>

ከአማራ ቆዳ በተሠራ ከበሮ: ጭፋሮ !! (አሥራደው ከፈረንሳይ)

ከአማራ ቆዳ በተሠራ ከበሮ: ጭፋሮ !!

(አሥራደው ከፈረንሳይ)

ክፍል ሁለት

መንደርደሪያ 

  ዕውን ኢትዮጵያ ምሁራን አሏት ?!  አሏት ከተባለስ፤ ዜጎቿ እንደቅጠል በሚረግፉበት በዚህ  አስከፊና ፈታኝ ወቅት፤ ከህዝባቸው ጎን ቆመው፤ አለንልህ ካላሉት፤ ከጅምላ ፍጅት፤ ከመታረድ፤ ከመፈናቀልና ከስደት ካልታደጉት፤ ምሁርነታቸው ለማንና ለመቼ ነው ?!  

ምሁርነት ከዘርና ከጎሣ በላይ፤ ክልል፤ ቋንቋና ዜግነት ሳይገድበው፤ የአገር ድንበር ተሻግሮ ዓለም አቀፉዊነት ነው::  እንደ ፀሐይ ጮራ፤ የግፈኞችን የግፍ መጋረጃ ቀዶ: ብርሃን የሚፈነጥቅ:: ከፍራቻው ወህኒ ቤት ወጥቶ፤ በድፍረት በፍትሕ ማማ ላይ ቆሞ፤ ነፃነትን ለሰዎች ልጆች ሁሉ የሚያውጅ ::

  በአንፃሩ፤ ምሁር በሆዱ ተሸንፎ ፤ ከምቾት ክልሉ ወጥቶ፤ አንዲት ስንዝር ያህል፤ ፈቀቅ ማለት አቅቶት፤ ጭንቅላቱን በሽንፈላው ውስጥ ወሽቆ: የሚያንኰራፋ ከሆነ፤ ትውልድን በክሎ አገር ያጠፋል:: ምድርም በድርጊቱ ትጠየፈዋለች፤ ታሪክም ይወቅሰዋል:: 

  የኢትዮጵያ ህዝብ፤ እንኳን ሲሸጡት ገና ሲያስማሙት፤ ቀድሞ መረዳት የሚችል ብልህ ህዝብ ነው :: የችግሩና የድህነቱ፤ ምንጮች አዘራፊዎቹ ህወሃት፤ ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) ሲሆኑ ዘራፊዎቹ ደግም አሜሪካና የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች እንደሆኑ፤ ጠንቅቆ ያውቃል :: ለህወሃትና  ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) የልመና አቁማዳ መሙያ፤ ላለመሆን፤ በዘርና በጎሣ መከፋፈሉን ትቶ፤ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ሲዳማ፤ ወላይታ፤ ከንባታ፤ ሃዲያ፤ ኮንሶ፤ ሱማሊ……ወዘተ. ሳይል፤ በአንድነት ተነስቶ፤ አገሩን ከአዘራፊዎችና ከዘራፊዎች፤ እራሱን ከውርደት፤ በጋራ ካልተከላከለ፤ ሁሉም በየተራው በተናጠል እየተመታ ይጠፋል ::

ህወሃት: ጥቂት ዘራፊና፤ አዘራፊ ቡድኖችን እንጂ፤ ሁሉንም የትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አይወክልም :: ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) ተብዬውም ጥቂት የኦሮሞ ቡድን ሌቦችና፤ አዘራፊዎችን፤ ይወክል እንደሆነ እንጂ፤  ጠቅላላውን የኦሮሞ፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አይወክልም :: ስለዚህ እነዚህን የዘርና የጎሣ፤ የፖለቲካ ዝሙተኞች በመጠየፍ፤ በአንድነት ተነስተን በማስወገድ፤ በነፃነትና በዕኩልነት አብረን የምንኖርባት፤ ኢትዮጵያን እንገንባ :: 

የዘር ግምቡ ይፍረስ ህጉም ይከለስ !!

