>

የዐድዋ ድል እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዋጽዖ (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

የዐድዋ ድል እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዋጽዖ

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

C:\Users\tere\Documents\አድዋ.jpg

አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይ፣ አርበኛ፣ የዓለም አቀፉ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ማዲባ የዐድዋ ድል በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በሀገራቸው በደቡብ አፍሪካና በመላው የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ የመላው ጥቁር ሕዝቦች አንጸባራቂ ድል መሆኑን በትልቁ ያሰምሩበታል፡፡

ማንዴላ የሀገራችን ኢትዮጵያ ሺሕ ዘመናት የነጻነት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ እንዲሁም በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አውሮፓውያንን የሐፍረት ሸማ እንዲከናነቡ ያደረገውና በባርነት፣ በቅኝ ግዛትና በጭቆና ቀምበር ሥር ለነበሩ መላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ብስራትን ያበሰረው ታላቁ የዐድዋ ድል በእርሳቸውና በደቡብ አፍሪካውያን የፀረ-ባርነትና የፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ መቼም የማያረጅ፣ ሕያውና ደማቅ አሻራ እንዳለው ይስማማሉ፡፡

ማንዴላ ከዐድዋው ድል በኋላ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነጻይቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስምና ጥላ ስር የተቀጣጠሉ የፀረ-ቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ የነጻነት እንቅስቃሴዎችን በማስመልከት በአንድ ወቅት ታሪክ አጣቅሰው ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-

Fundamental tenets of the Ethiopian Movement were self-worth, self-reliance and freedom. These tenets drew the advocates of Ethiopianism, like a magnet, to the growing political movement. …The Adwa victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.

(Nelson Mandela, Speech to the Free Ethiopian Church of South Africa) 

ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ፣ ነጻነትና አንድነት፣ ኪነ-ጥበብና ኪነ-ሕንፃ፣ ሕግና ፍትሕ፣ ሥነ ጽሑፍና ፍልስፍና … ወዘተ ዕድገት ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡ በተለይም ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነጻነትና አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነጻነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ተቋም ናት፡፡

ከዚህም የተነሣ ቤተክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋንኛ ምክንያቱ ቤተክርስቲያኒቱ ለመእምናኖቿ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነጻነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው፡፡ እናም ይህች ጠንካራ ሃማኖታዊ ተቋም ማዳከምና ብሎም መምታት ለብዙዎቹ የአገሪቱን የነጻነት ዋልታ ከመሠረቱ ማፍረስ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤ/ን ሕዝቡ በአገሩ፣ በነጻነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነጻነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መኾኗ በበርካታ የታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ነው፡፡ እስቲ ከላይ ያነሳሁትን እውነታ የሚያጠናክርልኝና የሚያስረግጥ ጥቂት ምስክርነቶችን ከታሪክ መዛግብት ላጣቅስ፡፡

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ ሀገራት ተጓዦች፣ አሳሾችና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩትና የሚስማሙበት አንድ እውነት አለ፡፡ ይኸውም፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነጻነታቸው ቀናዒዎች ናቸው፡፡›› የሚል ነው፡፡

በአንድ ወቅትም ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስ እ.ኤ.አ ፲፱፻፷፫ ‹‹አክሌዥያ›› በሚባል በፓሪስ ከተማ ለሚታተም ጋዜጣ፡- ‹‹የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር፡-

‹‹… ኢትዮጵያ ወራሪዎች ምድርዋን በግፍ የያዙባት መሆኑን ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነጻነቷን መልሳ አግኝታለች፡፡ በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን የዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆነዋል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም፡፡ ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ ክርስቲያኒቷ ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ በነጻነቷና በልዑላዊነቷ ቆይታለች…፡፡›› በማለት ጽፏል፡፡

ይኽችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በዐድዋው ጦርነት ወቅትም ለጦርነቱ ዘመቻ የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ጀምሮ በተለያዩ የጦርነት ዓውድ ግንባሮች ሁሉ ላይ ሣይቀር በመሳተፍ ጭምር ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ አደራዋን ተወጥታለች፡፡ በዓድዋው ዘመቻ በመቶ ሺሕዎች ሆኖ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ ነው በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በሚሊተሪ ሳይንስ ከሰለጠነ አውሮፓዊ ጦር ጋር ለመጋጠም ‹‹ስንቁን በአህያ ዓመሉን በጉያው›› አድርጎና የኢትዮጵያን አምላክ ተስፋ አድርጎ ወደ ጦርነቱ የተመመው፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ወደ ዓድዋ የዘመቱትም የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፣ ሊቀ ጳጳሱን ግብፃዊውን አቡነ ማቴዎስን፣ በርካታ ካህናትንና መነኮሳትን ጭምር አስከትለው ነበር፡፡ የዓድዋን ጦርነት በሰፊው የዘገቡ የውጭ አገራትና የአገር ውስጥ ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች እንደጻፉትም፡-

በጦርነቱ ቀን ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን እንደደፉ፣ ወይባ ካባቸውን እንደደረቡ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ ከንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ፣ ግማሹ ከእቴጌ ጣይቱ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንትና ወታደር ዘንድ ሆነው ወዲያና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙና ከጦርነቱ ሊሸሽ ያለውንም እየገዘቱ፣ ሲያበራቱና ሲያዋጉ መዋላቸውን ጽፈዋል፡፡

የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ትዕዛዝ የሆኑት አለቃ ገ/ሥላሴ በዓድዋ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ ስለ ‹ዐፄ ምኒልክ ታሪክ› በጻፉት መጽሐፋቸው እንዲህ በሥዕላዊ መንገድ አስቀምጠውታል፡፡

ንጉሡ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርሱ አቡነ ማቴዎስና የማርያም ታቦት የያዙት ካህናት በኋላቸው ነበሩ፡፡ እቴጌ ጣይቱም ከዘበኞቻቸውና ከሠራዊቱ ጋር ሆነው በአቡነ ማቴዎስና በታቦቷ ጎን ነበሩ፡፡ የአክሱም ካህናት ቅዳሜ ማታ እንደ ጥንቱ አስተዳድሩን ብለው ለንጉሡ ለማመልከት መጥተው አድረው የነበሩት፣ በዚህን ጊዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕልና ሰንደቀ ዓላማ ይዘው በእቴጌ ጣይቱ ግንባር ተሰልፈው ነበር፡፡

የጽዮን እምቢልተኞችም መለከታቸውንና እምቢልታቸውን እየነፉ በእቴጌይቱ ፊትና በሠራዊቱ ፊት ይጫወቱ ነበር፡፡

… ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ይላሉ አለቃ ገ/ሥላሴ ከሌሊቱ ፲፩ ጀምሮ እስከ ፬ ሰዓት ድረስ ተኩስ ሳያቋርጥ ከሁለቱም ወገን ሲተኮስ ድምፁ እንደ ሐምሌ ነጎድጓድ፣ ከተኩስም የሚወጣውም ጢስ የተቃጠለ ቤት ይመስል ነበር፡፡ በዚህ ቀን በዓድዋ በዓይናችን ያየነውንና በጆሮአችን የሰማነውን ለመጻፍ ችግር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ ኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር፡፡ በማለት ጽፈዋል፡፡

በሌላ በኩል ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ፣ ‹አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፡-

እቴጌ ጣይቱ በተፋፋመው የዐድዋው ጦርነት ውስጥ ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው በጦርነቱ መካከል መገኘታቸውን ጽፈዋል፡፡ አቡነ ማቴዎስም የማርያምን ታቦት አስይዘው ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ በፊት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን ጽፈዋል፡፡

ኢጣሊያዊው ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ኮንቲ ሩሲኒም ስለ ዓድዋው ጦርነት ውሎ ሲመሰክርም፡- 

ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር ዓፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ሌሎችም የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ ፲ ሰዓት ጀምሮ በዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱና በጸሎት ሲማጸኑ ነበር…፡፡ ሲል ስለ ዓድዋ ጦርነት በተወው ማስታወሻው ላይ አስፍሮታል፡፡

ዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይለዩ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወታደር፣ ገበሬ፣ ካህን፣ መነኩሴ… ሳይባል ሁሉም ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሳተፉበት ነው፡፡ የድሉ መንሥዔም ይኸው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነትና ልዩ ኅብረት ነው፡፡ 

ከዓድዋው ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለውጭ አገራት ወዳጆቻቸውና መንግሥታት በፃፉትም ደብዳቤያቸውም፣ ድሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከመግለፃቸውም በላይ ሳይወዱ በግድ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ነጻነት ሲሉ በገቡበት ጦርነት ምክንያት የእነዛ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ ስለ መፍሰሱ የተሰማቸውን ኀዘኔታም በመጋቢት ፳፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ በላኩለት ደብዳቤያቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-

… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም፡፡ ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…፡፡

አፄ ምኒልክ በተመሳሳይም ለሞስኮብ ንጉሥ ለዛር ኒቆላዎስም በላኩት ደብዳቤያቸውም፡-

እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ፡፡ ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረግሁት…፡፡ በማለት ድሉ ከኢትዮጵያ አምላክ ዘንድ የተገኘ መኾኑን ጽፈውላቸዋል፡፡

የዐድዋ ድል አውሮፓውያን፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ፣ አረመኔ ሕዝቦች ናቸው፡፡›› የሚለውን ከንቱ የሆነ መረዳታቸውንና ግብዝነታቸውን በዓለም ፊት እርቃኑን ያሳየ፣ ያጋለጠ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የሰብአዊ መብቶችና የጦር ምርኮኞች አያያዝ ሕግ ሳይጸድቅ፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮንቬሽንና ድንጋጌዎች ከመውጣታቸው በፊት ለወረራ በግፍ የመጣውን የኢጣሊያ ምርኮኛ ሰራዊት የሚገባውን ክብርና እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግ በዓለም ፊት የሞራል ልአልናቸውን፣ የበላይነታቸውንና ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅርና ክብር አሳይተውበታል፡፡

ስለሆነም የዐድዋው አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያውያን በጦር ግንባር ብቻ ሣይሆን በዲፕሎማሲው መስክም ድል ተጎናጽፋ ለሰው ልጆች ሁሉ ነጻነት፣ አንድነትና ክብር ዘብ የቆመች ልዑላዊት ሀገር መሆኗን ለዓለም ሁሉ ሕዝብ አስመስክራበታለች፡፡ በዚህ ፈርጀ ብዙ በሆነው ዐድዋው ድል ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵውያንን ሁሉ በማስተባበር የተጫወተችው ሚና፣ በድሉም ወቅት ውስጥ የነበራት ደማቅ አሻራና ትልቅ ድርሻ ሁልጊዜም ታሪክ የሚያስታውሰውና የሚዘክረው ለትውልድ ትውልድ ሁሉ የሚተላለፍ ሕያው ቅርስ ነው ማለት ይቻላል፡፡

አውሮፓውያን በአፍሪካ ያደረጉት የቅኝ ግዛት መስፋፋት ዘመቻና እንደ ኢጣሊያ ያሉ ሀገራት ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ እግራቸውን የሚዘረጉበት የቅኝ ግዛት ሀገራትን ለመማተር አስቀድመው ዓይናቸውን በኢትዮጵያ ላይ መጣላቸውን ዐፄ ምኒልክና ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተረድተው ነበር፡፡ ይህን ኢጣሊያን የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ በጥንቃቄ ሲከታተተሉ ከነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መካከል አለቃ ለማ ኃይሉ የተባሉ ሊቅ ከጦርነቱ አምስት ዓመት በፊት፤ ‹‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረሯ ነገር አይቀሬ መሆኑንና ግና በጦርነቱ ተሸንፋ የሐፍረት ሸማን ተከናንባ ኢትዮጵያን እንደምትለቅ፤›› የሚከተለውን ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው አብዬ መንግሥቱ ለማ፣ ‹‹መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል፡፡ ቅኔው እነሆ፡-

ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣

አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣

ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣

ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣

በከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል፡፡

ትርጉም፡-ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣

መከሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋት ቀርቧልና፡፡

ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣

በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል(ወልድ)፡፡ ብዬ ፲፰፻፹፫ ተቀኘሁ፡፡ ምኒልክ በቤተስኪያን የሉም ይኸ ሲባል፡፡ ይኸ ጥንቆላ ነው፤ ያድዋ ጦርነት ሳይደረግ ነው፡፡ ኸጣልያን ጋር ስምም ናቸው ያን ጊዜ አጤ ምኒልክ፡፡ አለቃ ወልድ ያሬድ መልካም መልካም!አሉና፣ እሑድን ዋልነ፡፡ ሰኞ ጉባዔ አለ፤ አለቃ ተጠምቆ ናቸው እሚያኼዱ፡፡ አለቃ ወልደ ያሬድ እርሳቸው እልፍኝ አጠገብ ቤት ሰጥተውናል፡፡ እርሳቸው መጥተው ይቀመጣሉ ኸጉባዔ ለመስማት፡፡

የኔታ ተጠምቆ

አቤት!

ኸኒያ ክፉዎች ጋር እኮ ጠብ ላይቀርልን ነው አሉ፡፡

እንግዴህ ትግሬ ናቸው አለቃ ተጠምቆ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ራስ መንገሻ አሉ ኸኒያ መስሏቸው፤

ኸነማን ጌታዬ? ኸነማን? አሉ ደንግጠው አለቃ ተጠምቆ፡፡

ኸነጮቹ

ምነው፣ ምነው? አሉ፡፡

እንዴ! የልጅዎን ቅኔ በቀደም አልሰሙትም?

በለማ ቅኔ ሆነ እንዴ ጦርነት? አሉ አለቃ ተጠምቆ፡፡

አናጋሪው ማን ይመስልዎታል? አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቅ የነበሩት አለቃ ለማ በዚኹ ቅኔያቸው እንደተነበዩትም ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት አይቀሬ መሆኑ ታወቀ፣ ተረጋገጠ፡፡ አለቃ በቅኔያቸው እንደተቀኙትም ሮማ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተጋድሎ አማካኝነት ታላቅ ውርደትንና ሽንፈትን ተከናነበች፡፡ ይህም ድልም ለጥቁር ሕዝብ ንቀት የነበራቸውን መላው አውሮፓውያን ያስደነገጠና ቆም ብለው እዲያስቡ ያደረገና በተቃራኒው ደግሞ በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ሥር ወድቀው የነበሩ አፍሪካውያንን፣ አፍሪካ አሜሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦችን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሔዱና ብሎም ለነጻነቱ፣ ለመብቱና ለሰብአዊ ክብሩ በአንድነት፣ በኅብረት እንዲነሳ ትልቅ የወኔ መነቃቃት የፈጠረና ለነጻነት ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ዐቢይ ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ 

 ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት የቅኝ ገዥውን፣ የሮማ መንግሥትን የግፍ ወረራና የዐድዋ ጦርነትን አይቀሬነት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ከመተንበይ ጀምሮ ለጦርነቱ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በመምከር፣ ሕዝቡን በማዘጋጀት፣ በክተት ዘመቻውና በዐውድ ጦር ግንባር ጭምር በመሳተፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ በነጻነቷ፣ በልዑላዊነቷ ታፍራና ተከብራ እንድትቆይ የበኩሏን መንፈሳዊና ታሪካዊ ድርሻዋን ተወጥታለች፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያኒቱ ለአፍሪካውያን፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌትና ዓርማ የመሆን ክብርን እንድትጎናጸፍ አስችሏታል፡፡ 

ይህን እውነታ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ታቦ ምቤኪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ፳፻፪ ዓ.ም. በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ባበረከተላቸው ጊዜ በልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው፡- የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነት ክብርና ዓርማ የሆነች ለአፍሪካ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ማከማቻ፣ ማእከል መሆኗን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፤

… the Ethiopian Church would the authentic African church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches I have mentioned called themselves the Ethiopian Church …. 

(The Former President of Republic of South Africa Tabo Mbeki/2010)

ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!

Filed in: Amharic