የጠቅላይ ሓሳዩን ጓደኞች እንተዋወቅ!!
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ዲያቢሎስ በሙሉ ኃይሉ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ የሚከታተል ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ይህን የሚክድ ጤናማ ሰው ይኖራል ብዬም አልገምትም፡፡ ዋናው ጤነኞች ስንት ይሆናሉ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
ወደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ማለቴ ሚኒስትራቸው ጓደኞች ከማምራታችን በፊት እንደተለመደው ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታና ስለምትገኝበት የመከራ አዘቅት ጥቂት እንበል፡፡
ዲያቢሎስ እያዋዛ ሀገራችንን የለዬላት የደም ባሕር እያደረጋት ነው፡፡ እንደምገምተው በአሁኑ ወቅት የመለስ ዜናዊን የተኮነነች ነፍስ ጨምሮ ታላላቅ የሣጥናኤል የሲዖል ባለሟሎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የመጨረሻውን አርማጌዴዖን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ በአራቱም አቅጣጫ ብናይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ፍም እቶን ላይ ተጥዳለች፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ እንዲሁም ከሞላ ጎደል በሁሉም ጠቅላይ ግዛቶቿ ሶዶም ወገሞራዊ ነበልባል እየተንቀለቀለ ነው፡፡ በውጤቱም በሁሉም የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በግልጽም ሆነ በእጅ አዙር የተቀመጡት አክራሪ ኦሮሞዎች ከዋናው ቤተ መንግሥት እስከ ክልል መስተዳድር እየተናበቡና እዚያና እዚህ በደስታ እየቦረቁ አማራን በመጨረስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኦነግ ቅን ታዛዥ የሆኑት ብአዴኖችም ሆዳቸው አይጉደል እንጂ እንመራዋለን የሚሉትን አማራ በአቢይና ሽመልስ ቅልብ ጦር ለማስፈጀት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሰሞኑን ሰሜን ሸዋ ውስጥ የአማራን ልዩ ኃይል በተኛበት በኦነግ ማስጨፍጨፋቸው አንዱ ማስረጃ ነው፡፡ አማራም በተዘረጋለት ወጥመድ ዘው ብሎ በመግባት ወያኔ የጠነሰሰለትንና ኦነግ/ኦህዲድ የተረከበውን በአማራ ላይ የታወጀ ጄኖሳይድ (የዘር ፍጂት) ማስተናገዱን ቀጥሎበታል፡፡ እርግጥ ነው መጨረሻው ድሉ ለአማራና አማራዊ ኢትዮጵያውያን መሆኑ ባይጠረጠርም ለጊዜው ግን የተዘረጋው ኦነጋዊ ሞራ የሚያስነብበን ሌላ ነው፤ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ተጠምዶ፣ ወደ አማራነት ነገዳዊ ስሜትም አልወርድም ብሎ በብዛትም በዕውቀትም ከማንም ሳያንስ እንዲሁ እያለቀ የሚገኘው አማራ በመሆኑ የዚህን ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ተፈጥሮ የሚጋራ ሌላው ጎሣና ነገድ ሁሉ በመጨረሻ ከዚህ የተገፋ ሕዝብ ጋር በመተባበር ጠላቶቹን ድባቅ እንደሚመታ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አዚሙ ሲለቀው፣ መከራው እስከአንጀቱ ሲዘልቀው የሚፈጠረውን ማየት በርግጥም ያጓጓል፡፡