የዘር ግምቡ ሳይፈርስ፤ ህጉ ሳይከለስ፤ በኢትዮጵ ሠላም ሊኖር አይችልም !!                               ህወሃት ከፋሽስት ጣልያን በወረሰው ስልት፤ ኢትዮጵያን በዘርና በጎሣ ከፋፍሎ፤ እግሩን አንፈራጦ፤ ለመግዛት ባወጣው ህገ አራዊት 27 ዓመታት የኢትዮጵያን  ህዝብ  እየ ዘረፈ አዘርፏል ::                 ቀጥሎ የህወሃት አሽከሮች፤ ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/)፤ ብአዴን ተብዬውን በጃንደረባነት ይዘው፤ ለ4ዓመታት፤ በዚያው ህገ አራዊት፤  የኢትዮጵያን  ህዝብ እየዘረፉና  እያዘረፉ ይገኛል ::   

ከአሁን በኋላ ህወሃትና አሽከሮቹ ባወጡት « ህገ መንግሥት ተብዬ » በትክክለኛ አጠራሩ ህገ አራዊት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ አገሩን የሚያዘርፍበት፤ እራሱን የሚያጠፋበት ምክንያት አይኖርም :: አማራውን ያገለል፤ ከሁለት ቤተሰብ የተወለድን ኢትዮጵያውያንን የካደ፤ የወልቃይት ጠገዴና፤ ሁመራና ራያ፤ እንዲሁም የአፋር ህዝብ ችግሮች፤ ህወሃት ባወጣው ህገ አራዊት አይፈቱም ::

መግቢያ

በክፍል አንድ መጣጥፌ፤  የህወሃትና ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) ጥርቅሞች፤ ላይጣሉ ተጣልተው፤ ላይታረቁ ታረቁ  እንጂ ሠላም አላወረዱም :: እንዲያውም ፤ ህወሃትና ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ ) በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት አንድ ትልቅ ደባ፤ አማራውን በጋራ ዘንጥለውና፤ ቀረጣጥፈው ለመብላት፤ ጥርሶቻቸውን ለመሞረድ የጊዜ መግዣ ለማግኘት ሲሆን፤ ታረቅን በሚል ቧልት በደቡብ አፍሪካ ጥርሶቻቸውን ጉራይማሌ ተነቅሰው ተመለሱ እንጂ፤ ዘላቂ ሠላም አላወረዱም፤ ብዬ ነበር ያቆምኩት::

በዚህ በሁለተኛው ክፍል፤ መለስ ዘናዊ እየሰደበን፤ አብይ አህመድ እየሰበከን ፤ እንዴት ለዚህ ውርደት እንደበቃን ለመቃኘት እሞክራለሁ ብዬ እንደነበርም አስታውሳለሁ::

ስለ መለስ ዘናዊ ዋልጌነት፤ አገር ያወቀው ጠሐይ የሞቀው እንደነበር ማንም አይረሳ፤ የአድዋ ድል ለደቡቡ ምኑ ነው፤ አማራን ተመልሶ እንዳያንሰራራ አድርገን ሰብረነዋልወርቅ ከሆነው ከትግራይ ህዝብ በመፈጠሬ እኮራለሁ፤ ኢትዮጵያን የመሰለ የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ትልቅ አገር እየመራ፤  ስሟን ለመጥራት ባለመሻት፤ ይች አገር እያለ እንዳንጓጠጣት ………. ወዘተ.  ወደመቃብር ወርዷል ::

መለስ ዘናዊን፤ እንደፈጣሪው ያመልክ የነበረው ዐብይ አህመድ፤ አጋጣሚ በፈጠረለት ክፍተት ወደ ስልጣን ሲመጣ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ መለስ ዜናዊ ፤ እየተሳደበ መምራት እንደማይችል ስለተረዳ  ለ27 ዓመታት ከእህል በባሰ ተርበን የነበረውን፤ የአገራችን የኢትዮጵያን ስም ፤ ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያ ! ኢትዮጵያ ! እያለ ሲሰብከን እውነት መስሎን ትጥቃችንን ፈታን ::                                       እነሱ ሊሰሙ የሚፈልጉትን እየነገርካቸው፤ አንተ ማድረግ የምትፈልገውን ሥራ !!  የሚል ፈሊጥ መሁኑ የገባን ውሎ አድሮ ነበር:: 

