>

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ለተፈጸመባት ጭፍጨፋ ውድመት የኢጣሊያን መንግሥት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሣ ሊከፍል ይገባዋል!!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፋሽስት ለተፈጸመባት ጭፍጨፋ ውድመት የኢጣሊያን መንግሥት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሣ ሊከፍል ይገባዋል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(የሪፖርተር ጋዜጣ እንዳወጣው)

  1. እንደ መንደረደሪያ

የዛሬው ዕለት የካቲት 12 ቀን (የሰማዕታት ቀን) በኢትዮጵያ በታሪክ የፋሽስቶች ዘረኝነት፣ አውሬያዊ ጭካኔና አረመኔነት በገሃድ የታየበት ነው፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ አድርጎ ለአምስት አመት በተቆጣጠረበት ወቅት 1929 ዓ.ም. በየካቲት 12 እለተ አርብ ነበር።

የዐፄ ኃይለ ሥላሴን ወደ እንግሊዝ መሰደድ ተከትሎ እና የሙሶሊኒን የቅኝ ግዛት ሕልም እንዲያሳካ የኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው ግራዚያኒ፣ የኔፕልሱን ልዑል መወለድ አስመልክቶ ለችግርተኛ ቤተሰቦች ገንዘብ እሰጣለሁ ብሎ በገነተ ልዑል ቤተመንግስት (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ) በርካታ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከተጋባዥ እንግዶቹም መካከል የጣልያን ሹማምንት የሜትሮፖሊታን ጳጳስ አቡነ ኪርል እና ሌሎች የኢትዮጵያ መኳንንቶች ተገኝተው ነበር።

ብራማ በነበረችው በዛች የወረኻ የካቲት አርብ የተገኙትም ኢትዮጵያውያን ከጠዋት ጀምረው አንድ በአንድ ቤተመንግሥቱ ግቢ መሰብሰብ ጀመሩ። እስከረፋዱም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሦስት ሺህ ያህል ነዋሪዎች በተገኙበት የግራዚያኒ መረሐ ግብር ተጀመረ። የዕለቱ አጀማመር ሲታይ ሊመጣ ያለውን የኀዘን ድባብ የገመተ ሰው ይኖራል ብሎ ለማሰብ ያዳግታል። ጥቂት ቆይቶ እኩለ ቀን ገደማ ሊሆን አካባቢ በዋናው በር በኩል ቦንብ ፈነዳ፣ ሁለተኛም ፈነዳ። ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ከየአቅጣጫው ጩኸት አስተጋባ። ሦስተኛ ቦብም ግራዚያኒ እና መኳንንቱ ከተቀመጡበት ጠረጴዛ አጠገብ ሲወረወር ግራዚያኒ ጠረጴዛ ስር ወደቀ። የተወሰኑ የጣልያኖቹን ሹማምንት መታ።

ቦምቡን የጣለው ከጣልያኖቹ ዘንድ በአስተርጓሚነት ይሠራ የነበረ አብርሃ ደቦጭ እና ጓደኛው ሞገስ አስገዶም የሚባሉ የኤርትራ ክፍለ ሀገር ተወላጅ ወጣቶች ነበሩ። በጥቅሉ ሰባት ቦምቦች ፈነዱ። ወዲያው ካርቴሲ ወደኢትዮጵያውያኑ መኳንንት ሽጉጡን አነጣጥሮ የመጀመሪያዋን አንድ ጥይት ተኮሰ። ካራ ቢኔሬዎችም (የጣሊያን የሲቪል ጠባቂዎች) ምሳሌውን ተከተሉ። በጥቂት ጊዜ ውስጥም ሶስት መቶ ሬሳዎች በዛ ግቢ ውስጥ ተከመሩ። ሀይለኛና ተገቢ ያልሆነ ጭፍጨፋ ነበር። ሽማግሌዎች፣ አይነስውራን፣ እግር የሌላቸው ለማኞች፣ ድሆች እናቶች እስከልጆቻቸው ነበሩበት። ሰላሳ ያህል ሰዎች ቆሰሉ። ለሶስት ሰአታት ያህል ያለቋረጥ በግቢው ውስጥ ተኩስ ተከፈተ። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ባለጥቁር ሸሚዞች፣ የጣልያን ሾፌሮች የቅኝ ግዛቱ ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን ይፈጁት ጀመር።

