>

በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እጃችሁን ያነሳችሁ ሁሉ፣ ከፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ የውርድት እና የውድቀት ታሪክ ተማሩ!!

በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እጃችሁን ያነሳችሁ ሁሉ፣ ከፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ የውርድት እና የውድቀት ታሪክ ተማሩ!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

  1. እንደ መንደርደሪያ

‘‘… እመብርሃን፣ የጌታዬ እናት፣ ድንግል ማርያም ሆይ … ይኸው ለቃል ኪዳን ምድርሽ፣ ለአስራት አገርሽ- ለእናት ምድሬ ኢትዮጵያ እንባዬን ከደሜ ጋር ቀላቅያለሁና… ይህን በዘረኞቹ ፋሽስቶች ክንድ በሕዝብሽ፣ በአገልጋዮችሽ ላይ እየወረደ ያለውን ግፍና መከራ በልጅሽ ፊት አዘክሪ፣ አሳስቢ፡፡ እናቴ ሆይ አዛኝቱ ያለ አንቺ ማን አለኝ፤ ተስፋዬ ልጅሽ ነውና ‹‹እግዝእትነ ስምዒ ኀዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ሲሉ የኢትዮጵያን ሰቆቃዋን፣ ጣሯንና ጭንቀቷን አሳስቢ ሲሉ ተማፀኑ… ምድሪቱም ለፋሽስት እንዳትገዛ አውገዝውና በመስቀላቸው ባርከው ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡’’

                                      (ሰማዕቱ ብፅዕ አቡነ ጴጥሮስ ዘኢትዮጵያ)

  1. ለ፵ ዓመታት የተረገዘ የፋሽስቶች ቂም በቀል!!

የዓለማችን የታሪክ እምብርትና የሥልጣኔ ቁንጮ የሆነችውን ታላቂቷን ሮማንና መላውን የአውሮፓውያኑን የቅኝ ገዢ ኃይሎች ቅስም የሰበረውንና አሳፍሮ የመለሰውን የ፲፰፻፹፰ቱን የዐድዋውን ሽንፈት ለመበቀል ነበር- ከዐርባ ዓመት በኋላ በፋሽስቱ መሪ በቤኒቶ ሞሶሎኒ ሰራዊቱን እስከ አፍንጫው አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ጦሩን ያዘመተው፡፡

ፋሽስት ኢጣሊያ በዚህ ሁለተኛ የበቀል ዘመቻው ዋንኛ ዒላማው የነበረችው ደግሞ ‘የሰው ልጆች ነጻነትና አንድነት ተምሳሌትና ትዕምርት/ሲምቦል’ የኾነችው- ጥንታዊቷ፣ ሐዋርያዊቷና ኩላዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ነበረች፡፡ የዓድዋውን ጦርነት ከዘመቻው እስከ ድሉ ድረስ በማስተባባርና ሕዝቡ ከፈጣሪው ለተሰጠው ነጻነት በአንድነት በጽናት እንዲቆም በማስተማሯ ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ- በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ክፉኛ ጥርሱን ነክሶባት ነበር፡፡

እናም ጣሊያንና እንዲሁም መላውን አውሮፓ/የቅኝ ገዢ ኃይል አንገት ካስደፋው ከዚህ የታሪክ ቅሌትና የሞራል ስብራት ሮማን ለመታደግ ‘‘እኔ ጀግናዋ አለሁ!’’ በማለት ነበር የፋሽስቱ መሪ ለራሱና ለሕዝቡ ቃል የገባው፡፡ ሞሶሎኒ ኢጣሊያንና መላውን አውሮፓን ሳይወዱ በግድ የሽንፈት ጽዋ እንዲጋቱ ያደረገችውን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመበቀል ሰዓቱ አሁን እንደሆነ በሮም አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ ሲል ነበር የተናገረው፡፡

‹‹ኢትዮጵያን አምላኬ የምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ መዳፌ ሊያድናት የሚችል ከሆነ የእኔንም እግዚአብሔር ልጨምርላት እችላለሁ!››

