>

ከታዲዮስ ታንቱ እስር ጋር ተያይዞ:- (ሞገስ ዘውዱ)

ከታዲዮስ ታንቱ እስር ጋር ተያይዞ:-

ሞገስ ዘውዱ


ስለ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ( ጋሼ የጨመርኩት በእድሜው ምክንያት ነው) ጋር ተያይዞ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ፣ እኔንም ጨምሮ። የሌሎቹን ባላውቅም የእኔ አስተያየት የሚከተሉት ናቸው።

(፩) በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ለምን ይጠረጠራል ወይም በበቂ ማስረጃ እና ፍትሃዊ መንገድ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ለምን ተቀጣ አይባልም፣ እኔም አልልም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ከህግ በታች ስለሆነ( ቢያንስ በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ)። ስለዚህ፣ ለምን ይጠረጠራል ወይም ይከሰሳል ብዬ አላውቅም!

(፪) በወንጀል መጠርጠር የግለሰቡን ማንነት( እድሜ፣ ሙያ፣ ታሪክ፣ ወዘተ) አይቀይርም። ለምሳሌ ፕሮፌሰር በወንጀል ተጠረጠረ ተብሎ ወያላ አይሆንም። አቶ ታዲዮስም  በሙያቸው( ልምዳቸው)ጋዜጠኛ እና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። ይሄን የክስ መዝገብ አይለውጠውም!

(፫)በይዘት ደረጃ አወዛጋቢ፣ አነጋጋሪ፣ አናዳጅ እና አልፎ አልፎ ቀጥታ የህዝብ ጥላቻ ያለበት ንግግር ያደርጋሉ። ኋላፊነት የማይሰማቸው ጋዜጠኞች ደግሞ እቤቱ ድረስ ሄደው ይሄን እንዲያደርግ ሆን ብለው  ያበረታቱታል፤ አብዛኞቹ እንዲያውም ስድቡን ያጣጥሙታል። ዛሬ ሲታሰር ግን ከጎኑ የሉም።

(፬) ተጠያቂነት ከመጣ ጥላቻ የዘሩ፣ የዘር ፍጅት የመሩ ሰዎች ሁሉ መጠየቅ አለባቸው። በዚህ ረገድ፣ ሌሎች ፋሽስቶች ዘና ብለው እየኖሩ ሽማግሌው ታዲዮስ ለብቻ ነጥሎ ማንገላታት የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ያሳብቃል።

(፭) ተከሳሽም ቢሆን ፍትህ ያስፈልገዋል( due process of law)!

በአለም-አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የተከሳሽ መብቶች አሉ: ግልፅ ክስ፣ ፈጣን ፍትህ፣ ገለልተኛ ፍርድ፣ የግለሰብ ክብር( trial with dignity)፣ እራስን መከላከል፣ ወዘተ። በዚህ ረገድ ሲታይ፣ ጋሽ ታዲዮስ ፈጣን ፍትህ ተነፍገው በፖለቲካ ውሳኔ እየተሳቃየ ይገኛሉ። ይሄንን ማንም ትክክለኛ ህሊና ያለው ሰው ይፀየፈዋል!

(፮) በእድሜ የገፉ ሽማግሌዎችን በእስር ማሸማቀቅ( harassment suits) ለህዝብ ካልጠቀመ( if not in the interests of justice) ክሱን መተው የተሻለ ነው። ለዚህ የሚሆን የቅርብ ጊዜ አሰራር አለን።  አቦይ ስብሃት የተፈቱት በወንጀል ስላልተጠረጠሩ ሳይሆን ( በሽብር ነበር የተከሰሱት) እድሚያቸው ስለገፋ እና የሳቸው እስር ላይ መቆየት ለፍትህ ስርዓት መጎልበት የጎላ አበርክቶ የለውም ተብሎ በመታሰቡ( political decision) ነው።

ስለሆነም፣ የክርክር እና የትችት ምክንያቶችን እየደባለቅን ባናቀርብ መልካም ነው!

Filed in: Amharic