በወቅቱ ፋሽሽት በሕዝቡ ላይ ያደረሰውን እጅግ አረመኔያዊ የኾነ ጭካኔና እልቂት በተመለከተ በወቅቱ አበባ የነበረ አንድ አውሮፓዊ ሐኪም እንዲህ ነበር የገለጸው፤

‘‘… ምን ዓይንት አጨካከን ነው፣ ደም በመንገድ ላይ እንደ ውኃ ሲፈስ ያየኹት የዚያን ጊዜ ነው፡፡ የወንዶች፣ የሴቶች፣ የልጀሆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል፡፡ ወዲያው ከባድ የቃጠሎ ጭስ አዲስ አበባን ፅልመት አለበሳት፡፡ የኗሪዎች ቤት ከተፈሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጥ እንዳሉ እሳት ተለቀቀባቸው፡፡ ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤኒዚንና ዘይት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየረስ እሩምታ ይገድሉታል፡፡

በዓለም ጦርነት ጊዜ ቁስለኛ ለማንሳት ከግንባር ከቀደመው ጦር ጋር አምቡላንስ ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ በሌላም ጦርነቶች ውስጥ ተካፋይ ኾኛለኹ፡፡ በሕይወቴ እንደ አዲስ አበባ ያለ እልቂት ግን አላየሁም፡፡’’

የፋሽስቱ ተወካይ ግራዚያኒ በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ላየ ስለወሰደው ርምጃ አስመልክቶ በሮማ ላለው ቅኝ ግዛት ሚ/ር በቁጥር 14-1154 ባስተላለፈው የቴሌግራም መልእክት እንዲህ ነበር ያለው፤

‘‘እነኚህ ጥቁሮች [ኢትዮጵያውያን] የኛን ወታደር ሲያዩ ‘ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!ይላሉ፡፡ ይህን የሚሉትም ለመቀጣጫ እንዲሆኑ ሁሉንም አስጨርስኳቸው፡፡’’ ብሏል፡፡ በዚያው ዘመን እ.ኤ.አ. በየካቲት 22 ቀን የወጣው የሮም ጋዜጣ ‘‘ዴል ፖፖሎ’’፤ ‘‘የአዲስ አበባ አጋማሽ በአሰሳው ጸድቷል፣ 2000 ኢትዮጵያውያን ተይዘው ወደ ደናኔና ወደ ሌሎች ማሰሪያ ቦታዎች ተልከዋል፡፡’’ ሲል ዘግቦ ነበር፡፡

በተመሳሳይም ጋዜጠኛው ቺሮ ፖጃሊ ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ቤ/ክ ላይ ስላደረጉት ግፍና ጭካኔ የካቲት 13 ቀን በአራዳ ጊዮርጊስ ቤ/ክ የሆነው ጭካኔ መሠረት አድርጎ እንዲህ ዘግቦት ነበር፡፡ ‘‘ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ ውስጥ ሰዎች መደበቃቸው ስለተሰማ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ቤኒዚን ተርከፍክፎ እሳት ተለቀቀበት፡፡ የቤተክርስቲያኑ ንዋያተ ቅድሳት- መጻሕፍትና ሥዕሎች በእሳት ነደዱ፡፡ ከቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከእሳቱ ለመሸሽ 50 ያህል ሰዎች ሲወጡ ተያዙና ከቤተክርስቲያኑ ጓሮ ተወስደው በቦምብ እንዲገደሉ ተደረገ፡፡’’