በተመሳሳይም የምሥራቅ አፍሪካ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ሹም- ጄኔራል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ለአለቃው ለሞሶሎኒ፡- ‹‹ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ራሷን ገጸ-በረከት  አድርጌ አቀርብልሃለሁ፡፡›› በማለት ነበር ኢትዮጵያን/ሕዝቦቿን እና ጥንታዊቷንና ሐዋርያዊቷን የኢትዮጵያን በቤተክርስቲያንን ለኢጣሊያ በገጸ-በረከትነት ለማቅረብ ፋሽስቶች በሮማ አደባባይ የተደራደሩት፤ የተስማሙት፡፡

ሰማይን የሚራገጥ በሚመስል ትዕቢትና ‘የታሪክ ቅሌት’ በፈጠረው ብርቱ ቁጭት ኢትዮጵያን በመዳፉ ስር ለማስገባት ከዐርባ/፵ ዓመታት በኋላ ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የመጣው ፋሽስት ኢጣሊያ- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀንደኛ ጠላቱ ብቻ ሳይሆን ለቅኝ ግዛት የመስፋፋት ዘመቻው ለኢጣሊያም ሆነ ለአውሮፓ አደገኛ እንቅፋት መሆኗን በማሰቡ- በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንና በሕዝቦቿ ላይ ብርቱ የጭካኔ ክንዱን አሳረፈባት፡፡

ፋሽስት ኢጣሊያ በዚህ የበቀል ዘመቻው እስከ አፍንጫው ከታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰማይ እየሰነጠቁ ሞትን የሚተፉ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከሉ የመርዝ ጭስ አረሮችን የተሸከሙ የጦር አውሮፕላኖችን ጭምር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡

በእነዚህ በሰማይ ላይ በሚምዘገዘጉ የፋሽስት ኢጣሊያ አውሮፕላኖች እንግዳ የኾነው የኢትዮጵያ ሕዝብም በጊዜው በእጅጉ ተደናግጦ ነበር፡፡ በእነዚህ ሰውነትን አሳብጠውና ብጥስጥስ አድርገው በሚገድሉ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሞት ላንቃቸውን ከፍተው የእሳት አሎሎን በሚያዘንቡ አውሮፕላኖች ባደረሱት ዘግናኝ እልቂት እጅጉን ግራ የተጋባው የአገሬ ሕዝብም በወቅቱ ‹‹ይህ ምን ዓይነት መዓት፣ ምን ዓይነት ጉድ ነው!›› በሚል እንዲህ መቀኘታቸውንና ፈጣሪያቸውን መሞገታቸውን የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡-

ከኢትዮጵያ ጸሎት ጣሊያኖች በለጡ፣

በዐርባ ዘመናቸው ክንፍ አውጥተው መጡ፡፡

የአምላክን መኖሪያ፣ የልእልናው መገለጫ የኾነውን ሰማይን በተዳፈሩትና ሰማዩን እየሰነጠቁ ሞት የሚያዘንቡትን፣ የእሳት መርዝ የሚተፉትን ትንግርትና ታኣምር የኾኑባቸውን የጦር አውሮፕላኖች የአገሬ ሰው በሌላኛው ቅኔው እንዲህ ሲሉ ነበር በአግራሞት የተቀኘላቸው፡-  

የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣

አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፣

አምላክ ለአንተው ፍራ፣

በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡

ይህን በአሰቃቂ ኹኔታ ሰውነትን በጣጥሶ የሚገድለውን የመርዝ ጭስ ፋሽስት ኢጣሊያ ለመጠቀም የፈለገው የኢትዮጵያውያንን የውጊያ፣ የመከላከል ሞራልና ቅስም በመስበር ቅኝ ተገዢ ለማድረግ ኾን ብሎ አስቦና አልሞ ነበር፡፡ በወቅቱ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ መጠቀም ስለሚገባው የመሳርያ ዓይነት በምስጢር አስተላልፎት የነበረውን መልእክት በተመለከተ የአሜሪካው ‘ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ’ የሚገኝ አንድ ታሪካዊና ምሥጢራዊ ሰነድ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ 

‹‹ተልእኳችን እንዲሳካ ከተፈለገ በጠላት ላይ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ከዚህም በላይ የሞራል ስብራት የሚያስከትለውን ልዩ የሆነ ፈሳሽ ቦምብና መርዝ ሼል እንደፈለጉ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡››

ዘረኛው የፋሽስት መንግሥት ይህን እኩይ ተልእኮውን ከግብ ለማድረስ በማስብም በተለይም ሕዝቡ ለነጻነቱ ሳይከፋፈል በአንድነት በጽናት ይቆም ዘንድ የሚያስተምሩትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶችንና ሊቃውንት በአደባባይ ላይ በግፍ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ አድርጓል፡፡

