>
5:26 pm - Saturday September 17, 0901

ጐሠኛነትን/ድንቊርናን ዕርቃኑን ያስቀረ የአባቶቻችን ውሳኔ (ከይኄይስ እውነቱ)

ጐሠኛነትን/ድንቊርናን ዕርቃኑን ያስቀረ የአባቶቻችን ውሳኔ

ለብፁዓን አባቶቻችን የቀረበ ጥሪ

ከይኄይስ እውነቱ

ቀዳሚው ማለፊያ ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ብፁዓን አባቶቻችን ዐቢይ በተባለ ልቡሰ ሥጋ ጋኔን የሚመራው የወንጀል አገዛዝ ከእስካሁኑ የከፋ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ወንድማችን አቻምየለህ ታምሩ አቡነ ጴጥሮስን አብነት አድርጎ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ  ሳትዘገዩ ተግባራዊ እንድታደርጉ እንደ አንድ ምእመን ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ይኸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ የኢኦተ ቤክ አማኞች በተለይ ዐቢይ ለሚባለው ዓላዊና በሱ ለሚመራው አገዛዝ ምድሩም፣ ባሕሩም እንዳይገዙና እንዳይታዘዙ ጥብቅ ግዘት/ውግዘት እንድታስተላልፉ በታላቅ አክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ የቀረውን ከጸሎታችሁ ጋር ለእኛ ለልጆቻችሁ ተዉት፡፡

በቅርቡ ብፁዓን አባቶቻችን በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው የቤተክርስቲያኒቱ የመጨረሻና የበላይ አካል በሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከቤተክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት አፈንግጠው የወንጀለኛውን የጐሣ ሥርዓት ተልእኮ ለማስፈጸም በተንቀሳቀሱ የቀድሞ ‹ጳጳሳት› እና ከነዚሁ አፈንጋጮች ሕገ ወጥ ‹የኤጲስ ቆጶስነት› ሲመት በተቀበሉት ግለሰቦችና ግብረ አበሮች ላይ ጥበብ የተሞላበት ሕጋዊ፣ ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ 

የዚህ አስተያየት ዓላማ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ በዝርዝር ለመመልከት ያለመ አይደለም፡፡ ይልቁንም ውሳኔው ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ታሪካዊት እና ዓለም አቀፋዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረቷና ጉልላቷ ራሱ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ መሆኑን በድጋሚ ለዓለሙ ያስመሰከረችበት ከመሆኑ ሌላ በውስጥና  በውጭ ኃይሎች ፈተናዋ በበዛበት ዘመን የሊቃውንት ደሀ አለመሆኗን፤ በሕግም በሥርዓትም ስንዱ እመቤት መሆኗን ለማያውቋት፣ በውስጥም በአፍአም ሆነው ለሚተቿት ያሳየችበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ይህም የአማኞቿን ኩራት፣ ጽናትና ተስፋ በእጅጉ ያደሰ ሆኖ አግቼዋለሁ፡፡ ብፁዓን አባቶቻችን በጉባኤ ያስተላለፉት ውሳኔ ብቻ ሳይሆን መግለጫ ሲሰጡም ሆነ በቃለ መጠይቅ ማብራሪያ ሲያደርጉ ንግግራቸው በዕውቀት የለዘበና ጥበብ የተሞላበት መሆኑ ከሃይማኖቱ በአፍአ ያሉትን ወገኖቻችንን እንኳ ያስደመመ ነበር፡፡ ያንዣበበው ሥጋት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንደተባለው የዓላውያኑ ትንኮሳና ጥቃት በጎ ገፅታ ሳይኖረው አይቀርም፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ መልእክት በመግቢያው ላይ የተቀመጠው የምእመን ጥሪ ነው፡፡

የጐሣ ፖለቲካ በሠለጠነበት ባለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት በወያኔና በወራሹ የወንጀል ሥርዓቶች ቀዳሚ ዒላማ ሆና ለሕግና ሥርዓቷ ባዕዳን በሆኑ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቃ ብትገኝም፣ በመንፈስ ቅዱስ ለሚሰጠው ከፍተኛ የቤተክርስቲያን አመራርነት ወይም ሲመት መመዘኛ ውኃ ልኩ ዕውቀት፣ ብቃት፣ ችሎታ፣ ምሳሌነት ያለው መንፈሳዊ ሕይወት መሆኑ ቢያንስ በመርህ ደረጃ የምትከተለው የብቃት ሥርዓት (Merit System) እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ 

በተቃራኒው ጐሠኛነትን ርእዮቱ ያደረገው ዓለማዊ አገዛዝ መሠረቱም ሆነ ጉልላቱ ድንቊርና ነው፡፡ ሕዝብ በይፋ እንደሚያውቀው ቅጥርና ሹመት ከቤተመንግሥቱ እስከ ገጠር ቀበሌ ማኅበር ጐሠኛነት፣ እከክልኝ ልከክልሀ፣ በትውውቅና በፖለቲካ ግንኙነት (Spoil System) ነው፡፡ ይህም አገርን በደናቊርት ሥር በማድረግ ለውርደትና ውድቀት ዳርገዋታል፡፡ 