  1. ለአርባ ዓመታት የተደገሰ የፋሽስቶች ቂም በቀል      

ፋሽስት በዓለም ሁሉ ፊት ሮማ የደረሰባትን ታላቅ እፍረትና ሽንፈት ለመበቀል እስከ አፍንጫው የታጠቀ ዘመናዊ ጦሯን በቫቲካን ጳጳሳት አስባርካ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው፡፡ የሞሶሊኒ ወደ ኢትዮጵያ የላከው ኃይል በጦር መሣሪያ ብዛትም ሆነ ዘመናዊነት በቂ ወታደራዊ ሥልጠና ከሌለው ከአገራችን የጦር ሰራዊት ጋር ፈጽሞ ማይወዳደር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ የኢጣሊያ ጦር ሠራዊት እስከ አፍንጫው ከታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሰማይ እየሰነጠቁ ሞትን የሚተፉ የመርዝ ጭስ አረሮችን የተሸከሙ የጦር አውሮፕላኖችን ጭምር የታጠቀ ነበር፡፡

ይህን በአሰቃቂ ኹኔታ ሰውነትን በጣጥሶ የሚገድለውን የመርዝ ጭስ ፋሽስት ኢጣሊያ ለመጠቀም የፈለገው የኢትዮጵያውያንን የውጊያ፣ የመከላከል ሞራልና ቅስም በመስበር ቅኝ ተገዢ ለማድረግ ኾን ብሎ አስቦና አልሞ እንደነበር ታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በወቅቱ ፋሽስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ መጠቀም ስለሚገባው የመሣርያ ዓይነት በምስጢር አስተላልፎት የነበረውን መልእክት የአሜሪካው ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ የሚገኝ ወታደራዊ፣ ምሥጢራዊ ሰነድ እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡ 

‹‹ተልእኳችን እንዲሳካ ከተፈለገ በጠላት ላይ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ከዚህም በላይ የሞራል ስብራት የሚያስከትለውን ልዩ የሆነ ፈሳሽ ቦምብና መርዝ ሼል እንደፈለጉ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡››

ፋሽስት በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. ዳግመኛ ወረራው በበቂ ኹኔታ ተዘጋጅቶና የዐድዋውን ሽንፈት በሚገባ ለመበቀል የመርዝ ጋስ ጭስ ሣይቀር ታጥቆ ነበር የመጣው፡፡ በተጨማሪም ፋሽስት ሕዝቡን በዘር፣ በጎሳና በቋንቋ በመከፋፈል በአንድነቱ እንዳይቆምና እንዲሁም ስለ አንድነቱና ነጻነቱ የሚያስተምሩና በጽናት እንዲቆሙ የሚመክሩ እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉትን የሃይማኖት ተቋማት ለማዳከምና ለማፍረስ ከተቻለም በሮም ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ለማድረግም ከፍተኛ የሆነ ዘመቻን ከፍቶ ነበር፡፡

ፋሽስት በዚህ ዘመቻው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ዋንኛ ዒላማው አድርጓት ነበር፡፡ የሰማዕታቱ የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል የግፍ ግድያ፣ የበርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መዘረፍና መውደም እንዲሁም ደግሞ የበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኾኑ ካህናት፣ መነኮሳት፣ መናኒያን፣ ዲያቆናትና ምእመናን ጭፍጨፋም የዚሁ የኢጣሊያ ፋሽስት መንግሥት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያራምድ የነበረው የከፋና እኩይ አቋሙ ማሣያዎች ናቸው፡፡

ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሊኒ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የነበረውን ንቀትና ጥላቻ ያሳየበትና ቢቻለውም ቤተ ክርስቲያኒቱን በፋሽስት ወይም በሮማ አስተዳደር ሥር እንድትሆን የነበረውን ሕልም የሚያጋልጠው እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 16/1935 በአስመራ ለሚገኘው ለጦር አዝማቹ ለማርሻል ባዶሊዮ ያስተላለፈው ጥብቅ ምሥጢራዊ ቴሌግራም እንዲህ ይነበባል፡-

