>
5:26 pm - Sunday September 15, 0785

ህዝብ የፈለገውን በአል በፈለገው መንገድ የማክበር መብት አለው (ባልደራስ)

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ  መግለጫ …!

ህዝብ የፈለገውን በአል በፈለገው መንገድ የማክበር መብት አለው

በዛሬው እለት የአለምን ታሪክ የቀየረው የአድዋ ድል በአል ተከብሮ ይውላል። ሆኖም ይህንን የመላው የጥቁር እና የተጨቆኑ ህዝቦች የነፃነት አርማ የሆነውን በአል የአራት ኪሎውን ስልጣን የተቆጣጠረው የኦህዴድ-ብልፅግናው መንግስት ቅድመ ዝግጅቱንም ሆነ የዛሬውን አከባበር ሆነ ብሎ አሰናክሏል። 

በቅድመ ዝግጅቱ ግዜ የፓርቲያችንን አባላት ጨምሮ የተለያዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን  በማሰር እና በማሳደድ፣ የበአሉ ማድመቂያ ልብስ የሚያዘጋጁ ተቋማትን በመዝጋት፣ የማስፈራሪያ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት እና በሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ለማስተጓጎል ሲጣደፍ ነበር። ነገር ግን ህዝቡ በእንደዚ አይነት መሰናክሎች ባለመሸነፍ በአሉን ሊያደምቅ የሚችሉ አልባሳትን በመልበስ በአሉን ለማክበር ወደ ምንሊክ አደባባይ እና አድዋ ድልድይ ለማክበር ተገኝቷል። 

ይህ አገር ወዳድነትን እና የአድዋ ክብርን ማየት የሚጠየፈው የኦህዴድ-ብልፅግናው መንግስት ወደ ምንሊክ አደባባይ እና ወደ አድዋ ድልድይ የሚወስዱ ዋና ዋና መንገዶችን ዘግቷል። ይህ ሳይበቃ ወደ አደባባዩ አልፈው የሄዱ የበአሉ ታዳሚያን ህዝብ ላይ የአስለቃሽ ጭስ እና የድብደባ ውርጅብኝ አድርሷል። 

ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የጊዮርጊስን ታቦት ለማንገስ በመናገሻ ገነተ ፅጌ አራዳ ጊዮርጊስ የተሰበሰቡ የቤተክርስቲያኒቱ ተከታዮች ላይ ጭምር የአስለቃሽ ጭስ ለቋል። በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በርካታ ህፃናት እና አዛውንት የተገኙ ቢሆኑም ለእነሱ እንኳን ባለማሰብ የጭካኔ ተግባሩን ፈፅሟል። 

አለም በሰለጠነችበት በዚህ ዘመን ጣሊያን ላይ እንኳን ያሉ ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው የአድዋን በአል እናክብር ቢሉ ጥበቃ እየተደረገላቸው በአሉን ማክበር ይችላሉ። በራሳቸው ሀገር ኢትዮጵያ ላይ ግን በአንባገነኑ የአብይ መንግስት ስር በአልን እንደፈለገው በፈለገው ቦታ እና ሰአት ማክበር አልተቻለም።

ይህንን አምባገነናዊ ድርጊት ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፍፁም የሚያወግዘው እና የሚታገለው ተግባር ነው። ህዝብ ላይ ድብደባ እና የአስለቃሽ ጭስ እሩምታን ያዘነቡ ሰዎች እና ቡድኖች በህግ ፊት ቅጣታቸውን ማግኘታቸው የማይቀር ነው። 

የዛሬው የአድዋ በአል ምንም እንኳን በአምባገነኑ የብልፅግና መንግስት ደብዝዞ ቢውልም፤ ለተከበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በድጋሚ “እንኳን ለተከበረው ቀን አደረሳችሁ!” ማለት ይወዳል። 

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!

https://fb.watch/j0C44lqnvf/

ድል ለኢትዮጵያ!

ድል ለዲሞክራሲ!

Filed in: Amharic