ለአብነትም፤ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም እንዲሁም ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኾኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና ምእመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የኢጣሊያ ፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው እኩይ የዘረኝነት ፖሊሲው/አቋሙ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የፋሽስቱ ሞሶሊኒ ጭካኔ፣ አውሬነት በዚህ ብቻ የተገታ አልነበርም፡፡ በተለምዶው ‹‹የአካፋው ሚካኤል›› ብለን የምንጠራው የካቲት ፲፪ ቀን በአዲስ አበባና በነዋሪዎቿ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳምና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አገልጋዮች ላይ ፋሽስቱ ግራዚያኒ ያደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋና እልቂት አስመልክቶ በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ- በዓይኑ ያየውንና የታዘበውን የፋሽስቶቹን ጭካኔና ግፍ በማስታወሻው እንዲህ ገልጾታል፡-

ኢትዮጵያውያን በየመንገዶቹና በየመኖሪያ ቤታቸው እንደ አውሬ እየታደኑ በመላ ከተማዋ ይደበደቡ፣ በጥይት ይቆሉ፣ በሳንጃ ይዘከዘኩና ነፍሳቸው እስክትወጣ ድረስም በዱላ ይቀጠቀጡ ነበር፡፡ መኖሪያ ቤታቸው በሚወረወር ነበልባልና ጋዝ በማርከፍከፍ እንደዚሁም በሰዎቹ ላይ ተቆልፎባቸው ከነሕይወታቸው እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ጭፍጨፋና ጭካኔ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን፣ መነኮሳትንና ቀሳውስትንም እንኳን አልመረጠም፡፡ በሁሉም የከተማው ማዕዘናት ከአራት ሺ በላይ ቤቶች እሳት ስለተለኮሰባቸው ከተማው በሌሊት የቀትር ብርሃን መስሎ ይታይ ነበር፡፡ የአራዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንም እሳት የተለኮሰበት ሲሆን ሕንፃውን ለማውደምም ሃያ ፈንጂዎች ተቀብረውበት ነበር፡፡

ይህ በአዲስ አበባና በነዋሪዎቿ የተመዘዘው የፋሽስቱ የጥፋትና የጭካኔ ሰይፍም ወደ ጥንታዊው ደብረ ሊባኖስ ገዳም ዘልቆ የገዳሙ መናኒያን፣ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ተማሪዎች በግፍ እንዲገደሉ፣ እንዲጨፈጨፉና እንዲጋዙ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ- ‘‘የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት፤’’ በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የጭፍጨፋ ርምጃ ኢጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪ፣ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹‹… የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገ/ማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ …፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡

  1. በግፍ የፈሰሰ የንጹሐን ደም ሲፋረድ!!

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስቶች የፍርድ ውሳኔ ለማሕተባቸው፣ ለቃል ኪዳናቸው ታምነው ለአገራቸው በተሠዉበት/ሰማዕት በሆኑባት በዛች ቀን እንዲህ ነበር ያሉት፤

… እምዬ ኢትዮጵያ … እናት አገሬ ደሜ ለነፃነትሽ፣ ለክብርሽ፣ ለአንድነትሽ ንጹሕ የፍቅር መሥዋዕት ሆኖ የፈሰሰ ነውና ጽኑና ኃያል በሆነው አምላክሽ ፊት ልክ እንደ አቤል ደም ለግፉአን ፍርድን የሚሻ፣ ፍትሕን የሚጠይቅ ይሁን! ሲሉ ዓይናቸውን ወደ ሰማየ ሰማይ አቅንተው አምላካቸውን እግዚአብሔርን በዕንባ ተለማመኑት፣ ተማጸኑት፡፡

እመብርሃን፣ የጌታዬ እናት፣ ድንግል ማርያም ሆይ … ይኸው ለቃል ኪዳን ምድርሽ፣ ለአስራት አገርሽ- ለእናት ምድሬ ኢትዮጵያ እንባዬን ከደሜ ጋር ቀላቅያለሁና… ይህን በዘረኞቹ ፋሽስቶች ክንድ በሕዝብሽ፣ በአገልጋዮችሽ ላይ እየወረደ ያለውን ግፍና መከራ በልጅሽ ፊት አዘክሪ፣ አሳስቢ፡፡