በቁጥር 421M እና በቁጥር 426 ዳግም ያስተላለፍክልኝን የምስጢር ቴሌግራም ደርሶኝ በሚገባ አይቼዋለሁ፡፡ የአክሱም ገዳም ተቀደሰ ሥፍራ እንደመሆኑና ካለውም ጥንታዊ ታሪክና ቅርስ አኳያ በጦር መሣሪያም ሆነ በማናቸውም ዓይነት ወረራ እንዳይነካና የኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ መቆየት አለበት የሚለውን የውጭ መንግሥታት አሳብ ከምንም አልቆጥረውም ማለትህና ወደፊትም ይህን አሳብ የምቀበል ሰው አይደለሁኝም ማለትህ ትክክለኛ ነህ፤ ጥሩም አድርገኻል፡፡ አሁን የቀረህ ደግሞ የአክሱምን ገዳም ካህናትና መነኮሳት ብዛታቸውንና ማዕረጋቸውን ጠይቀህ ካወቅህ በኋላ በገናናዋ በሮምና በሞሶሎኒ ዙፋን ሥር እንተዳደራለን የሚሉ እንደሆነም በውል አጽፈህና እያንዳንዳቸውን አስፈርመህ ቃል የገቡበትን ሰነድ ወደ እኔ እንድትልክልኝ ነው፡፡

ፋሽስት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ግፍና መከራ እንዲህ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እጅግ አሳዛኙ ነገር የቫቲካን ሃይማኖት አባቶች ለሞሶሎኒ የግፍ ወረራ ድጋፍ ማድረጋቸውና ጦርኑም ባርከው መላካቸው በታሪክ የተመዘገበ የቫቲካን ካቶሊካውያን የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ እፍርትና ቅሌት የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ የእነኚህን የቫቲካን የሃይማኖት መንፈሳዊ መሪዎችንና አባቶችን ቅሌት በወቅቱ የታዘበ ኤሊክ ሲንድሩም የተባለ ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ለሮማው ፖፕ በጻፈው ደብዳቤው እንዲህ ሲል ነበር ኀዘኔታውን የገለጸው፡-

… ቅዱስ ሆይ እኔ በሰሜን አገር የተወለድሁ አንድ ፕሮቴስታንት ስዊድናዊ ነኝ፡፡ … እርስዎ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ነዎት፡፡ ካቶሊክ ማለት ደግሞ የሁሉም ማለት ናት፡፡ ዛሬ እንግዲህ የእርስዎ ቤተ ክርስቲያን  በእውነት የሁሉም ናትን?! እርስዎ ከሞሶሎኒ ጋር ሆነው ከሌላው ዓለም ጋር በጠብ አሉ፡፡ እርስዎ የሚመሯቸው ጳጳሳት ኢትዮጵያ ለኢጣሊያን ቅኝ አገር እንድትሆን የሚገባ ነው ብለው ተናገሩ፡፡ ዘመቻውንም የተቀደሰ ዘመቻ ነው በማለት ለዘመቻ የተዘጋጁትን ታንክና ጦር መሳሪያዎች ባረኩ …፡፡

እርስዎ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሰዎች አገራቸውን ለመጠበቅ ቢሰበሰቡ የኢጣሊያ የአይሮፕላን ቦምብ ጥርግ አድርጎ ቢያጠፋቸው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ነው ብለው ያስባሉን!? ሴቶችንና ሕፃናትን በመርዝ ጭስ ሲፈጅ እግዚአብሔርን ያገልግላሉ ብለው ያስባሉን!? እርስዎ የዓለም ሁሉ አባት ነኝ ሲሉ ሳለ የሞሶሎኒ ባሪያ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ጸሎት ልታሳርግ አትችልም፡፡ ሌላው ዓለም እንደዚሁ ወደ እርስዎ አምላክ ሊጸልይ አይችልም፡፡

እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰውዬው ለሞሶሊኒ የሚታዘዙ ሆነዋልና፡፡ እርስዎ መናገር በተገባዎ ጊዜ ዝም አሉ፡፡ አሁንም በቅርብ የገና በዓል ነው፡፡ ለግፍ ጦርነት ወርቃቸውን የሰጡ ጳጳሳትም እንግዲህ ‹‹ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በምድር ላይ ሰላም ይሁን፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ ይሁን!›› ብለው ሊዘምሩ ናቸው፡፡ ይኽንንም መዝሙር ሲያዜሙ በደረታቸው ላይ የወርቅ መስቀል ሳያደርጉ አይቀርም፣ ነገር ግን በጀርባቸው ላይ የእንጨት መስቀል ቢሸከሙ በተሻላቸው ነበር …፡፡

የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ጭካኔና ግፍ ለዓለም ሁሉ በማጋለጥ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሊኒ በሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለምስራቅ አፍሪካ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት ‹Ethiopia and Eritrea› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ጠቅሰውታል፡-

… The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues. All prisoners have been shot. Inexorable reprisals have been effected against the populations guilty, if not complicity, at least of lack of favorable attitude. A telegram of March 1, 1937.

ትርጉም፡- ‹‹በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ብዙዎችን እንዲፈሩና እንዲሸማቀቁ አድርጓል፤ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ለኢጣሊያን እንዳይገዛ ሕዝቡን በሚያነሣሡና በዱር በገደል በአርበኝነት በተሰማሩት ፋኖዎችም ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል . . . ፡፡››

በወቅቱ በግራዚያኒ ላይ ለተደረገው የግድያ ሙከራ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እጃቸው አለበት በሚል በገዳሙ መነኮሳትና አገልጋዮች ላይ የተወሰደውን የግድያ እርምጃ ኢጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አልቤርቶ ሰባኪ Ethiopia Under Mussolini: Fascism and the Colonial Experience በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹‹… የገዳሙ መነኮሳት በሙሉ፣ የገዳሙ አለቃ አባ ገ/ማርያም ወ/ጊዮርጊስ ጭምር እንዲገደሉ አዘዘ፡፡ ግንቦት 21 ቀን 1937 ጄኔራል ፒየትሮ ማሌቲ በትዕዛዙ መሠረት 297 መነኮሳትን አስረሸነ፡፡ ወደ 153 የሚጠጉ መምህራን፣ ዲያቆናትንና ተማሪዎችን ወደ ደብረ ብርሃን ከተጋዙ በኋላ የሴራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ግንቦት 26 ቀን እንዲረሸኑ ተደረገ …፡፡›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ፋሽስት የደብረ ሊባኖሱ ግድያና ጭፍጨፋ የአቡነ ተ/ሃይማኖት ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት ግንቦት ፲፪ ቀን ነበር እንዲሆን ያዘዘው፡፡ ከበዓሉ ዋዜማ፣ በበዓሉና ከበዓሉ በኋላም በገዳሙ የተገኙ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና ከገዳሙ አቅራቢያና ከሩቅ አካባቢ በዓሉን ለማክብር የመጡ አገልጋዮችና ምእመናን ሣይቀሩ የዚህ ጭፍጨፋ ሰለባ ኾነዋል፡፡ ፕ/ር ኢያን ካምፔል ፋሽስት በደብረ ሊባኖስ ያደረሰውን ጭፍጨፋ በገለጹበት፤ ‹‹The Massacre at Debre Libanos Ethiopia 1937:- The Story of One of Fascism’s Most Shocking Atrocities›› በሚለው መጽሐፋቸው፡-

‹‹በግንቦት ፲፬ ቀን የፊንጫ ወንዝ ወደ ደም ጅረትነት ተቀይሮ እንደነበርና የፋሽስት ወታደሮችም በግፍ የገደሏቸውን ሰዎች በላያቸው ላይ አፈር ብቻ በመበተን ለአውሬና ለጅብ ራት እንዲሆኑ በየሜዳውና በየዱሩ ጥለዋቸው እንደነበር፡፡›› ጽፈዋል፡፡    

