>

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ሸፍጥን መሸከም አትችልም!ጥብቅ መልእክት ለኢትዮጵያውያን

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ሸፍጥን መሸከም አትችልም

ጥብቅ መልእክት ለኢትዮጵያውያን በያላችሁበት

ከይኄይስ እውነቱ

…በዚህ በሽተኛ ሰውዬ የጐሣ አለቅነት ኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነው ፋሺስታዊ፣ ናዚያዊ እና አፓርታይዳዊ አገዛዝ ቊጥር አንድ የህልውና ሥጋታችን ብቻ ሳይሆን በተግባር አደጋችን መሆኑን ከበቂ በላይ አይተናል፡፡ …ከእንግዲህ ወዲህ ይሄ ነውረኛ ተሳስቶ እውነትም ቢያወራ እንኳን ማንም ኢትዮጵያዊ ጆሮውን ሊያውሰው አይገባም፡፡ ወገኖቼ! የአገዛዙንና ግብር አበሮቹን ሸፍጥና ማጭበርበርያን በማዳመጥ የሚመጣ ማናቸውም ተጨማሪ ስሕተትን ኢትዮጵያችን በጭራሽ መሸከም አትችልም፡፡

አሁን ላይ የነውረኞች ቊንጮ የሆነውን ዐቢይ ማንነት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያወቀ ይመስለኛል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያዊነት ቅድስናና ልዕልና የመጨረሻ መገለጫ የሆኑትን የኢኦተቤ እና ክብራችንና ኩራታችን የሆነውን የዓድዋን ድል በለመደው ብልግናውና ንቀቱ ለማዋረድ፣ ለማራከስና ለማንኳሰስ ፊት ለፊት የጥፋት ዘመቻውን የከፈተ ጊዜ (አሁንም በሙሉ ኃይሉ ገፍቶበታል) በጉልበት የያዘው ሥልጣኑ በሕዝብ ልብና ኅሊና ዘንድ አክትሟል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚጠበቀው ቀሪ ጥፋቱን ፈጽሞ በታሪክ አቻ በሌለው ውርደት ከቅድስት ምድራችን በኖ ተንኖ መጥፋት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለቀሪው ጥፋቱ ታምነው ከዚህ ጭራቅ ጋር በዕብደትና ድንቊርናው እስከ መጨረሻው የሚዘልቁ የሉም ማለት አይደለም፡፡ 

ርእሰ መጻሕፍቱ በሁለት ልብ የሚያነክስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች እንደማያገኝ ይወቀው ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም  በውጩ ዓለም የምትኖሩ አድርባይ ወገኖቻችን እጅግ ሳይረፍድ አሰላለፋችሁን ብታስተካክሉ ራሳችሁን በቅድሚያ ከኅሊና ከሰሳና ወቀሳ÷ ሲቀጥል ከሕዝብ አስተያየት ፍርድ ቤት፣ ከዚያም ከትውልዱ መተፋትና በመጨረሻም በታሪክ የሰው ዝቃጭ ከመባል ልትተርፉ ትችላላችሁ፡፡ በውስጥም ያላችሁ ከዚህ ጭራቃዊ አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት ሆናችሁ – ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብላችሁ – በየዕለቱ የንጹሐንን ደም የምታፈሱ፣ ካፈርኹ አይመልሰኝን ትታችሁ ለልጆቻችሁ ብላችሁ አገር ከማፍረሱ የጥፋት ተግባራችሁ ከታቀባችሁ ቢያንስ በከንቱ የሚፈሰውን የዜጎች ደም ማስቆም ትችላላችሁ፡፡ 

 ነውረኛው ሰውዬ የማትነካውንና የማትደፈረውን የኢኦተቤክ በሠራዊቱ ብዛት ተመክቶ ለመዳፈር ሲያናፋ ተግዳሮቱ ደካማ መዋቲ ከሆኑት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ወይም ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ያለ መልካም እረኛ ተበትነው ሲቅበዘበዙ ከቆዩት ምእናኗ ጋር ሳይሆን የቤተክርስቲያኒቱ መሠረትና ጉልላት ከሆነው ከእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነበር፡፡ የማይነካውን በድፍረት ነክቷል የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ጥሉ ከሰማይና ምድር ንጉሥ ጋር ነው፤ ጥሉ ከአሸናፊዎች አሸናፊ፣ ከኃያላኖች ኃያል፣ ከጌቶች ጌታ ጋር መሆኑን አለመገንዘቡ ከአእምሮው የመለየቱ ዋና ምልክት ነው፡፡

