>

ከተለያዩ ት/ቤቶች ከኦሮሚያ ባንዴራ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ የታሰሩ መምህራን የዋስትና መብታቸውን ተነፈጉ...!

ከተለያዩ ት/ቤቶች ከኦሮሚያ ባንዴራ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ የታሰሩ መምህራን የዋስትና መብታቸውን ተነፈጉ…!

*… ዋስትና የተፈቀደላቸውም በፖለቲካዊ ውሳኔ በእስር ቤቶች የስቃይ ጊዜያትን እንዲያሳልፉ እየተደረገ ነው…

አማራ ሚዲያ ማዕከል


በአምሓ ደስታ መታሰቢያ_እንጦጦ አምባ ት/ቤትን ጨምሮ በአዲስ ከተማ እና የካቲት አካባቢ ባሉ የተለያዩ ት/ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል ባንዴራ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የታሰሩ መምህራን የዋስትና መብታቸው እየተከበረ አለመሆኑ ተገልጧል።

አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚሉት የኦሮሚያ ክልል ባንዴራን ማሰቀል እና መዝሙር ማዘመርን በአዲስ አበባ የተለያዩ ት/ቤቶች ለመተግበር የተደረገውን የኃይል እንቅስቃሴ ተከትሎ በ18 ት/ቤቶች አለመረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ በርካታ መምህራን እና ተማሪዎች ታስረዋል።

በተለይም ከአዲስ ከተማ እና የካቲት አካባቢ ካሉ ት/ቤቶች የታሰሩ መምህራንና ተማሪዎች በአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸው ይታወቃል።

ከአምሓ ደስታ መታሰቢያ_እንጦጦ አምባ ት/ቤት ተወሰደው ከታሰሩት ከ17 ያላነሱ መምህራን መካከል በሁለት መዝገብ ተከፍለው ፍ/ቤት እየተመላለሱ ቢሆንም በአራዳ ፍ/ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው ጥቂቶች ናቸው ተብሏል።

የዋስትና መብት የተፈቀደላቸውም እንደገና በይግባኝ አቤቱታ እየተሻረ በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ሀአሚማ ምንጮች ተናግረዋል።

እንደአብነትም መምህር ህዳር 22/2015 ዓም ከጠዋቱ 4:45 ላይ በእንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኦሮሚያ ባንዲራ እንዳይሰቀል አድርገሃል በሚል የታሰረው መ/ር ዘመነ ጌቴን ጨምሮ ሌሎች በመዝገቡ ያሉ ሁለት ተከሳሾች ያለፈው አርብ በ5 ሽህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ተወስኖላቸው ነበር።

የተጠየቀውን የ5,000 ብር ዋስትና ከከፈለ በኋላ ይግባኝ በመባሉ ታህሳስ 11/2015 በነበረው ችሎት ዋስትናው ተከልክሎ በእስር ላይ እንዲቆይ የተወሰነበት ስለመሆኑ አሚማ ከመኢአድ የትግል አጋሩ ለገሰ ወ/ሀና ለማረጋገጥ ችሏል።

Filed in: Amharic