በወቅቱም የኢጣሊያን የጦር አዘዦች ከግድያውና ከጭፈጨፋው ባሻገርም የገዳሙን ቁልፍ ተርከበው በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ የከበሩ ንዋያተ ቅድሳትን፣ የብራና መጻሕፍትን፣ በተለይም ደግሞ በ፲፮ኛው መቶ ክ/ዘመን በዐፄ ገላውዴዎስ ለገዳሙ በስጦታ የተበረከተውን በወርቅ የተለበጠና በዐራት ሰው ትክሻ የሚነሳውን ትልቅ የብራና ወንጌል ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ሰርቀው እንደወሰዱት የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም በገዳሙ ያገኙት ብዙ ሀብትና ቅርስ ያስገረማቸውና ዝርፊያው የጣማቸው የኢጣሊያ ወታደሮች የተደበቀ ወርቅና ብር እናገኛለን በሚል ተስፋ ፈጽሞ ሰብአዊነት በጎደለው ኹናቴ የገዳሙን መካነ መቃብሮች እንኳን ሣይቀር ቆፍረውትና ንደውት ነበር፡፡

በደብረ ሊባኖስ ገዳም በግፍ ስላለቁት፣ ወደ ሶማሊያ ተግዘው በዳናኔ ወኅኒ ቤት ስለሞቱት  የገዳሙ ተማሪዎችና በገዳሙ ላይ ስደረሰው አሰቃቂ እልቂትና ዝርፊያ በ፪ሺሕ ፫ ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ያወጣው ‹‹ዜና አብዮሙ ለሰማዕታት ዘ ደብረ ሊባኖስ ደቂቁ ለተክለ ሃይማኖት›› በሚል ርእስ የታተመው መጽሔት በፋሽስት ኢጣሊያ በገዳሙ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለት ሺ ገደማ ያደርሰዋል፡፡ በእርግጥ በፋሽስት ወረራው ወቅት ከደብረ ሊባኖስና ከሌሎች የአገሪቱ ገዳማትና ቅዱሳን መካናት በግፍ የተገደሉ፣ የተጨፈጨፉ፣ የተጋዙ በርካታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ገዳማትና ቅዱሳት መካናት የተዘረፉ ቅርሶችና ንዋይተ ቅድሳትም እጅግ የበዙ ናቸው፡፡ 

  1. እንደ መደምደሚያ

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ልዑላዊነትና በሕዝቦቿ ነጻነት ላይ ያላትን የማያወላውል ጽኑ አቋም በሚገባ የሚያውቁ አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች፣ ወራሪዎችና ተስፋፊዎችም በተለያዩ ዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስና ቢቻላቸውም በራሳቸው ግዛትና ቁጥጥር ሥር ለማድረግ ያልቆፈሩት ጉድጓድ፣ ያልወጡት ተራራ የለም ማለት ይቀላል፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ፤ ይህ ሙከራቸው ደግሞ መልኩንና ይዘቱን ቀይሮ እስካሁንም ድረስ የዘለቀ ነው ማለትም ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ቤ/ን በውጭ አገራት ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ዘንድ ጥርሳቸው እንዲነኩስባትና በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ያጋጠማቸውን ወረራ፣ የቅኝ ግዛት መስፋፋት በማውገዝና በመቋቋም ረገድ ያደረገችውን ተጋድሎና የከፈለችውን ክቡር መሥዋዕትነት የታሪክ ድርሳናት የሚመሰክሩት ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ በተሰጠ ነጻነት፣ በእውነት፣ በፍትሕ ላይ ያላት ጽኑ የሆነ አቋም ስለ ነጻነታቸው፣ ስለ ፍትሕና ስለ ሰው ልጆች እኩልነት በሚታገሉና በሚጋደሉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተሰማ፣ ትልቅ ክብርና ዝና ያለው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሀገራችን በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይም ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩና በሚያከብሩ የሰው ልጆች መካከል ያላት አኩሪ ታሪክ፣ ገድልና መልካም የሆነ ምስክርነት በኋላ ዘመን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት ለመጡ አውሮጳውያን እንደ እግር እሳት ነበር ያንገበገባቸው፡፡ እናም ይህን ለጥቁር ሕዝቦችና አፍሪካውያን መመኪያ የሆነ ታሪክ በማጠልሸት፣ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ቅርስና ታሪካቸውን ከመሠረቱ ለመናድ፣ በሃይማኖቱ ጽኑ የሆነውንና ለነጻነቱ ቀናዒ የሆነውን ሕዝብ ለመበቀል ሲል ፋሽስት የበቀል በትሩን ዘግናኝና አረመኔዊ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ አንስቷል፡፡

