>

ተስፋ ባልቆርጥም፣ መደንገጤን አልደብቅም፤ (አሰፋ ታረቀኝ)

ተስፋ ባልቆርጥም፣ መደንገጤን አልደብቅም፤ 

በባእለሲመተወ እለት ያደረጉትን ንግግር እንኳን እኛ ሰብአዊ ፍጡሮቹ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚበሩት አእዋፍ የሚረሱት አይመስለኝም “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” ነበር ያሉት፡፡ አፈሩ ይቅለላቸውና ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የእርሰወንና የአቶ ለማ መገርሳ ስለ ኢትዮጵያ   መቆጨትና በስሜት መንደድ አይተው “እነዚህ ከሰማይ የተላኩ ናቸው” እስከማለት አድርሷቸው ነበር፡፡ አቶ ለማ ብዙ ሳይቆዩ ገለል ቢሉም፣ እርሰዎ በቦታዎ ላይ ሆነው ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ማዕበሉን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብረው አልፈውታል፡፡ክብሩ ለእግዚአብሔር ይሁንና በተመጠነና በተዋበ አነጋገር የታወቁ ነዎት፤ ከተወሰነ ጊዜ ወድህ ጥያቄ የሚያጭርና “ምን እየሆኑ ነው?” የሚያሰኝ ንግግር እየሰነዘሩ ቀጥለዋል፡ባለፈው አዲስአባባን በተመለከተ አስተያየት ሲስጡ “ኦሮሞ ጠል” የሚል ቃል ተጠቀሙ፤ የኔ አይነቱ ተራ ሰው ቢናገረው አድማጭ የለውም፡፡ እርሰዎ በጎሳ ኦሮሞ፣ በሥልጣን የሐገር መሪ ሆነው ሲናገሩት፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚፈጥረው ስሜት አስፈሪም አነጋጋሪም ነው፤ በእርግጥም አነጋግሯል፡፡ ሰሞኑን ከካቢኔ ሚንስትሮቸዎ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ስለ ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ አንስተው ሲናገሩ፣ ከዶ/ር አብይ ጋር ካልቆምን ኢትዮጵያን እንደከዳናት ይቆጠር እያልኩ የምሟገተውን ሰው ያስደነገጠም ያሳዘነም አስተያየት ሲሰጡ ተከታትያለሁ፡፡

በኦርቶዶክስ ቤተችርስቲያን ውስጥ የተነሳውን ውዝግብ አስመልክተው በስጡት አስተያየት ላይ “የአንድ ሕዝብ በቋንቋው ከመጠቀም መብት”ጋር አያይዘው ሲገልጡት፣ ከመገረም ባለፈ ትዝብት አዳመጥኮዎት፡  በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩት የብዙ ክፍለ ዘመን ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ እንድሆን የተፈረደበት የአማራ ሕዝብ ልጆች፣ እርሰዎ ከመወለደዎ በፊት በነበሩት አመታት ጀምሮ ለሁሉም የሰው ልጆች እኩልነት የሕይወት ዋጋ ከፍለዋል፡፡ደርግምኮ አሉ የተባሉ የሀገሪቱን ባለሙያዎች ሰብስቦና አስጠንቶ፣ የብሔረሰቦች ኢንስቲቲዩት ከፍቶ ነበር፡፡ ብሔረሰቦች በቋንቋቸው እንድገለገሉ፣ ትግሉን የጀመሩት ኦሆድድና ትህነግ አልነበሩም አይደሉምም ለማልት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በኦሮሙኛ ቋንቋ እንደሚሰበክና እንደሚቀደስ እያወቁ፣ ኅሊናዎ እንደት ቢፈቅድለዎት ነው በኅይማኖት ሽፋን የሚካሄደውን የፖለቲካ ሸፍጥ ከቋንቋ ጋር ያያዙት? የየትኛው አካባቢ ሕዝብ ነው በኦሮምኛ ይሰበክልኝ ብሎ ጥያቄ ያነሳው? የተወገዙት ካህናት በኦሮሚያ ልዩ ሀይል ሲጠበቁና እንክብካቤ ሲደረግላቸውና፣ ሌሎቹ ሲንገላቱ እያየን “ ሕገመንግሥቱ ያጎናጸፈውን መብት መከልከል አልችልም” ሲሉን፣ እንዳለፉት አምባገነን መሪዎች የኛን የመገንዘብ ችሎታ ዝቅ አድርገው ገመቱት ልበል? ባለፈው የትግራይ ካኅናት የወሰዱትን አቋም ከሰሞኑ ሁኔታ ጋር ለማመሳሰል የሄዱበት መንገድ አስገራሚ ነው፡፡ በትህነግ ቁጥጥር ሥር የነበረች ቤተክርስቲያን ያለችውን ብትል ሰሞኑን እየሆነ ካለው ጋር ይመሳሰላልን? ክተወሰነ ጊዜ ወድህ የሚጠቀሙበት አነጋገር እርሰወን እርሰወን አልሼት እያለኝ ተቸግሬያለሁ፡፡