የኢትዮጵያ ነፃነት እንዳይደፈር፤ የኢጣሊያንን ፋሽስት በአድዋ ጦርነት ድል ያደረጉና፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ የኢትዮጵያን ስም ከፍ አድርገው ያስጠሩ፤ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሠንደቅ ዓላማዋን፤ ከፍ አድርገው ላውለበለቡት፤ ዳግማዊ ምኒልክና እተጌ ጣይቱ፤ ብሎም የአድዋን ድል ዕውቅና የነፈገ (የካደ) መናፍቅ፤ ሺ ጊዜ ኢትዮጵያ ! ኢትዮጵያ ! ቢል ልንዘናጋ ባልተገባን ነበር ::

ዛሬ ላይ ጭምብሉ ተገፎ ማን መሆኑን አይተናል፤ እስከ ኩላሊቱ ግልጥልጥ አድርገን ማንነቱን ስለተረዳን፤ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ስም እየማለ፤ የሚያጃጅለው እራሱንና መሰሎቹን ብቻ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል:: 

ሰሞኑንም ደግሞ « ዋልታ ረገጥ፤ ጽንፍ የረገጡ፤ – የአማራው ሸኔ ፤ የኦነግ ሸኔ » ……. ወዘተ. የሚል ዲስኩሩን አሰምቶናል :: በመሠረቱ ወደ ወላይታ የሄደው፤ የዳቦ ፋብሪካ ለመመረቅ መሆኑ ተነግሯል :: እግረ መንገዱንም፤ ትከሻ ለትካሻ ለሚተሻሻቸው፤ የቅርብ ሌቦቹ፤ ባንክ ዘራፊዎቹን የኦነግ ሸኔን ጨምሮም ሊሆን ይችላል፤ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ስለሌለ፤ በህግ እንደማይዳኙ ነግሯቸዋል::                 እኛን ያስደመመን፤ በወላይታው ዳቦ ውስጥ የተጠቀለለችው፤ « የአማራው ሸኔ ! » የምትለዋ መርዝ ፤ስትሆን፤ የምታነጣጥረውስ እነማን ላይ ነው? የሚለው ነው ጥያቄያችን::

ይህ አባባል « ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ » የሚለውን አገራዊ ብሂል ያስታውሰናል ::  ጉዳዩን ጠለቅ ባለ ሁኔታ ለመዳሰስ፤ አንባቢዎቼ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እያነሱ እንዲወያዩበት እጋብዛለሁ:: 

ይህን አባባል፤ ለምን አሁን መናገር ፈለገ ? በምን ምክንያት ? እነማንን ተማምኖ ? ከነማን ጋር ሆኖ ሊፈጽመው ?  መቼና  እንዴት ? የሚሉት ሲሆኑ፤ በበኩሌ ዐብይ አህመድ « የአማራው ሸኔ ! »ብሎ ሲናገር እማን ላይ ነው ያነጣጠረው ?! የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፤ ያለፉትን የዐብይ አህመድ ማኬያቬላዊ  ድርጊቶቹን፤ በጥሞና በቅደም ተከተል በመዳሰስ ለመመለስ እሞክራላሁ:: 