ስለሆነም የፋሽስት መንግሥት ለሰው ልጆች ሁሉ ነጻነት፣ ለፍትሕ፣ ለፍቅርና ለሰላም በቆመችው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ለፈጸመው ግፍ፣ ጭፈጨፋና ኢሰብአዊ ድርጊት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሣ ሊከፍል ይገባዋል፡፡ ይህን ጥያቄም ቅዱስ ሲኖዶስና የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች በአንድንት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሊያሰሙ ይገባል፡፡ 

ለአብነትም ‹የኒው ዮርክ ታይምስ› ከሁለት ዓመት በፊት የአርመን ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ከመቶ ዓመት በፊት ቱርካውያን በአርመን ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲናት ላይ ላደረሱት ጭፍጨፋ፣ ግፍና መከራ የአርመን ቤ/ን መሪና መንፈሳዊ አባት የሆኑት አቡነ አራህም I/አንደኛ የቱርክ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል የጠየቁበትንና ያሳሰቡበትን ሰበር ዜና አስነብቦን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የቤተክርስቲያንም በተመሳሳይ ‹የይቅርታና የካሣ› ጥያቄዋን ለኢጣሊያ መንግሥትና ሕዝብ ማቅረብ ይኖርባታል፡፡

በማጠቃለያዬም ባለፈው ጽሑፌ እንደገለጽኩት አኀት ቤተ ክርስቲያን የኾነችው የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ዓመት በፊት በቱርካውያን ለደረሰባቸው ግፍና ጭፍጨፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸውና ካሣ ሊከፈላቸው እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ በኾኑት በአቡነ አራኻም በኩል የተነሣው ጥያቄ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪ አጀንዳ ኾኖ ነበር፡፡

እንደ አርመናውያኑ ኹሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ እንደ ማኀበረ ቅዱሳን ያሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክና ቅርስ የሚቆረቆሩና በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ የሚገኙ ማኅበራትና ተቋማት፣ እንዲሁም ሁሉም ምእመናን ፋሽስት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ላደረሰው ግፍና ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም ይህን ግፍ በዝምታ ያለፈችው ቫቲካንም ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢው የሆነው ካሣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሰጣት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሊያሰሙ ይገባቸዋል፡፡

ለአብነትም የኢጣሊያ መንግሥት በቅኝ ግዛት ዘመን በሊቢያ ስላደረሰው ጭፍጨፋና ግፍ የ፭ ቢሊዮን ዶላር የካሣ ክፍያ እንዳደረገ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ሮም በኢትዮጰውያ ላይ ላደረሰችው ጭፍጨፋ፣ እልቂትና ግፍ ጣልያን ገነባችው የሚባለው የቆቃ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ የጉዳቱ መጠን እና ካሣ በዓለም ፍርድ ቤት ባልተዳኘ፣ ከጣልያን መንግሥትም ሆነ ከቫቲካን ይፋዊ የሆነ ይቅርታ ባላገኘችበትና ግን ለጊዜው ወዳጅነትን ለማደስ በሚል የተሠራ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ 

በበኩሌ በመጨረሻ ለመግለጽ የምወደው ነገር ቢኖር ምንም እንኳን በፋሽስት ኢጣሊያ መንፈሳዊ መሪዎቿና በርካታ አገልጋዮቿ በግፍ የተገደሉባትና የተጨፈጨፉባት፣ በዋጋ የማይተመኑ ቅርሶቿና ታሪኳ የወደመባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የፋሽስቱ ጭካኔ ሰይፍ ዋና ተጠቂና ሰለባ ብትሆንም ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆን አለበት ብዬ አላምንም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብም በአንድነት በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊያሰማ ይገባል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ አንድነት፣ በትናንትና በሕዝቦቿ የነጻነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ፣ ገናና ሥልጣኔና ታሪካዊ ቅርሶቻችን የምንኮራ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳንለይ የኹላችንም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ፣ ቁጭትና አቤቱታ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!

Filed in: Amharic