>

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያን ጉዳይ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ፓትርያርኮች ሊሰባሰቡ ነው!

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያን ጉዳይ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ፓትርያርኮች  ሊሰባሰቡ ነው!

የኤርትራ ፕረስ ድርጅት

የኤርትራ ቅዱስ ሲኖዶስን ጨምሮ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት ቅዱሳን ፓትርያርኮች በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስም በቅርቡ የተመሰረተውን ህገወጥ ሲኖዶስ እና በቅድስት ቤተክርስትያኗ ላይ የተከሰተውን ፈተና በተመለከተ ምክክር ለማድረግና ውሳኔ ለማሳለፍ በግብጽ ካይሮ ሊሰባሰቡ ነው።

የሚሰባሰቡት ቅዱሳን አባቶችም:- 

• የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሓፊ አቡነ እንደርያስ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ – 118ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካርኪን ዳግማዊ – 132ኛው የመላው አርማንያ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሳልሳይ – 22ኛው የህንድ ፓትርያርክ

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አግናጤዎስ ኤፍሬም- 122 ኛው የአንፆኪያና የመላው ሶርያ ፓትርያርክ

አምስቱም ቅዱሳን አብያተ ክርስትያናት በኢትዮዽያ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል አውግዘው ከነባሩና ከህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጎን እንደሚቆሙ በመግለጽ ቅድስት ቤተክርስትያኗ የደረሰባትን ክፉ ፈተና በሰላም እንድትሻገር እግዚአብሄርን በፀሎት እንደሚጠይቁም ጭምር ገልፀው ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ ለህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ለመላው ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን መልእክት መላካቸው ይታወሳል።

አሁን ደግሞ የአምስቱ እህት አብያተ ክርስትያናት መሪዎች በካይሮው ስብሰባ ተገኝተው በዘርና በቋንቋ የተዋቀረውን በእነ አቶ አካለወልድ (በቀድሞ ስሙ ሳዊሮስ) በተባለው ግለሰብ የሚመራውን ህገወጡን ሲኖዶስ ከማውገዝ ጀምሮ ከእነርሱ ጋር ህብረት ያለው፣ በገንዘብ፣ በምክር እና በሌላ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ድርጅቶችን እና ተቋማትን አውግዘው እስከመለየት ድረስ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Filed in: Amharic