>

ያልተሸበበ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያችንን ከማፍረሱ በፊት የኛችሁት ከእንቅልፋችሁ ንቁ...! (ሞገስ ዘውዱ)

ያልተሸበበ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያችንን ከማፍረሱ በፊት የኛችሁት ከእንቅልፋችሁ ንቁ…!

ሞገስ ዘውዱ

   ይሄ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው‼

በበርካታ ምክንያት ወ/ሮ አዳነች የተናገረችው በስህተት የተሞላ እና ህዝብን ለእርድ የሚያመቻች ነው። ይሄን ድርጊት ለማውገዝ ጤናማ አእምሮ መሸከም እና ለአገር ማሰብ ብቻ በቂ ነው። ይሄ አካሄድ ስህተት መሆኑን እንደሚከተለው ላስረዳ:-

(፩) ዜጎች በገዛ አገራቸው በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት አላቸው። ማንም ሰው ግለሰብን ወይም ቡድን ወደ ዋና ከተማው እንዳይገባ መከልከል አይችልም። 

(፪) የግለሰቦች እንቅስቃሴ የሚገደበው ወንጀል ሰርተው ሲገኝ ወይም ወንጀል ውስጥ ሊሳተፉ ሲሉ ማስረጃ ሲገኝባቸው ነው። ጥፋተኝነትም የሚረጋገጠው በፖለቲካ ውሳኔ ሳይሆን በፍትህ ሜዳ ነው። 

(፫) አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪነትን የሚወስነው ህጋዊ መስፈርት እንጂ የካድሬዎች ይሁኝታ አይደለም። 

(፬) ከሌሎች ክልሎች መጥተው ስልጣናችንን ሊነጥቁን ነው ማለት አንድምታው ሁለት ነው። በአንድ በኩል የአዲስ አበባ ህዝብ ፖለቲካዊ ህልውናውን የተነጠቀ(political agency) ነው ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። በሌላ መልኩ ከሌላ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ዜጋ የአገዛዝ ጠላት እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ነው።

(፭)የዚህ ገዢ ትርክት (mega narrative) ትርጉም ከዚህ በፊት አዲስ አበባ እንዳይገቡ የተከለከሉ እና ወቅታዊ ፖለቲካን ያገናዘበ ነው። “ሌሎች ክልሎች” የተባለው በተናጋሪውና በ target audience መካከል ግልፅ የሆነ ግንዛቤ የተወሰደበት ነው። ሌላው (the other anti-regime element) የተባለው ከአማራ ክልል የሚመጡትን የሚገልፅ ነው። 

(፮) ዜጎች አዲስ አበባ በገቡ በማግስቱ መሬት የሚወሩበት ተአምር የለም። በእርግጥ ሁሉም እንደሚያውቀው የከተማውን መሬት ሲቀራመት የነበረውና አሁንም የቀጠለው የብል[ፅ]ግና ካድሬዎች ናቸው። 

(፯)”መንግሥትህን ከጠላት አድን” የሚል አደኛ እና የመጨረሻው ጥሪ (desperate move) እየተደረገ ነው። ይሄ ደግሞ መሀል ዳር የማድረግና አዲስ አበባ የደም ገንቦ እንድትሆን ሴራ እየተጠመቀ ነው። 

(፰) መፍትሄው፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ከተማችን የብሄርተኞች መፈንጫ አይደለችም ብሎ መከላከል እና ለመብቱ መታገል ነው። በማበጠሪያ ላይ ሁለት መላጦች እንዲጣሉ መፍቀዱ አዲስ አበቤን ዋጋ እያስከፈለው ነው። ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደተናገርኩት፣ “አዲስ አበቤ እያለ ደንቢዶሎ እና ደምበጫ” ከተማውን የነፃ ትግል ሜዳ የሚያደርጉበት ምክንያት የለም። 

ያልተሸበበ ብሄርተኝነት ኢትዮጵያችንን ከማፍረሱ በፊት የተኛችሁት ከእንቅልፋችሁ ንቁ። This could the last straw that breaks the Camel’s back, unless we act now

Filed in: Amharic