የኢኦተቤክ ላይ ግልጽ ጦርነት በከፈተበት ሰዓት ‹‹ጭራቁ የመጨረሻውን ካርድ መዟል›› በሚል አንድ አስተያየት ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ ካርዱ በርግጥ አልቋል፡፡ ይህ ማለት ግን አንድ ሐሙስ በቀረው መንበሩ ላይ እስካለ ድረስ የማጭበርበሪያ አጀንዳዎቹ ይቆማሉ ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሰሞኑን የግል ‹ወዳጁን› ግብጽ በዓባይ ጉዳይ ልትወረን ነው፤ የዐረብ ሊግ ከጎኗ ቆማል በማለት ከዋናው ጉዳያችን የሚያናጥብ አጀንዳ ሊሰጠን እየሞከረ ያለው፡፡ በነገራችን ላይ አጥንት እንዳየ ጉንዳን የምንሰባሰብበትን አጀንዳ የሚሰጠን በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ኅብረት ፈጥረን ሙሉ ትኩረታችንን አገዛዙ ላይ በማድረግ ዕረፍት እንዳንነሣው ሲሆን፣ ሁለተኛው አዲስ አበባን ጨምሮ በየቦታው ለሚፈጽማቸው አገር የማፍረስ ‹ፕሮጀክቶች› ከለላ የማግኛ ዘዴ ነው፡፡ 

አሁን ላይ ለኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ከመደቀን አንፃር ከዚህ ነውረኛ ሰወዬና አገዛዙ ጋር በንጽጽር የሚቀርብ ማናቸውም የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይል የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ መንግሥት የሌለን በመሆኑ ግብጽ ከዓባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ጠይቃ ያጣችው ነገር የለም፡፡ አገር እያፈረሰ ያለ አገዛዝ በየትኛውም መመዘኛ የሉዐላዊነት ጠበቃ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ከአንድ ፕሮጀክት ጋር ተነፃፃሪ ሊሆን አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ በዓባይ ጉዳይ ላይ – ግድቡ የተሠራበት ቦታ፣ የፈሰሰው ገንዘብ፣ ለግብጽ ተብሎ የተደረጉት ለውጦች፣ የአገዛዙ ፍላጎት ወዘተ. – ከወያኔ ዘመን ጀምሮ እጅግ ጠንካራ ተዐቅቦ አለኝ፡፡ ለመሆኑ ዓባይን የሚያነሡ ሰዎች አገዛዙ በፈጠረው ጦርነትም ሆነ በሽብር ተግባሩ በግፍ ስለሚያልቁትና ስለሚፈናቀሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚቆረቆሩ ቢሆን ይህ አገዛዝ የ5 ዓመት ዕድሜ ሊኖረው ባልተገባ ነበር፡፡ 

ሐሳቤን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ አንድ ሕያው ምሳሌ ላቅርብላችሁ፡፡ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሱዳን፤ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ተወርረው የጠላት ኃይሎች በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያለማንም ጠያቂ ተደላድለው ከተቀመጡ ከዓመት በላይ ተቈጥሯል፡፡ እነዚህ ባዕዳን ኃይሎች መሬታችንን መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝባችን/ወገናችን ላይ መከራ በማጽናት እየገደሉ፣ ንብረት እየዘረፉና እያቃጠሉ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም በላይ በደቡብ ምዕራብ አንድ ኢትዮጵያዊ ጐሣ ተጨፍጭፎ ከጐሣው አባላት ከ50/60 የማይበልጡ እንደቀሩ በቅርቡ አገዛዙ ለጥፋት በተቆጣጠረው የሕዝብ ሚዲያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከተማ ጭምር ገብቶ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን የሚገድለው፣ የሚያስረውና የሚያፍነው አገዛዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ባልተመዘገበ ሁናቴ በሁለት ባዕዳን ኃይሎች ዳር ድንበራችን ተደፍሮና ዜጎቻችን ተጨፍጭፈው ዝምታ የመረጠበት ምክንያት ‹የዲፕሎማሲ ጥበብ› ይሆን? ከዚህ በላይ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ገጥሞት ነው? ከ40 ዙር በላይ አሠለጠንሁ የሚለው የሽመልስ ጦር ባለበት የተዋጊ ኃይል እጥረት ነው? እናስተውል! ግብጽ ለወረራ ብትመጣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ልዩነቱ ምንድን ነው? ይሄ ጭራቅ የሱዳንን ኃይል ራሱ ጋብዞ እንዳመጣ ሁሉ ግብጽንም በግብዣ ቢያመጣ አይደንቀኝም፡፡ 

