>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4360

"አምሓራ ሆይ! ራስህንም ኢትዮጵያንም አድን" (ከብርሃኑ ድንቁ)

“አምሓራ ሆይ! ራስህንም ኢትዮጵያንም አድን”

ከብርሃኑ ድንቁ

ኢትዮጵያ በግልጽ በሚታዩ እሴቶችና በግልጽ በማናያቸው መንፈሳዊ ሚስጥሮች ውህደት የተገነባች አገር ነች። ይህችን አገር ለማንበርከክ ወይንም ለመበተን የሚኬድበት መንገድ አስቸጋሪና እጅግ ውስብስብ የሆነው ለዚህ ነው። በየዘመናቱ የሚነሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች ከመንፈሳዊ ጋር የተዋሃዱን የቆዩ እሴቶችና ትውፊቶች መነጣጠሉ እጅግ ከባድ ስለሚሆንባቸው ብዙ እንዲዳክሩና እንዲደክሙ አድርጓቸዋል። ኢትዮጵያን በቅርብ ዘመናት ከፈተኗት ሁሉ ኦነግ የሚያራምደው ኦሮሙማ አስተሳሰብ ይጠቀሳል። ኦነጋውያን ኢትዮጵያን በቀላሉ ማፍረስ ባለመቻላቸው ሕዝብን ፍዳ አስቆጥረዋል፣ ምድሪቱን በእስታ ጠብሰዋል።።

በኦነጋውያን ቡድኖች መሃከል ያለውን ቅራኔ ያሰፋው የጊዜ ርዝመትና የሥልጣን ጉጉት ነው። ሁለቱም ወገኖች ኦሮምያን እናስገነጥላለን፣ ፊንፊኔ ዋና ከተማችን ነች፣ ኦሮሚፋን እናውጃለን፣ የገዳ ባህልን በአፍሪካ እናስፋፋለን፣ ወዘተ፣ የሚሉ የጋራ ስምምነት አላቸው። ነገር ግን ብልጽግና ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ – “ኢትዮጵያን በቀላሉ ማፍረስ አይቻልምና ጊዜ ወስደን መጀመርያ እሴቶችዋንና ትውፊቶችዋን እንሸርሽር፣ የተዋቡ ቃላት እየደረደርን እናዘናጋው፣ የሕዝቡን አንድነት ቀስ በቀስ እንናድ፣ ጀግንነቱን እናላላ፣ ረሃብ እያባባስን ቅስሙን እንስብረው፣ የዋጋ ንረት እየፈጠርን እናደኽየው፣ አስፈላጊ ሲሆን በዘር እየከፋፈልን እናባላው፣ ወዘተ፣” የሚል አዲስ ጮሌ ቡድን ብቅ አለ። ከዚህ ቡድን በልዩነት የቆመው ሌላኛው ቡድን ደግሞ – “አይሆንም የተፈለገው ተከፍሎ፣ የሚገደለው ተገድሎ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያናትን አቃጥለን፣ ዛሬውኑ ኦሮምያን ገንጥለን ሥልጣኑን መከፋፈል አለብን” የሚለው ነው።

የጊዜ ርዝማኔ – ከሥልጣን ጉጉትና የሙስና ተጠቃሚ ከመሆን ውጭ የርዕዮት ወይም የአስተሳሰብ ልዩነት በሌላቸው ሁለቱ ወገኖች መካከል ደም የሚያቃባ ልዩነት ጫረ። ልዩነቱ – ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ መከራ በመሆን ከታላላቅ ንብረቶች ማውደምና አረመኔ በሆነ መንገድ ሰው ዘቅዝቆ ከመስቀል ጀምሮ ሌሎች ሰቆቃዎችን ሥራ ላይ በማዋል በተጨማሪም በአምሓራ ሕዝብ ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ግፍ እንዲፈጸም ምክንያት ሆነ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያ የሚቆረቆርላትና ሕዝብን የሚጠብቅ መንግሥት የላትም።