ብፁዓን አባቶቻችን ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤክ ጠባይ በውሳኔአቸው እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹ምንም እንኳ ከቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ከኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን በጐሣና በቋንቋ የመለየት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንግዳ ክስተት ቢሆንም ቤተ ክርስቲየን ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጠባይዋ በተለየ፣ ታሪኳንና ሥርዓቷን በማይመጥን፣ ከሕግ መንፈሳዊ፣ ከሕግ ጠባይአዊ እና ከሕገ አእምሮ በወጣ መልኩ የደረሰባት ጥቃት፣ እና የመፈንቅለ ሲኖዶስን ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ አሳዝኖታል፤›› 

ጐሠኛነት እጅግ ኋላ ቀር የሆነና በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ሊታሰብ የማይችል የድንቊርና ሥርዓት ነው፡፡ ጐሠኛነት የአንድነትና እኩልነት ፀር ነው፡፡ ‹እኛና እነሱ› የሚል አመለካከት ፈጥሮ የጥላቻ፣ የመለያየትና የጭካኔ መራቢያ አመቺ ማሳ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር የተሰጠውን አእምሮና ነፃነት እንዳይጠቀም የሚያደርግና ክቡሩን ፍጥረት ከእንስሳነት አሳንሶ ወደ ግዑዝነት የሚቀይር አመለካከት ነው ጐሠኛነት፡፡ ይህንን አመለካከት ነው አባቶቻችን ከሕግ መንፈሳዊ (ከሃይማኖታዊ ሕግጋት)፣ ከሕገ ጠባይዕ (ባሕርያዊ ከሆነ የተፈጥሮ ሕግ) እና ከሕገ አእምሮ (በትምህርት ከሚገኝ ዕውቀት) ተቃራኒ ነው ያሉት፡፡

ሰማያዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት የምትወክለውና የምትሰብከው ቤተክርስቲያን ጠባይ የጐሠኛነት አስተሳሰብ የማይስማማት ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተቃራኒዋ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የገጠመን ፈተና እንዲህ በብርሃንና ጨለማ መካከል እንዳለ ልዩነት ጎልቶ የወጣ ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ መከራዋ የበዛውም የጐሠኞችን ድንቊርና በማጋለጧ፣ የጥፋተኝነት ሕሊናቸውን ፍንትው አድርጋ ስለምታሳይ ብቻ ሳይሆን መሠረተ እምነቷ (Dogma)፣ አስተምሕሮዋ (Doctrine) እና ቀኖናዋ (Canon) ባገር አንድነት፣ ባንድ አገር ሕዝብ አንድነትና ሉዐላዊነት፣ በእያንዳንዱ ግለሰብ የእግዚአብሔር ፍጡርነት (የአዳም ልጅነት)፣ ሰብአዊ ክብር፣ መብትና ነፃነት የምታምን ይህንኑ የምታስተምርና በዚህም ለሁሉም የጋራ የሆነ ብሔራዊ ማንነት የምትፈጥር በመሆኑ ጐሠኞች ደመኛ ጠላቷ አድርገው ቢመለከቷት አይደንቅም፡፡