ፖለቲካውን የተቆጣጠሩት ኦነጎች ሃይማኖቱንም ለብቻ ለመቆጣጠር ባቀዱት መሠረት ይሄውና ያላንዳች ሀፍረት ድፍን ማይማንን በድፍረታቸው፣ በዘር ሐረጋቸው፣ በቋንቋቸውና በሥልጣንና ገንዘብ ወዳድነታቸው መሥፈርት በመመልመል ጳጳስና ፓትርያርክ በሚል ሹመት አንበሽብሸው ኦርቶዶክስን እየበታተኗት ነው፡፡ ከደነቆሩ አይቀር ታዲያ እንደዚህ ነው፡፡ ጥጋብ ኅሊናን ያሳውራል፡፡ ትናንትን ያስረሳል፡፡ ነገን ያርቅና የሽዎችን ዕድሜ በመስጠት በዕብሪትና ትምክህት ያደነዝዛል፡፡ እንደጥጋብ መጥፎ የለም፡፡
ኦነግ/ኦህዲድ ጥጋቡን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ የጠገበ ደግሞ ከተራበም በከፋ እንደሚታዘንለት ብሂሉ አስቀድሞ አጽድቆታል፡፡ የጠገበ የሚናገረውን ብቻ ሳይሆን የሚያደርገውንም አያውቅም፡፡ ዕውቀት ላይ ያልተመረኮዘ ጥጋብ ደግሞ ገደል ይከታል፡፡ ለጊዜው ግን በሚያጥበረብር ጊዜያዊ ድል ያጃጅላል፡፡ አርፎ የተኛውን አማራ ከወዲያ ከወዲህ የሚጎነታትሉትና ዘሩን ለማጥፋት የሚራወጡት ተረኛ ኦሮሞዎች መጨረሻቸውን ያብጅላቸው እንጂ አካሄዳቸው እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ከወያኔ አለመማራቸው ደግሞ የድንቁርናቸውንና የጅልነታቸውን ለከት-የለሽነት በጉልኅ ያመለክታል፡፡ የወያኔን ጥጋብ መጨረሻ ያዬ ከወያኔም ብሶ እንዲህ ሲቀብጥ መታዘብ ከማሳዘን አልፎ የሰውን ልጅ ተፈጥሮ እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ውሻና ድመት እንኳ ከውሻና ከድመት ይማራሉ፡፡ የነዚህ ድንቁርና ግን ይለያል፡፡
እንደእውነቱ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ አትጠፋምም፡፡ ከዶፉ ዝናብ የሚተርፈውን አንድዬ ይወቀው እንጂ ከጎርፉና ከውርጅብኙ በኋላ ኢትዮጵያ ከነሙሉ ግርማ ሞገሷ ትነሳለች፡፡ በምን መልክ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ዓለምንም ትመራለች፡፡ አዲስ ነገር አልተናገርኩም፡፡ በተደጋጋሚ ሲነገር የተሰማውንና ብዙዎች እንደቀልድ የሚወስዱትን ነባር የአበው ቃል ለማስታወስ ያህል ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምትነሳ መሆኗ እንዳለ ሆኖ መጥፋት ካለባትና የዓለምም ፍጻሜ በርግጥም ደርሶ ከሆነ ከዚህ ጊዜ የበለጠ የትንቢቶች መገጣጠም ታይቶ እንደማያውቅ መመስከር ይቻላል፡፡ ሌሎች ሀገራት ጣጣቸውን ጨርሰው የምጽዓትን ቀን የመጨረሻ ፊሽካ እየተጠባበቁ እንዳሉ ሀገራቱ ከሚመሩት ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሕይወት መገንዘብ እንችላለን፡፡ በብዙ ሀገራት ጳጳሳትና መነኮሳት ሳይቀሩ የግብረ ሶዶም ኃጢኣቶች ሰለባ ከሆኑና እንዲያውም አብያተ ክርስቲያን ወደ ጭፈራ ቤትና ወደ ሙዚየምነት ከተቀየሩ ቆየት አሉ፡፡ በብዙ ሀገራት የእግዚአብሔርን ስም መጥራት እንደፋራ የሚያስቆጥርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ቁሣዊነትና ኢ-አማኒነት ፋሽን ከሆኑ ሰነበቱ፡፡ ኢሉሚናቲ በመባል የሚታወቁትና በግልጽም በተዛዋሪም የዓለማችንን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው በመንግሥታት ጀርባ በተለጠፈ ሥውር አንቀልባ ውስጥ ሆነው ምድርን የሚዘውሯት ኃይላትም ሰዎችን ከፈጣሪያቸወ ጋር አለያይተው ዓለማችንን በሞራልም በምግባርም ባዶ እያደረጓት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ያህል የማያስጨንቋቸው ሌሎች ሀገራት እንዳሉ ቢገመትም በወጥመዳቸው ሳትገባ የቀረችውና በታሪኳና በሃይማኖቷ ጠንክራ ዲያቢሎስን ሌት ከቀን እንቅልፍ ትነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ እርሷንም ወደጨለማው ግዛታቸው ለማካተት በተለይ ልጃቸውን አቢይ አህመድን ወደ ሥልጣን ካመጡ ወዲህ በተወሰነ ደረጃ እየተሳካለቸው ስለመሆኑ ብዙ ምልክቶች ይታያሉ – ለጊዜው ቢሆንም አልተሳካላቸውም ማለት አንችልም፡፡ በዚህ ዘመን ከነሱ አመራር ውጪ የሚንቀሳቀስ ኃይል የሚገጥመው መከራና ፍዳ ቀላል አይደለም፡፡ ራሽያን ማየት በቂ ነው፡፡ የቬንዞላው መሪ ሁጎ ሻቬዝ የተገደለበትንም ምክንያት መመርመር ተገቢ ነው፡፡(የጆን ፐርኪንስን መጽሐፍ አንብብ ከፈለግህ! Confessions of an Economic Hitman)) በሀገራችንም ጥቂቶች ብዙኃንን እንዴት አንቀጥቅጠው እንደሚገዙ ማየት ይቻላል፡፡ በ40 እና በ50 ሚሊዮን የሚገመተው አማራ ድብልቅልቁ እንዲወጣ ተደርጎ በራሱ ሰዎች ሳይቀር ወደመቅ እየወረደ የመታየቱ ምሥጢር የሚገናኘው ከዚህ ዓለም አቀፍ ሰይጣናዊ የጥፋት ኃይል ነው፡፡ እንጂ ኦነግም ሆነ ሕወሓት ወይም አጋሰሱ ብአዴን ከሰሜን ሸዋ ጦረኞች የሚያልፍ ኃይል አስፈልጓቸው አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለውና የወደፊቱ አስፈሪ ጨለማም የተጋረጠብን ንግርቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ የተከበብነው በሐጎስና በቶሎሣ ወይንም በከርሳም ሎሌዎቻቸው አገኘሁና ደመቀ ብቻ ሣይሆን በሉሲፈርና የርሱ ታዛዥ በሆኑት በነኤሎን መስክ፣ በነአንቶን ሌቪና አድሪ ኖርተን የጨለማው ግዛት አባላትም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የገጠመን ጦርነት ከሕዝብ ብዛት አኳያ የስንፍናና የፍርሀት አድርገን ልንወስደው እንችል ይሆናል እንጂ ረቀቅ ያለና መናፍስትም የሚሣተፉበት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ መፍትሔው ግን ቀላል ነው፡፡ ተመጣጣኝ ጥረት ማድረግ ብቻ፡፡ ከነሱ የበለጠ ትኩረት መስጠት፡፡ አለመፍራት፡፡ የፈጣሪን ጦርና ጋሻ መታጠቅ፡፡ ጎልያድን በሚመስሉ ግን በቀላል ንፋስ በሚበተኑ የአጋንንት መንጋዎች ላይ ዳዊታዊ ወንጭፍን መጠቀም፡፡ የጠላትን ኃይል አክብዶ አለማየት፡፡ በቃ፡፡
ልድገመው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ጊዜ ታልፈዋለች፡፡ ስታልፍና ለማለፍ ስትጥር ግን ብዙ ዋጋ ትከፍላለች፡፡
