹ ራስ ገዝ መሆን ደግሞ ለስሙ ከበላያቸው ዞን የሚል የአስተዳደር ስያሜ ያለው አደረጃጀት ኖረ እንጂ በአንድ አቀናጅቶ ሊያስተዳድራቸው አልቻለም” እንደ ባለስልጣኑ ገለፃ።

“ ስለዚህ የዞን መዋቅሩ ተንጠልጥሎ ነው የቀረው”  ይላሉ ሀላፊው “ በመሆኑም ሁሉንም ከተሞች በእኩል የሚያስተዳድር በከተሞቹም ላይ እውነተኛ ስልጣን ያለው መዋቅር አስፈልጓል”

የሸገር ከተማ አወቃቀርም የአምስቱን ከተሞች እድገት ተመጣጣኝ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሀላፊው  እምነታቸውን ነግረውናል።  በሌላ በኩል ከተሞቹን በእኩል የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ የየከተሞቹ የጸጥታ ሁኔታ የተለያየ ስላደረገው ይህም ይቀረፋል ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

አወቃቀሩ ወደ ህጋዊ ስራ እንዲገባም የጨፌ ኦሮምያን ውሳኔ ይጠብቃል ተብሏል።

የ ”ሸገር ከተማ”  አስተዳደር መቀመጫም አዲስ አበባ ትሆናለች የተባለ ሲሆን በቅርቡ በተሰራው የአስተዳደር ወሰን አከላለል ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮምያ የገቡት ስፍራዎች በአዲሱ ከተማ ስር ባሉ መዋቅሮች ውስጥ የሚታቀፉ ይሆናል። የሸገር ከተማን ለማስተዳደር የተመረጡት ከንቲባ የኦሮምያ ፕላኒንግ ኮሚሽን ኮሚሽነር  የነበሩት ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የኦሮሚያ ኮምኒኬሽን ፅቤት በጉዳዩ ላይ ወደፊት በከፍተኛ ሀላፊዎች ማብራሪያ ስለሚሰጥ አሁን መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ነግረውናል። [ዋዜማ ሬዲዮ/ሞዲያ ]

Filed in: Amharic