እናቴ ሆይ አዛኝቱ ያለ አንቺ ማን አለኝ፤ ተስፋዬ ልጅሽ ነውና ‹‹እግዝእትነ ስምዒ ኀዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ሲሉ የኢትዮጵያን ሰቆቃዋን፣ ጣሯንና ጭንቀቷን አሳስቢ ሲሉ ተማፀኑ… ምድሪቱም ለፋሽስት እንዳትገዛ አውገዝውና በመስቀላቸው ባርከው ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡

የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስና የጎሬው የአቡነ ሚካኤል፣ የበርካታ የቤክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ለነጻነት ክቡር መንፈስ የፈሰሰ ዕንባቸውና ደማቸው በኢትዮጵያ ተራሮች፣ ሸንተረሮች፣ ዱርና ጫካ ታላቅ የሆነ የነጻነት ደወልን አሰማ፣ አስተጋባ፡፡ ‘እምቢ ለነጻነቴ’ ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የፋሽስት ኢጣሊያን በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋና በሃይማኖት የመከፋፈል ዘመቻ ሳይበግራቸው ነፃነታቸውን በደማቸውና በአጥንታቸው ለማስመለስ ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ የእናት ኢትዮጵያን ሕመሟን፣ ሥቃይዋንና መከራዋን በዕንባቸውና በላባቸው፣ በደማቸውና በአጥንታቸው ታላቅ መሥዋዕትነት ይካፈሉ ዘንድ ዱር ቤቴ አሉ፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት በአገራቸው ዱርና ተራራ ተሰደዱ፣ ሌሎች ደግሞ በዕንባና በለቅሶ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከፋሽሽት ጭካኔ ይታደጋት ዘንድ ሱባኤ ገቡ፡፡ አምላካቸውን መማጸን ያዙ፡፡ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር ሱልጣን ገዳምም ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን መናኒያን፣ መነኮሳት፣ ካህናትና አገልጋዮችም የኢትዮጵያ አምላክ ለአገራቸው ነጻነትን ይመልስላት ዘንድ በጸሎት ተጋድሎ ተወሰኑ፡፡

በሌላ በኩልም- የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትንና የፍቅር መቅደስ በደማቸው ዳግም ሊቀድሱና ሊያከብሩ በነፍሳቸው የተወራረዱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች- ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግረውም በሮም አደባባይ በደማቸው ሕያው ታሪክን ጻፉ፡፡ የኦሮሞ ምድር ፍሬ የሆኑት ጀግናው ኢትዮጵያዊ ኮ/ል አብዲሳ አጋና ኤርትራዊው ዘርአይ ደረስ፡- በባዕድ ምድር፣ በግዞት እንኳን ሆነው፡- ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮዬ ይጣበቅ፡፡›› በማለት የእናት ምድራቸውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማቸውን በሮም አደባባይ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ኢትዮጵያዊነት የአንድነት እና የፍቅር መቅደስ መሆኑን በደማቸው መሰከሩ፡፡

ከማይጨው ዘመቻ መልስም ኢየሩሳሌም የሚገኘውን ዴር ሱልጣን ገዳምን ተሳልመውና የጥቂት ቀናት ቆይታ አድርገው መንገዳቸውን ወደ ጄኔቭ ያደረጉት ዐፄ ኃይለ ሥላሴም የሕዝባቸውን ግፍና መከራ በተመለከተም- በሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡ ንጉሡ በንግግራቸውም የኢጣሊያ የፋሽስት መንግሥት በአገራቸው ሕዝብ ላይ እያደረሱ ያሉትን ግፍና በዓለም መንግሥታት የተከለከለ መርዛማ ጭስ የአገራቸው ሕዝብ እየፈጀ መሆኑን በመጥቀስ ይሄን ዘግናኝና አሰቃቂ መዓት ኃያላኑ ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ በብርቱ ተማፀኑ፡፡ የሕዝባቸውንም አቤቱታ በአደባባይ አሰሙ፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቤቱታና የሕዝባቸው ለቅሶና መከራ ግን ለአውሮጳውያኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንደውም ለአንዳንዶቹ አውሮጳውያን ሀገራት ራሷን ከነጭ/ከአውሮፓውያን ጋር እኩል አድርጋ ለምታስበው ኢትዮጵያ ይህ ቅጣት የሚገባ፣ ልኳን እንድታውቅ የሚያደርግ ጦርነት መሆኑን በማመን ለፋሽሽቱ ሞሶሎኒ በግልጽና በስውር ‘‘በርታልን!’’ ሲሉ ቀኝ እጃቸውን አዋሱት፡፡

በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ተግባራዊ ምላሽ ያላገኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም፣ ‘‘… ይህን የአገሬንና የሕዝቤን ግፍና መከራ ችላ ብላችሁ ብታልፉት ታሪክና እግዚአብሔር ፍርዳችሁን ይሰጣችኋል …፡፡’’ ሲሉ ትንቢታዊ የሚመስል ታሪካዊ ንግግርን አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያን በአምባገነኑ የፋሽስት ሠራዊት መወረርና የሕዝባችንም ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮጳውያኑ አገራት ብዙም ሳይቆይ ከጀርመን በተነሳው በናዚ ሂትለርና በፋሽስቱ መሪ ሞሶሎኒ የጦር ክተት ታወጀባቸው፡፡

አምባገነኖችን፣ ግፈኞችን በጊዜው ተው፣ እረፉ! ለማለት ሞራል፣ ጉልበት ያነሰውና ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› የሚል ፖለቲካዊ ስላቅን ያተረፈው ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽንም›› በዓይኑ ፊት በአምባገነኖቹ ሂትለርና ሞሶሎኒ አገራት በግፍ ሲወረሩ የኃይለ ሥላሴ ትንቢታዊ ንግግር እየተፈጸመ እንደሆነ በወቅቱ ቀውሱን የታዘቡ ፖለቲከኞችና የታሪክ ምሁራን በሰፊው ጻፉ፣ መሰከሩም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ኢ-ፍትሐዊ ወረራና ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮጳውያን በራሳቸው ሲመጣ ግን ለመታገሥ አልቻሉም ነበር፡፡ ሳይወዱ ተገደው ወደ ጦርነት ገቡ፣ እናም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮጳ ሊፈነዳ ግድ ሆነ፡፡

የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች እንደጻፉት- ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት ሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኃይል ስትወረር ያሳየው መለሳለስና ደካማ አቋም እንደ አንድ ትልቅ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል መሆኑን ያስመሩበታል፡፡ ‹‹አክሲስ ፓወር›› በሚል በጀርመኑ ሂትለር፣ በፋሽስቱ ሞሶሎኒና በቶኪዮ/ጃፓን የተባባረ ኃይል ዓለምን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ለማድረግ የተነሡ ሮምንና ጀርመንን ለመመከት እንግሊዝና ፈረንሳይ ሌሎችን አገሮችን በማስተባበር ወደ ጦርነት ከተቱ፡፡

የኢትዮጵያና የሕዝቦቿም ለቅሶ በእግዚአብሔር ፊት ታሰበ፡፡ የግፍ ጽዋም ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ እናም፣ ‹‹ስለ ድሆች፣ ስለ ምድሪቱ ግፉአን፣ ፍትሕንና ፍርድን ስለተነፈጉ ምንዱባን እግዚአብሔር አሁን ይነሳል ይላል››፣ ‹‹እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡›› ተብሎ በአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት የተነገረለት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የመዓቱን ጽዋ በአውሮጳ ምድር ላይ አፈሰሰው፡፡ አውሮጳ/ዓለም እስከዛሬ አይቶት በማያውቀው መከራና ሰቆቃ ውስጥም ተዘፈቀ፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትና የአካል ጉዳተኛ የሆኑበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሎ የናዚውን ሂትለርና የፋሽስቱን ሞሶሎኒ ታሪክ በውርደት ደመደመው፡፡ ‘‘… የትኛው አምላክ ነው ኢትዮጵያን ከኃያሉ ክንዴ የሚያስጥላት’’ – ያለው ሞሶሎኒም በሮም አደባባይ አይወርዱ ውርደትን ተዋርዶ የሞት ስቅላት ተፈረደበት፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ገጸ-በረከት አድርጌ አቀርብልሃለሁ!›› ብሎ ለአለቃው ለሞሶሎኒ ቃል የገባው ማርሻል ግራዚያኒም- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የእምነት ጽናት፣ በአገልጋዮቿ ሰማዕትነት፣ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአርበኞቻችን የነጻነት ተጋድሎ ከንቱ ሆነ፡፡ የፋሽስት ኢጣሊያ ሰራዊትም በመጨረሻ ተሸንፎ፣ አፍሮና ተዋርዶ አገራችንን ለቆ ወጣ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በልጆቿ ደም የተቀደሰው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማዋ ዳግመኛ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡

እናም፤ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስ፣ የአቡነ ሚካኤል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት፣ ሊቃውንት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና አገልጋዮች- ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት፣ ለማሕተማቸው/ለቤተክርስቲያን ጽኑ የፍቅር ቃል ኪዳን ሲሉ በግፍ የፈሰሰው የሰማዕታቱ ደም፤

ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች- የእነ አብዲሳ አጋ፣ ዘርዓይ ደረስ፣ ጄ/ል ጃጋማ ኬሎ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ የራስ አበበ አረጋይ፣ ሸዋረገድ ገድሌ፣ የወ/ሮ ልኬየለሽ በያን፣ የእነ ሲሊቪያ ፓንክረሰት፣ የአፍሪካ አሜሪካዊው የኮ/ል ጆን ሮቢንሰን፣ የጋናው ክዋሜ ንኩርማ፣ የኬንያው የጆሞ ኬንያታ… ወዘተ. በአጠቃላይ የአፍሪካ አሜሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝብ የፀረ-ፋሽስት የአርበኝነት ተጋድሎና የፍትሕ ድምፅ የተነሳ- ኢትዮጵያውያን አርበኞች በሮም አደባባይ ሳይቀር በደማቸው ከፍ ያደረጓት ሰንደቀ ዓላማችንን በአገራችን ሰማይ ላይ ዳግመኛ በክብር ከፍ ብላ ተውለበለበች፡፡

ዳግመኛ ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው የሚያንቀላፋ እንጂ የማይሞት ጽኑና ሕያው የአንድነትና የፍቅር ውል ቃል ኪዳን መሆኑ ተበሰረ፡፡ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጽኑ ቃል ኪዳን ጋር የተገዳዳሩ፣ ሕዝቡን ለነጻነቱና ለአንድነቱ ጸንቶ እንዲቆም በምታስተምረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ላይ እጃቸውን ያነሱ ሁሉ- ዕድል ፈንታቸው፣ ጽዋ ተርታቸው ድቀት፣ ውርደትና ጥፋት መሆኑ በግልጽ ታየ፡፡

የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትና የፍቅር መቅደስን ሊያረክሱና ሊያራክሱ የተነሡ ሁሉ ለድቀት፣ ለውርደትና ለአሳፋሪ ሽንፈት መዳረጋቸው የታወቀ ሐቅ መሆኑ ተመሰከረም፡፡ በምንም የማይረታና የማይሸነፍ በዓድዋ የተበሰረው ጽኑ የኢትዮጵያዊነት ታላቅ መንፈስም ዳግመኛ በፋሽስቱ ሞሶሊኒ ውርደትና ውድቀት የተነሣ ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡

ይህ የኢትዮጵያዊነት ክቡር የአንድነትና የፍቅር መንፈስ የቋራው ካሣ/ቴዎድሮስ በመቅደላ አፋፍ የተሰውለት፣ አፄ ዮሐንስ፣ ‘‘ኢትዮጵያ አገርህ ልጅህ፣ ሚስትህ፣ እናትህ፣ ዘውድህ፣ ክብርህና መቃብር ናት!!’’ በሚል በመተማ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጦር የሰጡለት፣ እምዬ ምኒልክ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች በዓድዋ ጦር ግንባር በደማቸው የቀደሱት፣ ያከበሩትና ያወደሱት ነው … ይህ ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያዊነት የአንድነት፣ የፍቅር ቃል ኪዳን፣ ክቡርና ታላቅ መንፈስ!!

እናም እጃችሁን በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያነሳችሁ ሁሉ ከፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ፣ ከግራዚያኒ፣ ከዘረኞቹና ከአምባ ገነኖቹ ውርድትና ውደቀት ትማሩ ዘንድ ታሪክን ዋቢ አድርግን እንዲህ በድፍረት ልንነግራችሁ እንወዳለን!!

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!!

Filed in: Amharic