>

በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ጽንፈኛ ሽብርተኞች እያደረሱት ያለውን ጥቃት በተመለከተ የባልደራስ ድርጅታዊ መግለጫ....!

በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ጽንፈኛ ሽብርተኞች እያደረሱት ያለውን ጥቃት በተመለከተ የባልደራስ ድርጅታዊ መግለጫ….!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

 በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ሽብርተኛው ሸኔ በመባል የሚታወቀው የኦህዴድ ብልፅግና ተጠባባቂ ልዩ ኃይል  ድንገተኛ ጥቃት ፈፅሞ በርካታ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን፣ አመራር እና ሰላማዊ ሰዎችን መግደሉ ይታወቃል፡፡ መነሻቸውን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን ያደረጉ ታጣቂ ቡድኖች እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን ታጣቂዎች በቅንጅት ሰሞኑን የአማራ ልዩ ኃይልን መውጋታቸው ተነግሯል፡፡

የሽብርተኛው ኃይል  ጥር 13/2015 ዓ/ም በኤፍራታና ግድም ወረዳ ጀብውሃ ቀበሌ በሚገኘው በአማራ ልዩ ኃይል ካምፕ ላይ በቡድን መሳሪያ በመታገዝ ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ከ25 በላይ የአማራ ልዩ ኃይል እና 5 የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የቀበሌው አስተዳደር ሰራተኞች እና ኃላፊዎች መገደላቸው እና በርካቶች መቁሰላቸው ይታወቃል። ጥር 14 ቀን መለስተኛ መረጋጋት የታየ ቢሆንም ጥር 15/2015 ዓ.ም ከከሚሴ እና አጣየ መስመር መካከል ጨፋ ሮቢት በተባለ ልዩ ቦታና አካባቢው ዘግናኝ የአማራ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡

በተለይም ጥር 15 ቀን መነሻውን ኮምቦልቻ አድርጎ ወደ ሸዋሮቢት ይገባ የነበረ የአማራ ልዩ ኃይል  በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ዞን ታጣቂዎች ሰንበቴ በምትባል አካባቢ በከበባ ጥቃት ደርሶበታል፡፡ በዚህም በርካታ ልዩ ሀይሎች እና ሌሎች የፀጥታ መዋቅር አካላት ሕይወታቸው በታቀደ እና በታሰበበት መልኩ መቀጠፉን የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ አቶ መሀመድ አህመድ ተናግረዋል፡፡ ሰንበቴ ከተማ ምርዋ ሰፈር እና ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተራራ ላይ ጥር 15/2015  ዓ.ም የተሰው የልዩ ኃይል  አባላት አስክሬን ለቀናት ያህል አለመነሳቱም ተዘግቧል። ቀባሪ ጠፍቶ የአንዳንዶቹ አስክሬን በጅብ  መበላቱና ትርፍራፊ አካላት ብቻ ተገኝተው መቀበራቸውን የአካባቢው ሰዎች ለሚዲያ ገልፀዋል፡፡

ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ታጣቂ ሃይሉ ማታ ላይ ከሸዋ ሮቢት በቅርብ እርቀት የምትገኝ ዙጢ የምትባል መንደር ላይ በርካታ ቤቶች አቃጥሏል፡፡ ታጣቂዎቹ ጥር 17/2015 ዓ/ም በቡድን መሳሪያ የታገዘ ተኩስ ማጀቴ አከባቢ እና ጨፋ ሮቢት ከተማ ላይ ከባድ ተኩስ ከፍተው ውለዋል፡፡ ጨፋ ሮቢት ከምትባለው አካባቢ ከደሴ አቅጣጫ ይመጣ የነበረ የአማራ ልዩ ሃይልን ወደ ሽዋሮቢት አያልፍም በማለት ሲዋጉት መዋላቸው ታውቋል፡፡ የኦህዴድ ብልፅግና ተጠባባቂ ጦር የሆነው ሸኔ  በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ጀብውሃ፣ ቁርቁር፣ ጀጀባ ሰንበቴ፤ በአጣዬ ዙሪያ ጅሌ ጥሙጋ  እንዲሁም በሸዋሮቢት አቅራቢያ  ዙጢ  በሚባሉት አካባቢዎች በቡድን መሳሪያ የታገዘ ወረራ  መፈፀሙን ቀጥሏል።