ኦነግና ጽንፈኛ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ኦሮሚያ የትባል ሀገር የመገንባት የረዥም ጊዜ እቅድ እንዳላቸው ሳይደብቁ ነግረውናል፤ በአድስ አበባና በዙሪዋ የሚደረጉት ሙከራወች ሁሉ ወደዚያ እሚያመለክቱ ናቸው፡ በፈረንጅኛው testing the water የሚሉት መሆኑ ነው፡፡ የክልል ሰንደቅ አላማ አድስ አበባ ውስጥ መስቅሉ፣ በቋንቋችን ይዘመርልን መባሉ፣ አማርኛ ተናጋሪውን ከኦሮሚያ ክልል መመንጠሩ፣ ለሚቀጥለው ውሳኔ ያመች ዘንድ የመረጃ መፈተኛ መንገድ ይመስላል፡፡ በሰሞኑ ስብሰባ ላይ የነበሩት የካቢኔ ሚንስትሮቸዎ በጣም አሳዛኑኝ፣ በአንድ ቁጡ የዩኒቨርሲቲ ሌክቸረርና በተማሪዎች መካከል ያለ ግንኙነት ይመስል ነበር፡፡ ለመሆኑ የካቢኔ አባሎችዎ በሕዝብ ተወክለው የመጡ አይደሉም እንዴ? ምናለበት ይህንን የቁጣ ሀይል ወደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቢያዞሩትና በገፍ የሚጨፈጨፈውን አማራና ኦሮሞ ቢታደጉት?

የእምነት ሰው ከመሆነዎም በላይ የእግዚያብሔርን ቃል እንደሚሰብኩ አውቃለሁ፤ እንደሚያውቁት፣ ዘጸአት መዕራፍ 20 ቁጥር 3፣ እንድህ የሚል ቃል እናነባለን “ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” አንደበተዎ ላይ ከሚያሽሞነሙኗት ኢትዮጵያ ጎን በጎን ሌላ ዕቅድ እንዳይኖረዎት ምኞቴ ነው፣ ምክኒያቱም ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ውጭ የሚታሰበው ሁሉ ሀገርንም ትውልድንም ያጠፋልና፡፡ ስለሰላም ሁኔታም ሲያብራሩ አንድ አስፈሪና አስደንጋጭ ሀሳብ ጨምረዋል፡፡ የቀይ ሽብርን ዘመን አንስተው፣ ያስከተለውን ውድቀት ካብራሩ በሗላ፣ አድስ አበባ ውስጥም የግለሰብ ግድያ ለመጀመር ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፣ ከተጀመረም ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡ እነማናቸው? ኦነግ ሸኔ? “አማራ ሼኔ” ትህነግ? የመዕራቡ አለም መሪ ቢሆኑ ኖሮ፣ የተጣራ ማብራሪያ ሳይሰጡ ወደቤተዎ አይገቡም ነበር፡፡ አህጉሩ አፍሪካ፣ ሀገሪቱም ኢትዮጵያ ሆነችና፣፡ አስፈሪውን ሀሳብ ወደ ሕዝቡ ወረወሩለት፣ የጠየቀም የለም፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና በሀጫሉ ላይ እንደተደረገው በአንዱ ኦሮሙኛ ተናጋሪ ባለሥልጣን ላይ አድስ አበባ ውስጥ ግድያ ቢፈጸም፣ ከኦሮሙኛ ተናጋሪው ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ምን ሊበቃው ነው? 

