>
5:14 pm - Wednesday May 1, 8667

የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ  ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ ...!

የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ  ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ …!

 

የሰንደቅ ዓላማና  የብሔራዊ መዝሙር አዋጆችን በመጣሰ  በአ.አ የመንግሥት ት/ቤቶች ላይ  የኃይል እርምጃ ህገ ወጥ በመሆኑ እንዲያቆም ያሳስባል፡፡

የኦህዲድ ብልጽግና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል እና የክልሉን መዝሙር በኃይል እንዲዘመር ከሚፈጽማቸው ተግባራት  ጋር በተያያዘ የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ ሰዎች መታሰራቸውን እና የንበረት ጉዳት መድረሱን የተለያዩ ተቋማቶች ገልጸዋል፡፡

ኦህዴድ ብልጽግና እነዚህን አምባገነናዊ እርምጃዎች እየወሰደ ያለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 እና የብሔራዊ መዝሙር አዋጅ ቁጥር 673 በመጻረር መሆኑ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ የሰንደቅ አላማ አዋጅ 654/2001 አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 1፣  ‹‹በትምህርት ቤቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚሰቀለው ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ይሆናል›› ይላል። ይኸው አዋጅ 654/2001 በክፍል 1 አንቀፅ 3 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ግዴታ የተጣለባቸው ወይም የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን የሚመለከታቸውን ሲዘረዝር፣ በአንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ አንድ ‹‹በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የግዛት ወሰን ውስጥ  የክልል መንግሥታትና የከተማ መስተዳደሮችን ጨምሮ ነው›› ይላል፡፡ በሌላ በኩል የብሔራዊ መዝሙር አዋጅ ቁጥር 673/2001 በአንቀፅ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ‹‹በት/ቤቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማ የሚሰቀለው ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር ይሆናል ይላል፡፡

ቅጣትን በተመለከተ በአንቀጽ 24 ከንዑስ አንቀጽ 1- 3 ባሉት አንቀፆች ይህን ሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ግዴታ በሚጥሱ ላይ ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ተኩል በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ ይደነግጋል፡፡

በአዋጅ በተደነገገው መሠረት ህጉን የጣሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና የእነሱ ጉዳይ አከናዋኞች ለህግ ቀርበው መቀጣት ሲገባቸው፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና አምባገነኖቹ ባለሥልጣኖች ‹‹ህግ ይከበር›› ያሉ ተማሪዎችን፣ መምህራንንና ወላጆችን የግድያ፣ የድብደባና የእሥራት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረጋቸው ‹‹ከእኛ በላይ ማንም የለም፤ ምን ታመጣላችሁ?›› የሚል የትዕቢት ተግባር መፈጸማቸውን ያሳያል፡፡ በዚህ አምባገነናዊ ሥራቸው በየካ ክፍለ ከተማ በቀበና አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ባንዲራ መሰቀል ጋር በተያያዘ በመንግሥት በተወሰደው የኃይል እርምጃ የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል፡፡ ‹‹የኦሮሚያ ክልልን ባንዲራ አንሰቅልም፤ መዝሙሩንም አንዘምርም›› ያሉ በርካታ የአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም መካከል የጉለሌ ክ/ከተማ እንጦጦ አምባ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ ቂርቆስ ክ/ከተማ የሽመልስ ሀብቴ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የጠመንጃ ያዥ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ለሚፈጠሩ ችግሮች ብቸኛው ተጠያቂ የከተማ አስተዳደሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ አደረጃጀቶች ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል። እንባ ጠባቂ ተቋሙ አክሎም የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ የሚያገኛቸው ልዩ ጥቅሞች እና የአፈጻጸም ሥርዓት ባልተቀመጠለት ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀልና እና መዝሙሩ እንዲዘመር የሚያስገድዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ‹‹ግለሰብ ባለሥልጣናት›› መኖራቸው ጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በበኩላቸው ከኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የተዋስነው የኦሮምኛ ማስተማርያ ስለሆነ ትምህርቱ ሲሰጥ መዝሙር መዘመር እና ባንዲራ መስቀልን ያስገድዳል ብለዋል፡፡ ከንቲባዋ አክለውም ‹‹ይህ አጀንዳ የፅንፈኛው ፋኖ እና የምዕራባዊያን እንጂ የህዝቡ አይደለም›› ሲሉ መናገራቸው ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያት የሰጡ አካላት በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ሕዝብን የመበደል ሥራ ላይ መጠመዱን ጠቅሰው አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ሓላፊ መላኩ ታምሩ በበኩላቸው ‹‹የኦሮምያን ባንዲራ አንሰቅልም፤ መዝሙርም አንዘምርም›› ያሉ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጠው ‹‹እርምጃ ወስደንባቸዋል›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹የተቃውሞውን ሰልፍ የመሩትን አካላት ዘመናዊ መሣሪያን ተጠቅመን ለይተናቸዋል፣ ችግሩ ሲፈጠር ከቤታቸው ነበሩ›› ካሉ በኋላ  የከሰሷቸው አካላት እንዳሉም ሓላፊው ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር የማዘመር እና ባንዲራ የማሰቀሉ ሂደት እንደሚቀጥል እና በሚቃወሙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰደም መላኩ ታምሩ ተናግረዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን በርካታ ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች እስር እና ድብደባ የተፈፀመባቸው ሲሆን የአንዳንድ ት/ቤቶች ንብረትም መውደሙ ታውቋል፡፡