ሽብርተኛው ኃይል  በከባድ መሳሪያ የተደገፈ ድንገተኛ ተኩስ በልዩ ኃይሉ እና በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ ከከፈተበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ጥር 18/2015 ዓ/ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ ጀምሮ በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ ሀገረማርያም ሟጨራ ቀበሌ ስር በሚገኙ ከስምንት በላይ በሚሆኑ መንደሮች ላይ ታጣቂዎቹ ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፣ በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የክልሉ ፀጥታ ኃይል ቢኖሩም ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል እርምጃ አለመውሰዳቸው ታውቋል፡፡

የቀበሌው ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ላለመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረጉ ሲሆን፣ በርካቶችም ቆሰስለዋል፡፡ ወራሪ ቡድኑ ብዛት ያለው ኃይል ከማሰለፉም ባሻገር ላውንቸር፣ ብሬል እና ድሽቃን የመሳሰሉ የቡድን መሳሪያዎችን ጭምር መጠቀሙን የጥቃቱ ሰለባዎች ተናግረዋል፡፡ ይህ ኃይል እነዚህን የቡድን መሳሪያዎች የሚያስታጥቀው የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

አጣየ እና አካባቢው ባለፉት አራት ዓመታት ለስምንተኛ ጊዜ በታጣቂ ኃይል  መወደሙ ይታወቃል፡፡ የፌደራል መንግሥቱ በክልል መንግሥታት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገባም በሚል ሽፋን በአካባቢው ላለው የጸጥታ ችግር ትኩረት አለመስጠቱ በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር ይበልጡኑ እያባባሰው መጥቷል።

ከወራት በፊት ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ ወደ 70 የሚደርሱ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸው ይታወቃል፡፡ በሰሜን ሸዋ የሽብርተኛው ቡድን ጥቃት መሰንዘር ከጀመረ ጀምሮ በሚሰጠው ወታደራዊ መረጃ እየተጠቀመ በካምፕ ዉስጥ በሚገኝ የአማራ ልዩ ኃይል ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ300 የማያንሱ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸው እና በርካቶችም መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል ከህወሓት ጋር ሲያደርገው በነበረው የተጧጧፈ ጦርነት እንኳን በአንድ ጊዜ ይህን ያህል የልዩ ኃይል አባላት በክህደት ስለመሰዋታቸው አልተዘገበም፡፡

አሁን ላይ የተፈጠረውን ችግር ልዩ የሚያደርገው በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እራሱን ከነአካቴው ከአማራ ክልል ነፃ እንዳወጣና የአማራ ክልላዊ መንግሥት ማናቸውም ታጣቂ ኃይሎቹን ወደ ዞኑ ማስገባት እንደማይችል በይፋ ለማወጅ መብቃቱ ነው፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው የኦሮሞ ልዩ ዞን ተጠሪነቱ ለአማራ ክልላዊ መንግሥት ሊሆን ሲገባው፣ አሁን ሰፍኖ በሚገኘው የነገድ ፖለቲካ ምክንያት የኦሮሞ ክልላዊ መንግሥት ለልዩ ልዩ ታጣቂዎቹ የመረጃ፣የስንቅና የትጥቅ ድጋፍ በማቅረብ በአማራው ክልል ልዩ ኃይል ላይ እያደረሱ ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት  የአማራው ክልል መሪ ነኝ የሚለው የብአዴን/ብልፅግና መንግሥት ለማዉገዝ እንኳን ድፍረት አላገኘም፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት ያወጣውም የተድበሰበሰ መግለጫ  ጥቃት አድራሽ ሽብርተኛ ኃይሉን በትክክለኛ ሱሙ ለመጥራት ፈርቶ ፀረ ሰላም ሀይሎች ያደረሱት ጥቃት በማለት ገልጿታል፡፡

 ይባስ ብሎም የክልሉ መንግሥት በመግለጫው በኤፍራታ ግድም፣ አጣየ፣ ሰንበቴ፤ ጀውሃ እና በሸዋሮቢት ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ቀበሌዎች የተፈፀመውን ዝርፊያ እና ግድያ የብሔር መልክ ያለው እንዲመስል ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ በማለት ለገዳዮች ከለላ የሚሰጥ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ይህ የኦሮሞ ሽብርተኛ ታጣቂ ኃይል በሰሜን ሸዋ አማራዎች ላይ እየደረሰ ያለው በክልላዊና በፌድራል መንግሥታዊ ቅንጅት እየተመራ የሚገኘው እልቂት ተባብሶ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳያመራም ተሰግቷል፡፡ በኦህዴድ/ሸኔ ጦር እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት ለኦሮሞ ቁመናል በሚሉ ሚዲያዎች እና አክቲቪስቶች በስፋት እየተደገፈ መገኘቱም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች አርቆ ለማስተዋል የተሳናቸው መሆኑን ከማመልከቱም ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት በአንድ ብሔረሰብ የለየለት ፍፁማዊ የበላይነት ለዘለቄታው ለማስቀጠል የማይቻል መሆኑን ሊገነዘቡት አለመቻላቸውን ያመለክታል፡፡