 ለግድያ ሙከራ የተሰማራውን ቡድን ማኅበራዊ መሠረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመግለጽ ግደታ አልነበረበወትም? የሚናገሩትን የሚያውቁ፣ ለአፍ ወለምታ የተጋለጡ ሰው እንዳልሆኑ አውቃለሁ፤ እንደዋዛ ጣል ያደረጉት ግለሰቦችን የመግደል ዕቅድ ማን እንደሆነ፣ ሊያሳካ የሚፈልገው ተልኮ ምን እንደሆነ ለመረጠወት ሕዝብ ካላብራሩ፣ ይህንን የኑሮ ጉስቁልና ያሰቃየውን ህዝብ በፍርሐት ቆፈን አፍኖ ለመያዝ የተዘጋጁ ያስመስለወታል፡፡ እኤአ ከ 1892 እስከ 1980 የኖረችው ዝነኛዋ አሜሪካዊቷ የመድረክ ተዋናዊት Mae West፣ ‘’የምትኖርው አንድ ጊዜ ነው፣ ሆኖም በአግባቡ ከተጠቅምክበት ራሱ በቂ ነው’’ ትላለች፡፡ You only live once, but if you do it right, once is enough. ባለፉት አራት አመታት ውስጥ እጂግ አስደናቂና ትውልድ ሲያስታውሳቸው የሚኖር ሥራ ሠርተዋል፡፡ አንድ ሰው በህይወቱ ሊያደርግ ከሚችለው በላይ የተሳካ ውጤት አሥመዝግበዋል፡፡ ደክሞወት ከሆነ፣ ይሻላል የሚሉትን ሰው ተክተው ይረፉ፡፡ ያንን የመሰለ የሕዝብ ፍቅር ወደ ጎሳ ከረጢት ይዘውት ሊወሩ ዳርዳር እያለዎት ከሆነ፣ እርሰወን ከመአቱ የኔን መሰሎችም እያዘንን ወደ መቃብር ከመውረድ እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃ ስከታተል፣ እርሰወን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚደረግ የጠላት ሤራ አድርጌ እቆጥረው ነበር፡፡ የሰሞኑ ድርጊተወ የኔን የቀደመ እይታ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በስሙ የሚነገድበት ቅኑ የኦሮሞ ሕዝብም አብሮት የኖረው ምስኪን ወሎየ እፊቱ በስለት ሲታረድ ደስ ብሎት ያድራል ብሎ መገመት ኦሮሞን አለማወቅ ነው፡፡

እየሆነ ያለውንና የእርሰወን የሰሞኑን የአቋም ለውጥ ስመለከት፣ የአስቴርና የመርዶክዮስ ውዝግብ ታወሰኝ፡፡ “አንች በንጉሡ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ አታስቢ፡፡ በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ፣ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ሥፍራ ይሆንላቸዋል፣ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ” መጽሐፈ አስቴር 4፤ 13-14:: አማርኛ ተናጋሪው ከሰሜን በትህነግ፣ በደቡብና በምዕራብ በኦነግ ቁምስቅሉን እያየ ይገኛል፡፡ እርሰወ ሲመጡ እረፍት ያገኛል የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ ወከባው በእጥፍ ጨምሯል፤ ሚንስትሮቸዎ ትንፍሽ እንዳይሉ አስጠነቀቋቸው፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳን ማን ሀይ ይበላቸው? ‘ሁሉ ለኛ ሁሉ በኛ” የሆነ አካሄድ ኢትዮጵያን አይጠቅማትም፡፡

የሚያመልኩት አምላክ ቅናውን ያሳይዎ፡፡

Filed in: Amharic