ተመልከት፡፡ ፖለቲካው በማን እንደተያዘ እናውቃለን፡፡ ለማስታወስ ያህል አንዳቸውም ሀገራዊ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የሌላቸው ሆዳሞች፣ በሀሰት ዲግሪዎች የተንበሸበሹ ማይማን፤ ከ6ኛና ከ7ኛ ክፍል ያላለፉ ደናቁርት፣ ከሆዳቸው በቀር ዘመድ የሌላቸው ዓሣሞች፣ ፍትህን በገንዘብና በዘረኝነት እንዳሻቸው የሚያዛቡ ዳኞች፣ በሙስና ህግንና መመርያን የሚጥሱ መለዮ ለባሾች፣ ሀገርን በመሸጥ ጭምር ሀብት የሚያካብቱ ሚኒስትሮችና ኮሚሽነሮች ወዘተ. የሚመሯት ሀገር የትም አትደርስም ብቻ ሳይሆን በየቀኑ ወደመቀመቅ እንደምትነጉድ ለመገንዘብ ከዐይናችን በላይ ዋቢ አያስፈልገንም›፡፡ በፖለቲካው ተስፋ ስንቆርጥ ወደሃይማኖቱ መዞራችን ደግሞ አግባብ ነው፡፡
ሃይማኖቱን ስናይ ሁሉም በሚባል ደረጃ በኃጢኣትና በወንጀል ድርጊት የጨቀዬ ነው፡፡ የትኛው የሃይማኖት መሪ ስንት ሀብት አካበተ፣ ከስንቷ ዲቃላ ወለደ የሚለው የቁጥር መበላለጥ ካልሆነ በቀር ሁሉም በኃጢኣት ሥር የሚርመጠመጥ ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ ማንም በማንም ላይ ወቀሳ ለመሰንዘር የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ለምሣሌ ይህ ሁሉ ግፍና በደል በተለይ በወለጋና በትግራይ እንዲሁም በሸዋና በሻሸመኔ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ልክ እንደአቡነ ጴጥሮስ ግፈኞችን አውግዞ የሰማዕትነትን መለኮታዊ ፀጋ ለመቀበል አንድም ጳጳስ አልደፈረም፡፡ በልማዳዊው አገላለጽና እንደውነቱም ከሆነ አንድ ሰው መነኮሰ ማለት ሞተ ማለት እንደመሆኑ የሞተ ሰው ምንም የሚፈራው ነገር ሊኖር ባልተገባ ነበር፡፡ …. ስለሆነም የጠፋነው ሁላችንም ነን፡፡ የጠፋነው ከአናት ጀምሮ ነው፡፡ የጠፋነው የቃየልን ወንድምነት ሁላችንም በመጋራታችን ነው፡፡ እናም ንስሃ መግባት ያለብን ሁላችንም ነን፡፡ ክፉ ነገር የታዘዘብን ሁላችንም ከእግዚአብሔር መንገድ በመውጣታችን ነው፡፡ ከፈጣሪ ትእዛዝ የወጣ ደግሞ መልካም ነገር አይጠብቀውም፡፡ አመልካች ጣታችንን እንመርምራት፡፡ ይህን ስል ግን ለቅጣት የተላኩብን የእነአቶ አካለወልድ (የፕትርክና ስሙ ማን እንደሆነ ረሳሁት) መፈንቅለ ሲኖዶስ ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ይህ አስቂኝ ድራማዊ ክስተት መጋረጃው ሲዘጋ ይበልጥ በሣቅ የምንፈነዳበት አስገራሚ ትራጂ-ኮሜዲ ነው፡፡
አናት ከተበላሸ ግርጌም ይበላሻል – በፖለቲካውም በሃይማኖቱም፡፡ በሀሰትና በማስመሰል በዓለም የአንደኝነትን ሥፍራ የሚይዘው ጠ/ሚኒስትር ተብዬው ግለሰብ ከትምህርት ደረጃው ጀምሮ ብዙ ይወራበታል፡፡ በ94 ዲግሪ ወስዶ በ96 12ኛን እንደጨረሰ ይነገራል፡፡ ነገሩ ሁሉ “አንበሣ ምን ይበላል?” ቢሉ “ተበድሮ”፤ “ምን ይከፍላል?” ቢሉ “ማን ጠይቆ” እንዲሉ ሆነና ጉዟችን ሁሉ የጭቡና በማኅበራዊ ዕብደት የታጀበ ሊሆን በቃ፡፡ ጨካኝነቱንና ፀረ-አማራነቱን በተግባር እያየነው ስለሆነ መስካሪ አንፈልግም፡፡ ዋሾነቱንና አስመሳይነቱንም በግልጽ የምናይለት፣ እርሱ ግን አብዝቶ የሚኮራበት አጋንንታዊ ባሕርይው ነው፡፡ “ኳስ አበደች” ማለት አሁን ነው ታዲያ፡፡