በሰሜን ሸዋ በአማራ ልዩ ኃይል አባላት ካምፕ ላይ በደረሰው ግድያ፣ አጣዬን ጨምሮ በሌሎች የሰሜን ሸዋ ከተሞች ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ለስምንተኛ ጊዜ እንዲቃጠሉ እና እንዲወድሙ በርካታ አማራ ማህበረሰብ አባላትም በግፍ እንዲገደሉ፣ እንዲሰደዱ እና ሀብት ንብረታቸው እንዲዘረፍ መደረጉ ባልደራስ በታላቅ የሃዘን ስሜት እየተገነዘበው ነው፡፡ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ የተጫነው የነገድ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ የእነዚህ ፅንፈኛ የነገድ ብሔርተኞች  አላማም በህወሓት በኩል ነፃ የትግራይ ሪፖብሊክን፣ በኦነግ/ኦህዴድ/ብልፅግና በኩል ደግሞ ነፃ የኦሮሚያ ሪፖብሊክን ማዋለድ ነው፡፡ በሁለቱም በኩል እየተፈራረቁ የሚያካሂዱት ዘመቻ እቅድ በምናባቸው ያሳሏቸውን በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ሊመሰርቷቸው ያሰቧቸውን “ነፃ ሪፖብሊኮች” ከሌላ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች የፀዱ እንዲሆኑ በማድረግ፣ በተለይም ደግሞ ከአማራው ክልል የተቻላቸውን ያህል መሬት በጉልበት በመንጠቅ ወደራሳቸው ክልል ማጠቃለል ነው፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ በአማራው ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ባልተቋረጠ ሁኔታ የተጋረጠበት  የህልውና አደጋ  የሚባለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ህወሓት ከኦነግ/ኦህዴድ ብልፅግና መንግሥት ጋር በሰላም ስምምነት ሽፋን እየተሞዳሞደ ያለው  ይህን ዓላማቸውን በፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን በመጠቀም ማስፈፀም ነው፡፡ ይህም ህወሓት ምእራብ ትግራይ ብሎ የሚጠራውን ወልቃይት ሁመራ ጠገዴን እንዲሁም ደቡብ ትግራይ ብሎ የሚጠራውን ራያን መጠቅለልን ያለመ ሲሆን፣ በአንፃሩ የኦነግ/የኦህዴድ ብልፅግና መንግሥት ደግሞ በደቡብ ወሎ ከሚሴ ዋና ከተማው የሆነውን በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የኦሮሞ ልዩ ዞንን እና ሰሜን ሸዋ ወደ ኦሮሚያ ክልል ማጠቃለል ጨምሮ አዲስ አበባን እና ድሬድዋን በመዋጥ ከተቀረው ኢትዮጵያ የተገነጠለ የኦሮሚያ ሪፖብሊክን  መመሥረት ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ በዚህ የህወሓትና የኦህዴድ/ኦነግ ሤራ እንዳትበተን የማድረግ እምቅ ኃይል ያለው የአማራው ማህበረሰብ፣ ይህን እምቅ ኃይሉን ወደ ተጨባጭ ኃይል በመቀየር እና ከተቀሩ የኢትዮጵያ ነገዶች ጋር በመተባበር  ህልውናውን በመታደግ እና በዚህም ሂደት ኢትዮጵያን ከመፈራረስ የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት ትክሸው ላይ ወድቋል፡፡ ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት አማራው ብአዴን የጫነበትን በመካከሉ ያለውን አውራጃዊ ልዩነት አጥፍቶ፣ አንድነቱን አጠናክሮ እና ትግሉን ከሌሎች የኢትዮጵያን መገነጣጠል ከማይቀበሉ ነገዳዊ፣ ሀገራዊና አካባቢያዊ ኃይሎች ጋር አስተባብሮ ራሱን፣አካባቢውን እና ብሎም ሃገሩን ከጥፋት በመታደግ ከኢትዮጵያ ምድር የነገድ ፖለቲካ ከነአካቴው እንዲወገድ ለማድረግ እንዲተጋ ፓርቲያችን ባልደራስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ 

የባልደራስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ቀን 23/2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

#ኢትዮጵያ #አዲስ_አበባ #መረጃ

Filed in: Amharic