ዛሬ በቤተ ክህነቱ እና ሳይገባቸው ዐፄ ምንይልክ ቤተመንግሥት በገቡት ወሮበላ ጐሠኞች መካከል ያየነው ፍጥጫ የዕውቀት እና የድንቊርና ነው፡፡ ከጐሣ፣ ከቋንቋ፣ ከቀለም፣ ከዘር፣ ከድንበር በላይ ሆና ዓለም አቀፋዊ ጠባይ ያላት የኢኦተቤክ ጐሠኞቹና አሳዳሪዎቻቸው እንደሚናገሩት የሥልጣኔና የዕድገት እንቅፋት ሳትሆን በተቃራኒው የሕግ፣ የሥርዓት፣ የትምሕርት፣ በብቃትና ችሎታ ላይ የተመሠረተ አመራር ምንጭና ባለቤት ናት፡፡ በነገራችን ላይ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የኢኦተቤክ /ክርስትና/ ለኢትዮጵያ ያደረገችውን አበርክቶ በጥቂቱ የዳሰስሁበትን መጣጥፍ መመልከቱ መጠነኛ ግንዛቤ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያን መንበረ ሥልጣን በጉልበት የያዙት ጐሠኞች አለቃ ሐሰት ሁለተኛ ባሕርይው ሆኖ ሌት ተቀን አገር በማጥፋት የተጠመደ ቢሆንም፤ ለሰውየው የለመደው አፈ ጮሌነት መስሎ ቢታየውም፤  ሳይወድ በግዱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አፉን ከፍቶ ፈቱን ጸፍቶ ቤተክርስቲያን ‹አገር› ነች በማለት አናግሮታል፡፡ ታዲያ አገር ከሆነች ጦር መስበቁን፣ የግድያና አፈና ዛቻ ማስፈራሪያውን እና የጥፋት ነጋሪት ጉሰማውን ምን አመጣው? እንደ ኢኦተቤክ አስተምሕሮና ትውፊት ‹አፍን ከፍቶ ፊትን ጸፍቶ› የሚለው ብሂል ከተናጋሪው ፍላጎትና እምነት ውጭ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ እውነት እንዲነገር የሚደረግበት መንገድ ነው፡፡ ያም ሆኖ ኢትዮጵያንም ሆነ ተዋሕዶን ለመታደግ የሚፈልግ ሁሉ  በልቡ ሊጽፈው የሚገባ ቁም ነገር ቅጥፈት ሁለተኛ ባሕርይው የሆነውን ሰውዬ በፍጹም ካለማመን መነሣት ነው፡፡ ይህ ዐረሚ ዛሬ በለመደው ብልግና ብፁዓን አባቶቻችንን ይዤባቸዋለሁ በሚለው ጥፋት ምድራዊ፣ ማን አለብኝ ባዮችና ራስ ወዳዶች ከሚል ክስ አልፎ በቤተክርስቲያናችን/በሃይማኖት ጉዳይ በይፋ ሙሉ ለሙሉ ጣልቃ ለመግባት ዝቷል፡፡ በቤተክርስቲያናችን ላይ ላሠማራቸው ነውረኞች ጥብቅና ከመቆም አልፎ ተባዳዮች በማድረግና በእኩልነት በማየት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለመቀልበስ በይፋ የዓመፃ ንግግር አድርጓል፡፡ ስለሆነም ሥርዓት ኬላለው ዐረሚ ጋር የሚደረገውን ልምምጥ አቁማችሁ ባስቸኳይ አገርንና ሃይማኖታችንን ትታደጉ ዘንድ በልዑል እግዚአብሔር ስም የልጅነት ጥሪዬን ከእግራችሁ በታች ሆኜ አቀርብላችኋለሁ፡፡

በነገራችን ላይ አፈንጋጮቹን ያሰማራቸው የወንጀል አገዛዝ የለየለት ድንቊርና ዋና ማሳያ የቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና ለድርድር የሚቀርብ ተራ የዓለሙ ሸቀጥ ማድረጉ ነው፡፡ አንድም የለመዱት ንቀትና ማንአለብኝነት ነው፡፡ ዓለማዊው ፖለቲካ በሕግና በሥርዓት የሚመራ የአገርና ሕዝብ አስተዳደር ጥበብና ፍልስምና ከመሆኑ ይልቅ ተራ ‹ቁማር› ነው ብለው የሚያስቡ መደዴዎች ስለ መንፈሳዊው ሥርዓት ምን ሊገባቸው ይችላል? በትንሹ ያልታመነ ለትልቁ ማን ይሾመዋል? እንግዲህ ወገኖቼ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ አገር  የወደቀችው በነዚህ ዐረማውያን እጅ ነው፡፡ዛሬ ዳኝነት በሌለባት፣ ፍርድ በሚጓደልባት፣ ፍትሕ በተቀበረባት፣ ባጠቃላይ የሕግ የበላይነት በሌለባት ኢትዮጵያ እና እነዚህን ‹ሕገ አራዊት› ባሠለጠነው የጐሠኞች አገዛዝ ቀርቶ ትክክለኛ የመንግሥትነት ባሕርይ ባለው ሥርዓትም ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈውን ዓይነት ጥንቅቅ ያለና ደርዝ ያለው የውሳኔ አካሄድ ለማግኘት ይቸግራል፡፡

አባቶቻችን በውሳኔአቸው እንዳኮሩንና ሕዝበ ክርስቲያኑ ከጎናቸው ቆሞ ላገርና ለቤተክርስቲያናችን የሚጠቅም ትእዛዛቸውን ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ዐውቀው፤ ወንድማችን አቻምየለህ ታምሩ እንዳሳሰበው ውግዘቱን አንድ ደረጃ ገፋ አድርገው አገርንና ቤተክርስቲያንን ሊያፈርስ ሌት ተቀን እየሠራ ባለው የጐሠኞች አገዛዝ ላይ በጥብዐት መንፈስ ቢያስተላልፉ ኢትዮጵያንና ተዋሕዶን መታደግ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ አጥፊዋ ታዳጊዋ እንደማይሆን ከእናንተም የተሰወረ አይደለምና፡፡ በጸሎት ምክሩበት፡፡ ውሳኔአችሁን በተስፋ እንጠብቃለን፡፡

ጥብዐት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጸጋ ሆኖ፣ እግዚአብሔር የሚወደው ወይም ለጠቅላላው የሚበጅ በጎ ነገር ለመፈጸም ወይም ራስን ለሰማዕትነት ለማዘጋጀት የሚሰጥ ድፍረት/ቊርጥ ሐሳብ ወይም ለመልካም ተግባር መጨከን ነው፡፡

Filed in: Amharic