>

በጅሮንድ ለጥ ይበሉ ገብሬ ፤ አሳዛኙ ፍጻሜያቸው (ታሪክን ወደኋላ)

በጅሮንድ ለጥ ይበሉ ገብሬ ፤ አሳዛኙ ፍጻሜያቸው

ታሪክን ወደኋላ

በጅሮንድ ለጥ ይበሉ ገብሬ ፤ የየካቲት 12ቱን የእነ አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም ጥቃት ሀሳቡ ከተጠነሰሰ አንስቶ የማቀናጀት ስራ ሲሰሩ የነበሩ ስመጥር አርበኛ ነበሩ። ከጥቃቱ በሁዋላ አብዛኛዋቹ በሴራው ላይ የተሳተፋ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በጅሮንድ ግን እስከ ነጻነት ዘልቀዋል ፤ ከነጻነት በኋላም በተለያዮ መንግስታዊ የሀላፊነት ቦታዋችም ላይ ሰርተዋል።

በጅሮንድ በትልልቅ ሽምግልናዎች ላይ ይሳተፋም ነበር ፤ ጀነራል መንግስቱ ነዋይ እና ግርማሜ ነዋይ ሊያገቡ ሲል ሁለቱን ወጣት መኮንንኖች ያባት ያህል ይቀርቧቸው ስለነበር ሽማግሌ ሆነው ከተላኩት ውስጥ እሳቸው ዋነኛው ሰው ነበሩ፤ አስገራሚው ነገር ደግሞ በጅሮንድ  ለጥ ይበሉ የተገደሉት በ 1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት በገነተ ልኡል ቤተመንግስት በነዚህ ወድማማቾች ነበር።

በጀሮንድ ለጥ ይበሉ ገብሬ አሟሟታቸው አስገራሚ ነው።  የ 1953 ቱ የነብርጋዲየር  ጀነራል መንግስቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግስት ፤ መፈንቅለ መንግስት አድራጊዋቹ የሚልፈጔቸውን ሰዎች እየያዙ ባሉበት ሰአት ወደ ቤተመንግስት ያመራሉ፤ ክቡርነታቸው አትገቡም እየተባሉ ነበር  በግድ አስቸግረው ወደ አስፈሪው የሞት ጎዳና የገቡት ።

ነገሩ ወዲህ ነው በጅሮንድ ለጥ ይበሉ ገብሬ ማንም ሳይጠራቸው ቤተመንግስት ካልገባሁ ብለው ጃነራል መንግስቱን አስቸገሩ “እርስዎ  አልተፈለጉምና ወደ መጡበት ይመለሱ ” በማለት ጀነራል መንግስቱ ቢከላከላቸውም……

“ግርማዊት እቴጌ ታመዋል እይተባለ እንዴት ብዬ ሳልጠይቃቸው ልመለስ ፤ጥርሴን ነቅዬ ያደግሁት እኮ እዚሁ ቤተ-መንግስት ውስጥ ነው ውለታ አለብኝ”

በማለት አሻፈረኝ ይላሉ በዚህ መሀል ገርማሜ ነዋይ ይደርሱና   እንዲገቡ ፈቀዱላቸው ፤ ገብተው ግን ብዙም አልቆዩም ፤ ነገርየው የጤና አለመሆኑን ከተገነዘቡ በሁዋላ ” ልውጣ ” አሉ “ቅድም ተለምነው አሻፈረኝ ብለዋል ፤ ከዚህ በሁዋላማ የሰው ምስጢር አይተው የትም መሄድ አይችሉም”  የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ይሰጣቸዋል ከዚህ በኋላ ግን አልተመለሱም ፤ ከሌሎች  የአፄ ኃይለሥላሴ ባለስልጣኖች ጋር በአረንጔዴው አዳራሽ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል።

@ታሪክን ወደኋላ

Filed in: Amharic