“ጊዜ ወስደን ኢትዮጵያዊነትን እንናድ” የሚለው የብልጽግና ቡድን ከኦሮሙማነት ሌላ ሁነኛ ፍልስፍና ባይኖረውም – ኢትዮጵያ – ኢትዮጵያ – በማለት የሚኒልክን ቤተ መንግሥት በማስዋብና ችግኝ በመትከል ለማዘናጋት የተጠቀመው ስልት የተዋጣለት መለኛ አድርጎታል። ይህ ቡድን – እያሳመነም ይሁን እያምታታ እንዲሁም ሰው እያሳረደም ሆነ እያቃጠለ እንዳው በጠቅላላው የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ- ያሻውን በእርጋታ ሲተገብር ቆይቶ በመጨረሻ ወደ ታላቂቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጉዳይ ላይ ደረሰ። አዲሱ ቡድን የኢትዮጵያና የቤተ ክርስትያኒቱ ወዳጅ መስሎ በመቅረብ ውስጥ ውስጡን ግን ይህችን እጅግ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረች የእግዚአብሄር ማደርያ – ንዋይ በተቆረጠላቸው አይዟችሁ ተብዬዎችና ተላላኪዎች ሲያስወርፋትና ሲያንቋሽሻት ቆይቷል። ቡድኑ በቅርብ ሰሞን ሲቀልበው የቆየውን ደፋር ዓይን አውጣ ልኮ – ከዘመን ዘመን የተሸጋገረችውን ቤተ ክርስትያን – ጣዖት አምላኪ የድህነት ምንጭ፣ ኋላ ቀር – በማስባል አሰደባት። ይሄ አልበቃ ብሎት ደረጃውን ከፍ በማድረግ ስልታዊውን እና በክፋት የታጀበውን የኦሮምያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ተብዬው መዋቅራዊ ተግባራትን አገባዶ ሲኖዶስ መስርቻለሁ አለ። እዚህ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ የደረሰው የኦሮሚያ ብልጽግና ቡድን ኢትዮጵያን የማፈራረስና ኦሮምያን የመመስረቱ የመጨረሻው መጀመርያ መሆኑን ያልተረዳ ካለ ከህልሙ መንቃት አለበት።

“በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ” እንደተባለው የዋሆቹ ኦነጋውያን ሥልጣን እና ገንዘብን መዳረሻ ግባቸው አደረጉ እንጂ ኦሮምያ ብትገነጠል የሚመጣውን ታላቅ ችግር እና መከራን ላንድ አፍታ እንኳ ቆም ብለው ያሰቡበት አይመስልም። ኦነጋውያን በለስ ቀንቷቸው ኦሮምያን ቢያስገነጥሉ ኢትዮጵያ የተሸከመችው የአፍሪካ ቀንድ ጣጣና የኃያላን አገሮቹ ፉክክር ባንድ አፍታ የሚከመረው ኦሮምያ ላይ መሆኑን አልተረዱ ይሆን? ሥልጣን፣ ሙስና ቅብጠትና መሽሞንሞን የቋመጡት የኦሮምያ ፖለቲከኞች ኦሮምያን ባስገነጠሉ ማግስት አንዳች ሳይፈይዱ ሲቃና ሞት እንደሚያውካቸው አውቀውት ይሆን? ሽቅርቅሮቹ – የዝና እና ምቾት ምኞት ሠለባ የሆኑት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሰዎችን ትርጉም የለሽ በሆነ ጦርነት እንደሚማግዷቸው አስተውለው ይሆን?

እንደው ለመሆኑ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ውንድሞቹ ጋር ሆኖ የአድዋው ድል ባለቤት የሆነውን ጀግናውን የኦሮሞ ሕዝብ ለቅኝ ገዥዎች አጎንባሽና ተገዥ ማድረጉ ምን ይፈይድላቸዋል? ሌላው ቢቀር ረዥም እድሜ ያስቆጠረች ኢትዮጵያዊቷን ቤተ ክርስትያን ለሁለት መክፈል ማሰቡ – ከእግዚአብሄር ጋር መጣላት መሆኑን ተረድተውታል? የኤርትራ ፕሬዚዴንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ቢያስገነጥሉም እንኳን አገራቸውን የቅኝ ገዥዎች ርካሽና አስነዋሪ ባህል ማራገፍያ አላደረጓትም። ነጋ ጠባ አሜሪካ የሚመላለሱት ሽሙንሙኖቹ ኦነጋውያን እንደ አቶ ኢሳያስ ድፍረት የተላበሱ ይሆኑ? እንጃ ያጠራጥራል። የኦሮምያ መገንጠል ወርቅ የምትወልደዋን ዶሮ እንደማረድ ያለ በስሜት የሚዳክሩ ሞኞች ምኞት ነው። ኢትዮጵያ ሁሉን መከራ የቻለችው በኢትዮጵያዊነቷ ነው። ሁሉም ይግባው!! አንቀጽ 39 መከራ ቻይነቷን ማኮሰሻ መተት ነው። ታሪክም እኮ ትፋረዳለች።