  1. ጀነራል አሳምነው ጽጌን፤ ዶ/ር አምባቸውንና ሌሎቹን የማስገደል፤ ሴራውን ጠንስሶ ሲያበቃ፤ የድርጊት ትዕዛዙን ለመስጠት፤ ወሎ ሄዶ ያደረገውን ንግግር አስታውሱ :: « የምንሰጣችሁን ባጀት፤ ለወታደር ስልጠና : ትጠቀሙበታላችሁ………… »ወዘተ. :: ከዚያ በኋላ የሆነውን፤ ሁላችሁም ስለምታውቁት ጊዜ አላባክንም ::
  1. ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ጓደኞቹ፤ የባልደራስ አባላት፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ፤ ውጥር አድርገው ሲይዙት፤ እስክንድርን « ጦርነት እንከፍታለ »ብሎ መናገሩን አስታውሱና፤ አሁን በአዲስ አበባ እየተደረገ ያለውን አጢኑ::  
  1. የኦሮምያን ባንዲራ፤ በአዲስ አበባ ት/ ቤቶች ውስጥ መሰቀል፤ ህዝብ በመቃወሙ፤ በፓርላማ ውስጥ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ደሙ እየፈላ : ስሜቱን መቆጣጠር እስቲያቅተው ድረስ፤ ከአንድ የአገር መሪ በማይጠበቅ መልኩ « አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ኦሮሞ ጠል ሃይሎች …. አሉ ! » ብሎ በመናገር፤ ህዝብ፤ እርስ በራሱ እንዲተላለቅ አውጆ ፤ ብዙ ወገኖቻችን እስካሁን ድረስ እያለቁ፤ እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ናቸው ::
  1. በወለጋ፤ በሸዋ፤ በአርሲ፤ በወሎ፤ በራያና አፋር፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በኦነግ ሸኔ  ህይወታቸው ለተቀጠፈ የአማራ ነገድና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን፤ እህቶቻችን፤ አባትና እናቶቻችን እንዲሁም ሕፃናት፤ እልቂት ቅንጣት ያህል ሳይጸጸት « ሰው እየሞተ : ችግኝ አይተከልም የሚለን ጠላት ነው ! አስከሬኑ ጥላ እንዲኖረው: የሞተበት ቦታ ችግኝ እንተክላለን » በማለት ሲናገር መስማት፤ ይህ ሰው በሰዎች ህይወት መጥፋት የሚደሰት፤ ነጮቹ « ሳዲስት » የሚሉት ፍጡር እንደሆነ አስመስክሯል :: 
  1. አሁን ደግሞ፤ ወደ ወላይታ በመሄድ፤ በተጋገረ ዳቦ የተለወሰ መርዙን፤ ለህዝብ ጠቅልሎ ሲያጎርስ : « የአማራው ሸኔ ! » በማለት፤ በብዙ ባንኮች ዘረፋና ብዙ የአማራና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን በመፍጀት ከሚታወቀው፤ « ኦነግ ሸኔ ጋር »  ፋኖን « የአማራ ሸኔ ! » ብሎ በመወንጀል፤ በማሰርና በማሳደድ፤ የአማራውን ህዝብ ለመፍጀት ወስኗል :: 

እራሱ ዐብይ አህመድንና መሰሎቹን ጨምሮ፤ በህወሃት ተጠራርገው ከመጥፋት፤ ወይም ከመሰደድ፤ ከአገር መከላከያና ከአማራው ልዩ ሃይል ጋር በመተባበር፤ አገርን ከትልቅ አደጋ የታደጉ፤  የህዝብ ልጆችን ለማጥፋትና፤ የአማራውን ነገድ፤ ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ፤ ከቀድሞ አሳዳሪያቸው፤ ከህወሃት ጋር ሆነው፤ ለመዝረፍና ለመፍጀት የያዙትን ዕቅድ ነግሮናል :: 

በአሜሪካና፤ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የገንዘብ ዕርዳታ፤ የጦር መሳሪያና፤ የሳተላይት መረጃ እየታገዙ፤ (በደርግ ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል እንዳረረጉት) ዛሬም ኢትዮጵያን አፈራርሰው፤ ታላቋን ትግራይና ፤ በእነሱ አጠራር፤ የኦሮምያ ኢምፓዬር  የሚሉትን፤ ለመመስረት፤ የሚደረግ አኩይ ተግባር ነው ::

ኢትዮጵያን ለአፍ ማሟሻነት እየተጠቀሙ ፤ በዘርና በጎሣ ፍቅር በማበድ ፤ የፖለቲካ ቁማር መቆመር ይሏችኋል ይች ናት !!

