>
5:14 pm - Thursday April 20, 6062

የዳኛ ያለህ....! (በእውቀቱ ስዩም)

የዳኛ ያለህ….!

(በእውቀቱ ስዩም)


“አምላክ ሆይ፤ ለፍጥረትህ የአምላክነት ስልጣን ብትሰጠው ባንድ ቀን እናልቅ  ነበር “ ይላል አንድ የጥንት የግእዝ ባለቅኔ፤ ( አሐደ እለት እምተፈጸምነ ለፍጥረትከ አምላክ ፥ እመ አምላክ ትሬስዮ )

በዚህ ባለቅኔ እምነት ፥ የእግዜር ፍጡራን (ሰዎችና መላእክት ) ጨካኞች ናቸው ፤ ዓለም በኒህ ፍጡራን ጭካኔ እስከዛሬ ጨርሳ  ያልወደመችው በፍጡራኑ  የአቅም  ውስንነት ምክንያት ነው::

የሰው ልጅ በውስጡ የበጎነት ቡቃያና የክፋት ቡቃያ የያዘ ፍጥረት ነው፤ የበጎነቱ ቡቃያ ሲፋፋ ጥሩ ዜጋ ይሆናል፤  ይፈበርካል፤ ይገነባል፤ ለጎረቤቱ ያስባል፤ ለባላጋራው ይራራል ፤ ለራሱም ሆነ ለእህት ወንድሞቹ የደስታ ምንጭ ይሆናል፤ በተቃራኒው የክፋቱ ቡቃያ ከጸደቀለት፥  የሚሰራው የውድመትና የጭካኔ  የሆሊውድ ሆረር ፊልሞችን ያስንቃል:: ይህንን ኖረን አይተነዋል::

አንድ ማህበረሰብ በግለሰቦች የጭካኔ እና የውድመት ማምከን የሚችለው  በሁለት መንገድ ነው፤ በልማድ እና በህግ፤  በአገራችን በበዙ የብሄረሰቦች ባህል ጠላትን መግደል የሚከበር ድርጊት ሆኖ ቆይቷል ፤ እንዲያውም ገድሎ መፎከር ፥ የብስለት Maturity) ማስመስክርያ ነበር፤ ቢያንስ አንድ ጠላት  ወይም የዱር አውሬ፥ መግደሉን ያላስመሰከረ ወጣት ሚስትም ሆነ የማህበረሰብን ከበሬታ ማግኘት አይችልም ነበር::

ያም ሆኖ  ያገር ልማዶች ጭፍን ጭካኔን የሚያበረታቱ አልነበሩም፤  ያልታጠቀ ሰው መግደል፤ በጦር ሜዳ ላይ የተገኙ ህጻናትን፥ ሴቶችን እና የሀይማኖት ሰዎችን መጨፍጨፍ እንደ ነውር ይቆጠር ነበር፤   እኒህን ድርጊቶች የሚፈጽም ሰው፥ “ ግፈኛ” እና “  ወራዳ “ ይባላል እንጂ “ጀግና”  ተብሎ አይጠራም ፤  በርግጥ ይህንን ልማድ የሚጥሱ በየጊዜው እዚህም እዚያም አይጠፉም፤ ግን በስራቸው አልተከበሩበትም::

ሁለተኛው መንገድ ህግ ነው፤    የመንግስት ቀዳሚ  ስራ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉትን ሽፍቶችና ነፍስ ገዳዮች  በገቡበት ገብቶ መቅጣት ነው፤ ነገስታት “ጃንሆይ”  የሚባሉት በከንቱ አልነበረም፤ “ ጃን”  ዳን ከሚለው ሴማዊ ቃል የመነጨ ሲሆን ዳኛ ማለት ነው፤ ፍርድ ከመስጠት የሚቀድም የመንግስት ተግባር የለም::

ዛሬ ጭካኔን የሚያመክኑ የማህበረሰብ ልማዶች ታመዋል፤ ወይ ከስመዋል፤ አለበለዝያ ፥ ያገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰዋል፤ የጭካኔ ስራ እሚሰሩ ሰዎች  ይሉኝታ ፤ እና ሀፍረት ቅንጣት አይነካቸውም፤ የጭካኔ አዝመራቸውን እንደ ድመት አይነምድር ከማዳፈን ይልቅ በቪድዮ ቀርጸው ይለቁልናል፤

የመጨረሻ ተስፋችን  ህግ ነው፤ መንግስት በግል እና በጅምላ ነፍስ የሚያጠፉትን አሳድዶ ለፍርድ እማያቀርብ ከሆነ እንደሌለ ይቆጠራል፤ ከላይ እንዳልኩት የመንግስት ህልውና ዋና ማሳያው ወንጀለኞችን መቅጣት ነው፤ ወንጀለኛን በቸልታ የሚያልፍ መንግስት መና ከሰማይ ቢያወርድ ፥ ወተት እና ማር ከአለቶች ላይ ቢያፈልቅ  ጥቅም የለውም::

የዘመናችን ማህበረሰብ የቡድኖች ጥርቅም ሆኗል ፤ የቡድናችን አባል ነው ብለን የምናስበው ሰው የጭካኔ ድርጊት ቢፈጽም ለማውዝ አንፈጥንም፤ እንዲህ አይነቱ ለቡድን ማድላት አባዜ  ከፖለቲካም ያልፋል፤  በእግር ኳስ ጨዋታ  ላይ የምንደግፈው ሰውየ ሌላውን በጠረባ ቢጥለው አይደብረንም፤ በተቃራኒው ቡድን ተጫዎች ተጠርቦ ቢወድቅ ቁጣችን እንደ ሳት ይነዳል፤ ደግነቱ ፍጹም ስልጣን ያለው የሜዳ ዳኛ ፤ ብጫና ቀይ እየሰጠ ጨዋታው በስርአት እንዲመራ ያደርጋል፤

 ከሁሉ አስቀድሞ፥ መንግስት ዋናውን ጉልበቱን ፥ እውቀቱን አጠራቅሞ ህግ  ያስከብር!  ሌላው ጸጋ ሳንጠራው ይመጣል!

Filed in: Amharic