>

ጭራቁ የመጨረሻውን ካርድ መዟል (ከይኄይስ እውነቱ)

ጭራቁ የመጨረሻውን ካርድ መዟል

ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለሰይጣን ወይጐይይ እምኔክሙ፡፡ ያዕ.4÷7

(እግዚአብሔርን እሺ በጄ በሉት፤ ሰይጣንን እምቢ ወግድ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡)

ከይኄይስ እውነቱ

በእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ አባትና እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እኅቶቼ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን የመጨረሻ ምሽጋችን የሆነውን ሃይማኖት ሊያጠፋ፣ በሃይማኖት ያለንን ጽኑ ተስፋ ሊነጥቅ ያሰፈሰፈ ጭራቃዊ አገዛዝ ከደጃፋችን ቆሟል፡፡ የአገራችን ኢትዮጵያና የጋራ ቤታችን ዋና ዓምድ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት (ርትዕት) ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዕጣ ፈንታ÷ዕድል ተርታ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የሚገኙበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስላል፡፡ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሳልገባ አገራችን ኢትዮጵያና ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ላይ ያነጣጠረው ጥቃትና ጥፋት ታሪካዊና ድንበር ዘለል ምክንያቶች ያሉት፣ በምዕራባውያን አሰማሪነት በባዕዳን ሚሲዮናውያን እና በውስጥ ቅጥረኞችና ባንዳዎች አስፈጻሚነት ለዘመናት በቅንጅት ሲፈጸም የቆየ መሆኑን በመጠቆም ወደዛሬው ርእሰ ጉዳዬ አመራለሁ፡፡

ሰሞኑን መላው የተዋሕዶ ልጆችን ያሳዘነና ያስቆጣ የነውሮች ሁሉ ቁንጮ በወንጀል ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡ በኢኦተቤክ ላይ የተፈጸመው አሳፋሪና ሕገ ወጥ ድርጊት ጭራቁ ዐቢይ አሕመድና የወንጀል ድርጅቱ ኦሕዴድ እንዲሁም ለሽብር ዓላማ ያሰማራቸው ኦነጋዊ ሠራዊት እውነተኛ ፍላጎታቸውንና ማንነታቸውን በይበልጥ ያጋለጠ ነው፡፡ ክስተቱ እንደ ድንገተኛ ደራሽ የመጣ አይደለም፡፡ ባለፉት 32 ዓመታት ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ ባለፉት 5 የሰቈቃ ዓመታት በዕቅድ ሲሠራበት የቆየና የሚጠበቅ ነው፡፡ የወንጀል አገዛዙ በተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስርጎ ያስገባቸውን ነውረኞችና ካድሬዎች ‹መነኮሳት› እና ‹ካህናትን› ተጠቅሞ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይጣናዊ በሆነ በጐሠኛነት አስተሳሰብ ነጥቆ ለመውሰድ ሙከራ አድርጓል፡፡ በመድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ባለን ትምክህት አይሳካለትም፡፡ እኛም ልጆች ደግሞ ድርሻ ያለን መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስም የቤተክርስቲያንን ብሎም የአገርን ህልውና ለማስከበር በሠላሳ ሁለት ዓመታት ውስጥ ያልታየ ተገቢ፣ ታሪካዊ፣ ሕገ ቤተክርስቲያንን ያስከበረ፣ ከባለቤቱ የተሰጠውን አደራ የጠበቀ እና የቤተክርስቲያኒቱን አባላት፣ አኀት አብያተ ክርስቲያናትን እና ደጋፊዎቿን ሁሉ ያኮራ – የአገር አፍራሾች ተልእኮ ለማስፈጸም የተንቀሳቀሱትን ነውረኞች – ሥልጣነ ክህነታቸውን ገፎና አውግዞ ከቤተክርስቲያኒቱ አንድነት የለየበትን – ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ 

ይሁን እንጂ በጭራቁ የሚመራው የጥፋት ተልእኮው አስፈጻሚዎችም ሆኑ ፈጻሚ ቅጥሮችን ያነሣሣው ሰይጣናዊ መንፈስ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለመቀልበስ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ባየ ጊዜ የመጨረሻ ቀስትና ጦሮቹን ለመወርወር ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለጭራቁ የሆኑ ቡድኖችን በማቋቋም አገዛዛዊ ሽብር ለመፈጸም አሰማርቷል፡፡ በዚህም መሠረት በብፁዐን አባቶቻችን፣ የሕገ ወጦቹን ውሳኔ አናስፈጽምም ባሉ በየደረጃው በኃላፊነት በሚገኙ አገልጋይ ካህናት ላይ ግድያ ለመፈጸም እንዳቀዱ መረጃው ከደረሳቸው ወንድሞች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የዚህ ሽብር ድርጊት የመጀመሪያው እንቅስቃሴ በጅማ የተሠራ አዲስ ካቴድራል ቤተክርስቲያንን ቅዳሴ ቤት ለማክበር በ20/05/2015 ዓ.ም. የተጓዙትን ሊቀ ጳጳስና ረዳታቸውን በማገትና ወደ አ.አ. በመመለስ፤ በይቅርታ የተመለሱ አባትን አፍኖ በመሰወር ተጀምሯል፡፡ ዓላማውም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን በማስፈራራት ለድርድር እንዲቀርቡ በማድረግ ውሳኔአቸውን ለማስቀየር ያለመ ነው፡፡ ይህ የጥፋት አካሄድ ከፍተኛ አገራዊ ቀውስ የሚያስከትልና የወንጀል ሥርዓቱንም ፍጻሜ መጀመሪያ የሚያቃርብ ይመስለኛል፡፡ የማይነካውን ነክተዋልና፤ የማይደፈረውን ደፍረዋልና፡፡ ጥፋት የሚመስለውን ጉዳይ ለበጎ የሚለውጥ እግዚአብሔር አምላክ ጥበቡ አይመረመርም፡፡ ምንም እንኳን ተካክለን ብንበድልም ባለቤቱ የሚያውቃቸው በርካታ ቅዱሳን አባቶቸና እናቶች ያሉባት ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንደማይተዋት ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ 

በርእሴ እንደገለጽሁት የወንጀል አገዛዙ አለቃ የመዘዘው የመጨረሻውን ካርድ ነው፡፡ የአገር ዋልታና ካስማ የሆነችውን ተዋሕዶ ቤክ ለጐሠኛነት በማስገበር የግብር አባታቸው ወያኔ የፈጠረላቸውን ‹ኦሮሚያ› የሚባል ተምኔታዊ ‹አገር› በኢትዮጵያና በቤተክርስቲያኒቷ ፍርስራሽ ላይ እውን ለማድረግ ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች ምን እናድርግ? ለመጨረሻው ‹ፍልሚያ› መዘጋጀት ነው፡፡ ፍልሚያው ሥጋ ከለበሱ አጋንንት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ቤተክርስቲያናችን በሥርዓት ባለቤት የምትመራ በመሆኗ ሁሉ በሥርዓት ይሁን የሚለውን ቃለ እግዚአብሔር መሠረት አድርጋ ‹መንግሥት› ነኝ ለሚለው ነገር ግን የአገራዊው ምስቅልቅል ምንጭና ኃላፊ ለሆነው አገዛዝ የቤተክርስቲያኒቱን ሉዐላዊነት እንዲያስከበር፣ የተቃጣባትን ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ጥቃት እንዲያስቆም የምትጠይቀው ከአጥፊው መፍትሄ ፈልጋ አይደለም፡፡ ሥነ ሥርዓታዊ በመሆኑ እና ምናልባትም ለራሱ ህልውና ሲል አንድ ጊዜም ቢሆን እንኳን የመንግሥትነት ባሕርይ የሚያሳይ ከሆነ በሚል የሰለለ ተስፋ እንጂ፡፡

በነውረኞቹ የተፈጸመው ድፍረት የአገዛዙ እጅ እንዳለበት የቅርቡ ምስክር ለሕገ ወጦቹ መንግሥታዊ ጥበቃና የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ፤ ለኢኦተቤክ ደግሞ ሕዝብ ግብር የሚከፍለባቸውን መገናኛ ብዙኃኖች ከመንፈግ በተጨማሪ ከብፁዓን አባቶች ጥበቃን በማንሣት ተገልጾአል፡፡ ወረድ ብለን እንደምናየው ከዚህም ያለፈ የሽብርተኛነት ድርጊት ለመፈጸም ዐቅዷል፡፡

  ፍልሚያው ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ በማለት በማንአለብኝነት አብጠው ሊፈነዱ ከደረሱ፣ ያልተገባ ሥልጣንና ጐሠኛነት ከአእምሮአቸው የለያቸው፣ ይህም በፈጠረላቸው ሁሉ የኔ የሚል ለከት ያጣ ስግብግብነት ናላቸውን ያናወዛቸው ‹ዕብዶች› ጋር መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም ትልቁ መንፈሳዊ መሣሪያችን ጾምና ምሕላ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ለሰማዕትነት መዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡ ፍልሚያው ከዐላውያን (ከሃዲ ነገሥታት) አገዛዞች ጋር ነው፡፡ ፍልሚያው ዲያቢሎስ ከሚጋልባቸው ከዘመኑ ፈርዖኖች፣ ናቡከደነፆሮች፣ ዲዮቅልጥያኖሶችና ኔሮኖች (የጐሣ ጣዖት ከተከሉብን ኢሕአዴጋውያን) ጋር ነው፡፡ ባጭሩ ረቂቃን ብቻ ሳይሆኑ ሥጋ የለበሱ ግዙፋን ‹አጋንንቶች› ጭምር ነው፡፡ 

በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንዳስተማረን ሰይጣን አጋንንትን እምቢ ወግድ በማለት ከዚህች ከተቀደሰች ምድራችን ኢትዮጵያ ባጠቃላይ፤ ከኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በተለይ እንዲርቅ እንዲሸሽ ማድረግ ከእውነተኛ ተዋሕዶ አባቶቻችን በላይ  ባገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም የምንገኝ የእኛ ልጆቻቸው ኃላፊነት መሆኑን በሚገባ በመገንዘብ የተነሣብንን ጠላት መቃወም መመከት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከማሳወቅ ባለፈ ከየትኛውም አካል ፈቃድ የማያስፈልገውን ሀገር-አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ከርእሰ ከተማችን አ.አ. ጀምሮ በመላው አገራችን በተለመደ ኢትዮጵያዊ ጨውነትና ተዋሕዶአዊ ሥርዓት ማድረግ፤ ለዚህም የቤተክርስቲያኒቱን መዋቅር ተጠቅሞ ሰንበት ተማሪዎችን፣ ካህናትን፣ ቤተክርስቲያን ዕውቅና የሰጠቻቸውን ማኅበራት እንደ ታላላቅ የቤተክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ የዐደባባይ በዓላት ጊዜ እንደሚደረገው በማስተባበር መፈጸም ይቻላል፡፡ ሌላው ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት እንዲሁም በየገዳማቱ የሚገኙ ካህናት አባቶቻችንን መጠበቅ፤ ቅርሶችንና ሕንፃ ቤተክርስቲያንን ከአደጋ መጠበቅ፣ በቤተክርስቲያናችን ስም የሚነግዱ ሐሳውያን መምህራንን ማጋለጥ፤ የወንጀል ሥርዓቱ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ በሃይማኖት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በማድረግ የሚፈጽመውን ነውር ከጠቅላይ ቤተክህነት የውጭ ግንኙነት በኩል የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ሥራና ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በውጭ የምትገኙ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ለ5ቱ እኅት (ኦርየንታል) አብያተክርስቲያናት፣ ለተቀሩት ምሥራቅ ኦሮቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ ለዓለም አቀፉ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፤ ለተባበሩት መንግሥታትና በሥሩ ለሚገኙ የሚለከታቸው ድርጅቶች ፣ ለአፍሪቃ ኅብረት፣ ለአውሮጳ ኅብረት፤ ለኤምባሲዎች ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ጊዜያዊና ወቅታዊ መፍትሄዎች ሲሆኑ፤ ዘላቂ ችግሮቻችንና ተግዳሮቶቻችንን በሚመለከት ብፁዓን አባቶቻችን በሲኖዶስ ውሳኔአቸው እንደገለጹት ጥናትን መሠረት ያደረግ ዘላቂ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በመጨረሻም ከዚህ ሁሉ ሴራ በስተጀርባ የወንጀል ሥርዓቱ መኖሩ የዐደባባይ ምሥጢር በመሆኑ፣ አሁንም አባቶቻችን በውስጣቸው ተሰግስገው የሚገኙ የአገዛዙ ካድሬዎችንና የሌላ እምነት ተወካዮችን ለይቶ ሕገ ቤተክርስቲያንን የተከተለ ርምጃ እንዲወስዱ ይጠበቃል፡፡ አብዛኛው ምእመን ‹ቄስ› በላይና ግብር አበሮቹ የፈጸሙትን ነውር በሚገባ ስለሚያውቅና ወደ ቤተክህነቱም (ያውም በኃላፊነት) የተመለሱት በእውነተኛ ንስሓና ቀኖና ቤተክርስቲያንን ተከትሎ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ስላለው (በተጽእኖ እንደሆነ ስለሚገምት) ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ወይም ግለሰቡ በቤተክህነቱ ውስጥ ካለው የኃላፊነት ቦታ እንዲነሣ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለናል፡፡ የተዋሕዶ ሃይማኖት አማኞች ነን ብለን በጐሣ/በዘር ጉዳይ ውስጥ የተዘፈቅን ካለን ወደ አባቶቻችን ቀርበን ዛሬውኑ በንስሓ እንመለስ፡፡ እኛ ሁላችን የአንድ ክርስቶስ ዘር ነንና፡፡ በመንፈስ ከሥላሴ ዳግም ልደት የተወለድን፤ የእግዚአብሔር ልጅነት ያገኘንና ሀብተ መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን መሆኑን አንዘንጋ፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያናችንን ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች በሆነችው በእናቱ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡

Filed in: Amharic