>

የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሥራ ማቆም አድማ....?!? (DW)

የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሥራ ማቆም አድማ….?!?

DW


በዩኒቨርሲቲዎች መምህራን የፊታችን ሰኞ ኅዳር 26 ቀን፣ ይደረጋል የተባለውን የሥራ ማቆም አድማ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን እና ቴክኒክ ረዳቶች ማኅበር እንዳልጠራው ዐስታወቀ። የኢትዮጵያ 42 ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበር የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ ጥሪ አለማቅረቡን ፕሬዝዳንቱ ዶክተር በፍቃዱ ዘለቀ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW)ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር በፍቃዱ እርሳቸው በሚመሩት ማኅበር ሥም ለኢትዮጵያ መንግሥት የቀረቡት ዐሥራ አራት ጥያቄዎች በእርግጥም ዩኒቨርሲቲዎች መምራን እና ቴክኒካል ረዳቶች መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ ቢያረጋግጡም የሥራ ማቆም አድማ ግን እንዳልተጠራ ገልጸዋል። ማኅበሩ ይህንን ያደረጉት የማናውቃቸው የተደራጁ አካላት ናቸው ብሏል። ይህን ያደረጉ ያላቸውንም እንደሚከስ ዐሳውቋል። ዶክተር በፍቃዱ፦ «ይህን ጥያቄ ያቀረበው ኢንፎርማል ግሩፕ የኛን ሎጎ ተጠቅሞ ነው ጥሪውን ያቀረበው። እኛ  ደግሞ ይህንን ተከታትለን በሕግ እንጠይቃለን። የሥራ ማቆሙ አድማ እና የጠየቅነው ጥያቄ አይደለም 14 ጥያቄዎችን ግን ለመንግስት ጠይቀናል። እነዚህን ጥያቄዎች እኛ በአሠራራችን ለትምህርት ሚኒስቴር ነው ያስገባነው» ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

በተቃራኒው ዶይቸ ቬሌ ያነጋገራቸው የዩኒቨርስቲ መምህራን የሥራ ማቆሙን አድማ ለማድረግ እንደውም ዘግይተናል ብለዋል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ማኅበርን ስም እና ዓርማ በያዘ ደብዳቤ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ኅዳር 15 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የተሰራጨው መግለጫ ዐሥራ አራት ጥያቄዎችን የያዘ ነው። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ ዕድገት፣ የቤት አበልን የተመለከቱ ይገኙበታል። ደብዳቤው በተጨማሪ ሥራዎች የሚገኝ ገቢ ላይ የግብር ቅነሳ፣ የሦስተኛ ዲግሪ የምርምር ገንዘብ መጠን፣ የመምህራን የዝውውር ጉዳዮችን ጭምር ያካተተ ነው።

Filed in: Amharic