በመሆኑም በዚህ በብዙ የተምታቱ ስብዕናዎች የሚሰቃይ ሰውዬ ሥር የምትማቅቅ ሀገር እንደነ “ነቢይ” ደምሳሽና እንደነ “እህተ ማርያም” የመሳሰሉ አጭቤዎች ይህን ገልቱ ዜጋ ኪሱን ሲሞልጩትና አእምሮውን ባዶ ሲያደርጉት ብናይ በማንም ልንፈርድ አንችልም፡፡ የዓሣ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ አቢይ አህመድ ዋሾና አጭበርባሪ ሆኖ ሳለ ቸርቹ ውስጥ የሰበሰበውን ጅላንፎ “በባንክ ደብተርህ 10 ሽህ ብር ኢየሱስ ጨምሮልሃል፤ ላቤን የተረግሁበትን ሶፍት ብትበላ ትፈወሳለህ፤ ማታ ነይና ጸልየልሽ ታረግዣለሽ….” እያለ በሦስትና በአራት ዓመት ሕጻን አእምሮ ምዕመናኑን ቢያጃጅል የሚፈረደው በማንም ሳይሆን በሚጃጃለው ገልቱ ዜጋ ነው፡፡ በየቦታው የሚደረገውን ስንሰማ ኢትዮጵዊ ሆኖ መፈጠርን እንጠላለን፡፡ እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ላይ ነን፡፡ በሃይማኖት ስም የሚፈጸመው ማጭበርበር ገደቡን አልፎ በተለይ አሁን አሁን መንግሥት የለንም እንጂ የመንግሥት ያለህ ያስብላል፡፡ በበኩሌ የዘመኑን ማለቅ የምረዳው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ በሃይማኖት ረገድ ህጸጽ መኖሩን ስጠቁም ደግሞ በሁሉም ሃይማኖቶች ማሉቴ ነው፡፡ ከአንድ ዝቅተኛ ገቢ ካለው ደብር ከፍተኛ ገቢ ወዳለው ደብር ለመዛወር አንድ ቄሰ ገበዝ ለሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣን የሚከፍለውን ጉቦ ብትሰሙ ታብዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ቅርጽና ይዘቱ ይለያይ እንጂ በሁሉም ሃይማኖት የተንሠራፋውንና እግዚአብሔርንም ፊቱን እንዲያዞርብን የሚያስገድደውን ንቅዘትና ነውር ቆጥረን አንዘልቀውም፡፡
እህተ ማርያምና “ፍቅርሲዝም” የሚባልን አዲስ እምነት ዘባራቂው ወጣት ደምሰሽ ግን ለጠቅላዩ በጣም የሚቀርቡት የነፍስ ጓደኞቹ መሆናቸውን ሳልጠቅስ ይህችን ጽሑፍ መጨረስ የለብኝም፡፡ ለመዝናናት ያህል እነዚህን ሁለት አጭበርባሪ የሰይጣን ልጆች ስመለከት በዓይነ ኅሊናየ የሚታየኝ አባታቸው አቢይ አህመድ ነው፡፡ ራሱን ቁጭ አድርጎ ነው የወለዳቸው – በመንፈስ፡፡ የነሱ ቀላል ነው – የሚያጃጅሉት ጥቂት ነውና፡፡ የአቢይ ግን ሀገርን የመምራት ያህል ትልቅ ኃላፊነትና ልጓም በመያዙ እንጦርጦስ እየከተተን ነው፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ እነእስራኤል ዳንሳ፣ እነአዩ ጩፋ፣ በሁለት ካራ በሊታው ዳንኤል ክብረት፣ ወዘተ. የዚህ አበሾዋም ጠ/ሚኒስትር የቅርብ ጓደኞችና የዓላማው ተጋሪዎች ናቸው፡፡ መጪውን ጊዜ በጣም ፍሩ ታዲያ፡፡ ዕብድና ወፈፌ ሀገር ሲመራ ዕዳው ብዙ ነው ወንድሞቼና እህቶቼ፡፡አብዝተን እንጸልይ፡፡ መከራው በቶሎ እንዲያልፍ፤፣ የቅጣቱ መጠን ለዘብ እንዲል፣ የተደበቀው ወርቃማው መንግሥት በቶሎ እንዲገለጥና የጉግማንጉጉ መንግሥት ወደመጣበት የጥልቁ ጨለማው ግዛት እንዲመለስ ሁላችንም በየምናምንበት የሃይማኖት ራስ ተንበርክከን እንለምን፡፡ ወቅቱ የአሥረሽ ምቺው ሳይሆን የአርምሞና የሱባኤ ነው፡፡ በተቻለን መጠን ከቡረቃና ከጮቤ ረገጣ እንታቀብ፡፡