ያልተሻሩ እና በሥራ ላይ ያሉ ከላይ የተጠቀሱትን የብሔራዊ ሠንደቅዓላማ እና የብሔራዊ መዝሙር አዋጆችን ኦህዴድ ብልጽግና በመንግሥታዊነቱ በቀዳሚነት እራሱ አክብሮ ዜጎች እንዲያከብሩት ሊያደርግ ሲገባ፣ ዋንኛው ህግ ጣሽ እራሱ ሆኖ ተገኝቷል። ተማሪዎች በዜግነታቸው በተደነገጉ መንግሥታዊ ህጎች የተከበሩላቸው መብቶች ህገወጥ በሆኑ መንግሥታዊ ኃይሎች ሲሻሩ፣ መብታቸውን ለማስከበር በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ሲያሰሙ ‹‹በጽንፈኞች እየተመሩ ነው›› በማለት የቁራ ጩኸት ከማሰማት አልፎ በዕድሜ ለጋ በሆኑ ትናንሽ ተማሪዎች ላይ ድብዳባ፣ እስራት እና አልፎም ግድያ መፈጸም በህግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው።

ኦህዴድ ብልጽግና የጽንፈኝነት እና የህገወጥነት ትርጉም ተሳክሮበታል። የአንድን ነገድ ቋንቋ እና ባንዲራ በሌሎች ቋንቋውን በማያውቁ፣ ሰንደቁን ሃገራዊ አይደለም ብለው ሰላማዊ ተቃውሞ ባነሱ ህጻናት ተማሪዎች ላይ በኃይል በመጫን የነገድ ጽንፈኝነትን እያራመደ ይገኛል፡፡ እራሱ ጸረ ዲሞክራሳያዊ ሁኖ ሳለ፣ ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ በሚል የአጉል ብልጣብልጥነት ፈሊጥ ለትክክለኛ መብት መቆምን እንደ ህገወጥነት እና ጽንፈኝነት መቁጠሩ ተገቢ አለመሆኑን ሊገነዘብ ይገባል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ወላጆች ከተማሪዎቻቸው እና ከልጆቻቸው ጋር በመቆም ላነሱት ሀገራዊ ጥያቄና እየከፈሉ ላሉትን መስዋትነት ባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የትግል አጋርነቱን ይገልጻል።

 

የባልደራስ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ  ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

#አዲስ_አበባ

#ኢትዮጵያ

ታህሳስ 19/2015 ዓ.ም.

Filed in: Amharic