የጉራጌ ዞን ከዛሬ ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ ውሳኔ ተላለፈ….!
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ከዛሬ አርብ ህዳር 16፤ 2015 ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ አስታወቁ። የጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን የተደረገው፤ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር “በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር” ባለመቻሉ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
የደቡብ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ይህን ያስታወቁት፤ የጉራጌ ዞን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ትላንት ሐሙስ በሰጡት መግለጫ ነው። የጉራጌ ዞን በተደራጀ ኮማንድ ፖስት እንደሚመራ ትላንት ምሽት በደቡብ ክልል ቴሌቪዥን በተላለፈው መግለጫቸው ይፋ ያደረጉት አቶ አለማየሁ፤ “የኦፕሬሽኑን ስራ” የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ልዩ ኃይል በቅንጅት እንደሚመሩ ተናግረዋል።
ሁለቱ አካላት ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችን ይዘው፤ በተደራጀ መንገድ በአካባቢው ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን የጸጥታ ችግር እንደሚያስተዳድሩ የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። በደቡብ ክልል በማዕከል ደረጃ ይህንን የሚያስተባብር አካል መቋቋሙንም አክለዋል።
ኮማንድ ፖስቱ “በተደራጀ መንገድ በጥፋት ውስጥ ተቀላቅለው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር” የማዋል ተግባር እንደሚያከናውን አቶ አለማየሁ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። “የጥፋት ይዘቱን ያቀደ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ አጥፊ ድርጊት የፈጸመ፤ በግለሰብም፣ በቡድን ደረጃም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች በደንብ በተደራጀ መንገድ ተለይተዋል” ያሉት የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፤ “የጸጥታ ኃይሉ እነዚህ ኃይሎችን በሙሉ በቁጥጥር ስር ያውላል” ሲሉ በቀጣይነት የሚወሰዱ እርምጃዎችን አመልክተዋል።
እስካሁን በተደረገው ጸጥታን የማስከበር ስራ፤ በድርጊቱ ተሳተፈዋል የተባሉ ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል። “የጸጥታ አካላችን ቀጥታ እዚህ ላይ ተሳታፊ የነበሩ፣ ፊት ለፊት የተገኙ ከ70 በላይ ሰዎችን ይዟል” ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህን ተከትሎም በተጠርጣሪዎቹ ላይ “በተደራጀ መንገድ ምርመራ የማጣራት ሂደት” እንደሚደረግ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)