ምዕራባውያን፤ በተለይ የቀድሞ ቅኝ ገዢ የአውሮፓ አገራት፤ እስካሁን ድረስ፤ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ባደረሰችባቸው ሽንፈት፤ ቂማቸውን እንደቋጠሩ ናቸው:: የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በአንድነት ለአገሩ ዘብ ከቆመ፤ በጦርነት እንደማያሸንፉት ስለሚያውቁ፤ ከመሃከላችን፤ ተጣመው ያደጉ፤ ቡድኖችን በመመልመል፤ በማሰልጠን፤በማስታጠቅ፤ የገንዘብና የሳተላይት፤ ድጋፍቸውን በመስጠት፤ ኢትዮጵያን ለመበታተንና ህዝቧን ለማዋረድ እንቅልፍ አይወስዳቸውም :: 

ምክንያቱም፤ ምዕራባውያን ለአፍሪካ ህዝብ ነፃ መውጣት፤ ተምሳሌት የሆነች፤ ኢትዮጵያን ማፈራረስ ከቻሉ፤ አፍሪካን ዳግም ቅኝ ለመግዛት፤ መንገዱ ክፍት ነው:: ምዕራባውያን፤ ቀድመው ቅኝ የገዟቸውን የአፍሪካ አገራት፤ ቅኝ የገዙት አገራቸውን ብቻ ሳይሆን፤ አይምሯቸውንም ጭምር ስለሆነ፤ ተመልሰው ቅኝ ለመግዛት ቢመጡ፤ በምንና እንዴት ቆልፈውባቸው፤ ቁልፉን ይዘው እንደወጡ ስለሚያውቁ፤ በምን ብልሃት ተመልሰው ከፍተው ቅኝ እንደሚገዟው ያውቃሉ ::

ለዚህ ነው ምዕራባውያን ህወሃትና፤ ብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) ተብዬ ጠማሞችን፤ እንደ መሣሪያ  በመጠቀም፤ ኢትዮጵያን ለማፈራረስና የህዝቧን ቅስም ሰብረው ለማዋረድ፤ በህወሃት 27 ዓመታት አሁን በብልጽግና፤ (ኦህዴድ/ኦነግ/) ደግሞ 4 ዓመታት እያስፈጁን ያሉት::

ምዕራባውያን፤ ስለ ሞራል ልዕልና ለሌላው ሲሰብኩ እንጂ፤ ለራሳቸው በተግባር ሲፈጽሙ አይታዩም:: መመሪያቸው፤ የእኛ የእኛ ነው፤ የሌሎችም የእኛ ነው፤ የሚል የቅሚያና የዘረፋ ስልት መሆኑን፤ የባሪያ ንግድና፤ የቅኝ ገዢነት ዘመናቸው ይነግረናል:: በተቃራኒው: የእናንተ የእናንተ ነው፤ የእኛ ደግሞ የራሳችን ነው፤ ብሎ አገሩንና ሕዝቡን ከዘረፋ የሚከላከል፤ ጠንካራ የጥቁር ህዝብ መሪ ሲያጋጥማቸው፤ በቅጥረኞች ያጠፉታል፤ ወይም ከያሉበት ተጠራርተው ይቦጫጭቁታል::

ወገኖቼ ! የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን፤ የውሃውን ጦርነት ካወጁብን ሰነባብቷል:: የነጠፈ አይምሮ ያላቸው የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ የገዛ ወገኖቻቸውን በመጨፍጨፍ፤ የአንድ ጎሣ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት፤ ለመመስረት ሌት ተቀን ይባጃሉ:: 

የውሃው ጦርነት፤ መርጦ የሚያስቀረው ጎሣ አይኖርም፤ ጠራርጎ የሚያጠፋው፤ ሁላችንንም ነው :: ሁላችንም አብረን ላለመጥፋት: ሁላችንም በአንድነት መነሳት ይኖርብናል ::

ጊዜው የሚጠይቀው፤ በመቻቻል፤ አብሮነትን አጠናክሮ፤ በአንድነትና በእኩልነት በኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ ከፍ ብሎ በመገማሸር፤ ለጋራ እድገትና ደህንነት አብሮ ዘብ መቆም መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል::  

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

ነፃነት፤ እኩልነትና ወንድማማችነት ይለምልም !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !! 

ታኅሣሥ 21 ቀን 2015 ዓ.ም (29/12/2022 ) እኤአ 

Filed in: Amharic