ወገኖቼ! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እጅግ ረዥም እድሜ አላት። ቤተ ክርስትያኒቱ ዛሬ አጉራ ዘለሎች እንደሚያንቋሹሻት ሳይሆን ለመንግሥት አካላት እውነትን በማስጨበጥና ምሬት በመስጠት እንዲሁም ትምህርትን በሃገሪቱ ከማሠራጨት አንስቶ በጦር አውድማ ከጠላቶችዋ ጋር እስከመፋለም መስዋዕት የከፈለች የእግዚአብሄር ቤት ነች። ከየኔታ እስከ መሪ ጌታ ከቀሳውስት እስከ ሊቀ ሊቃውንት ያሉ የቤተ ክርስትያኒቱ አገልጋዮች ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ የሠሩ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ናቸው።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን – ክርስቶስ ከአብ ያንሳል ያለውን አርዮስ፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል ያለውን መቅዶንዮስ፣ ክርስቶስን ማርያም አልወለደችውም ወላዲተ አምላክ (Theotokos) ልትባል አይገባትም የክርስቶስ እናት (Christokos) ትባል ያለውን ንስጥሮስ እንዲሁም አውጣኪስና ፍላቭያኖስን የመሳሰሉ ሃሠተኞችን ገና ከጠዋቱ ባደባባይ የሞገተች፣ ቀኖናዎችንና ዶግማዎችን ያጸናችና ታላላቅ ገድሎችን ያስመዘገበች ጽኑ ቤተ ክርስትያን ነች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ዛሬም ጽኑ ነች፣ ማንኛውንም መከራ ማለፍ ትችልበታለች።

ኢትዮጵያ የኃይማኖቶች እኩልነት በጽኑ የሚተገበርባት አገር ነበረች። እስላም ክርስቲያኑ ተከባብሮ ተፋቅሮ የሚኖርበት አገር ኢትዮጵያ ነች። ሥርዓትን የሚከተሉ እንደ ዶክተር ደረጀ ከበደ ያሉ ጠንካራ ዘማርያንን ያፈሩ ግብረገብን የሚተገብሩ ጨዋ አማኞችን ያቀፉ የፕሮቴስታንት የእምነት ቤቶች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የዘመኑ መጨረሻ ሆነና ዛሬ የእግዚአብሄር ቤቶች ሆዳቸውን ብቻ በሚያፈቅሩ ተልካሻ ግለሰቦች ተሞሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ጥቅማቸውን ብቻ የሚያሳድዱ እንዳሉ ሁሉ የፕሮቴስታን ቤተ ክርስትያናትም በነዋይ አፍቃሪዎችና በዓይን አውጣ አለቆች እየታመሰች ትገኛለች።

የሁኔታዎች መቀያየር፣ የመንግሥት ጥበቃ መነፈግና የአማኞቿ ድክመት እንጂ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ስትሟገት የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ንዋይን የማምለክ አባዜ በተጠናወታቸው በምዕራቡ ዓለም አሸረጋጆች የሚዘበትባት አልነበረችም። ዛሬ ላይ እውን የሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጋረጡና የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የተባለውን አንጃ ቤተ ክርስትያን ምሥረታ ታስቦበት በእቅድ የተመራ ሤራ ነው። ሁሉም ነገር ከላይ እሰከታች መዋቅራዊ መሆኑ ዛሬ በገሃድ ታየ።

ወገኖቼ! የአምሓራ ነገድ ራሱን አደራጅቶ ወደ ቀድሞ ቁመናው ሲመለስ ሥርዓት እቦታዋ ትመለሳለች። ለኢትዮጵያ መስዋዕት በከፈለችው እንዲሁም ወደ እግዚአብሄር በምታደርሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ላይ ይህ ሁሉ ድፍረት የተፈጸመው የአምሓራው ነገድ ባለመደራጀቱና ባንድነት ባለመቆሙ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። ጠንካራ ድርጅት ተሳዳቢዎችንና ዓይን አውጣዎችን ገደብ ማስያዙ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ያስከብራል።

የአምሓራው ነገድ መፍትሄ የሚያመጣው ዳተኛነቱን አሽቀንጥሮና አላስፈላጊ ምኞቶችን ገድቦ ራሱን ሲያደራጅ ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ አማራው ክርስትና እና እስልምና ኃይማኖቶቹን እያስናቀ በጥቂት አጉራ ዘለሎች ሲዘለፍና ሲናቅ መኖር ብቻ ነው እጣ ፋንታው። የአምሓራ ነገድ ሆይ! “ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ፣ ባትጣፍጥ ግን ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል” የሚለውን የራስህን ብሂል መልሰህ መላልሰህ አጢነው።የመጨረሻው ዘመን ንዋይ አሳዳጆችን፣ ቤተ ሠሪዎችን፣ ጉበኞችንና አታላዮችን ወደ ፊት ያመጣል። የመጨረሻው ዘመን የንዋይን ጫፍ ለመጨበጥ የሚቅበዘበዙትን ያበዛል። እግዚአብሄር በመጨረሻው ዘመን እንድንጠነቀቅ እንጂ ለንዋይና ለጥቅም እንድንገዛ አላዘዘንምና አምሓራዎች – እናስተውል።

Filed in: Amharic