አንዳንዶቻችን ሉዐላዊነት ላይ አንደራደርም ስንል እንሰማለን፡፡ ዛሬ በተዛባው የዓለም አቀፉ ሥርዓት ምክንያት፤ ጉልበተኞቹ ምዕራባውያን ባገሮች ውስጥ በሚያደርጉት ልዩ ልዩ ጣልቃ ገብነት፣ በዓለም አቀፍ ተቋሞቻቸው ብድርና የድህነት አዙሪት ውስጥ በሚያቆይ ‹ዕርዳታ› አማካኝነት የተሟላ የምንለው ሉዐላዊነት አዳጊ አገር ውስጥ ይኖር ይሆን? ይህንን ለጊዜው እናቆየውና፣ በዚህ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሉዐላዊነት ከተደፈረ የአገዛዙን ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ የአገራችን ግዛት በውጭ ኃይሎች መያዝ የግዛት ሉዐላዊነት መደፈር (violation of territorial sovereignty) አይደለም ወይ? የዜጎች ባገዛዙ በገፍና በግፍ መፈጀትና መፈናቀል፤ አገዛዝ-ወለድ በሆነ ረሃብና ጠኔ ማለቅ የሕዝብ ሉዐላዊነት መደፈር (violation of people’s sovereignty) አይደለም ወይ? መቼስ ይህን ግፍ ፈጻሚዎቹ የግድ ባዕዳን መሆን አለባቸው ብለን አንከራከርም፡፡ ወይም ‹የደደቢት ሰነድ› የጐሣ እንጂ የሕዝብ ሉዐላዊነት አያውቅም የሚል ክርክር ውስጥ አንገባም፡፡ በሌላ አነጋገር በዚህ በሽተኛ ሰውዬ የጐሣ አለቅነት ኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነው ፋሺስታዊ፣ ናዚያዊ እና አፓርታይዳዊ አገዛዝ ቊጥር አንድ የህልውና ሥጋታችን ብቻ ሳይሆን በተግባር አደጋችን መሆኑን ከበቂ በላይ አይተናል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ወገኖቼ! አይሆንም እንጂ፣ የመጣበትን የሕዝብ ማዕበል መከተሪያ ግብጽን ጨምሮ (ነውረኛው ጋብዟትም ይሁን በራሷ ጊዜ ብትመጣ) ከማናቸውም ባዕዳን ኃይል ጋር ጦርነትን እንደ አማራጭ የሚወስድ ከሆነ፣ እንደኔ እምነት መልሳችን መሆን ያለበት አንተና ሌላኛው ዕብድ ሽመልስ አውሬ ሠራዊታችሁን ይዛችሁ ሂዱና ተዋጉ ማለት ነው፡፡ እኛ ካላዳመጥናቸው በየጊዜው በሚፈጥሩት ቀውስ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረግ እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በነገሥታቱ ዘመን የውስጥ ልዩነት ቢኖር እንኳን ባዕድ ወራሪ ሲመጣ ሕዝቡ አንድ ሆኖ ይከት እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ አሁን ከጐሠኞቹ አገዛዝ ጋር ያለን ‹የውስጥ ልዩነት› ተብሎ በተራ ቋንቋ የሚገለጽ ጉዳይ አይደለም፡፡ ከባዕድ የከፋ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ደመኛ ጠላት ነው የገጠመን፡፡ ጥቁር ፋሺስት ያልነውም ያለምክንያት አይደለም፡፡ 

ነገ ተነገ ወዲያም ሌሎች ቀሪ አጀንዳዎች ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከእነዚህ አውሬዎች ለመታደግ የምንፈልግ ሁሉ የኅብረታችን የመጀመሪያው መገለጫ ክፉዎችንና ተላላኪዎቻቸውን አለማዳመጥ፡፡ በማናቸውም መልኩ አለመተባበር፡፡ ወግድ! ሰይጣን በሉት፡፡ ሲቀጥል ተደራጅተን ወይም በምናምንበት አደረጃጀት ውስጥ ገብተን አገዛዙን ለመቅበር መታገል ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ መከራው አንድ ባንድ ቤታችንን እያንኳኳ ይመጣል፡፡ በነገራችን ላይ ክፉዎቹ በውስጥ በውጭም አሉ፡፡ አንዳንዴም የኢትዮጵያዊነት የበግ ለምድ ለብሰው ብቅ በማለት አገዛዙን ለመፋለም የምናደርገውን እንቅስቃሴ በተልካሻ ንግግራቸው የሚያኮላሹ እንዳሉ ማወቅና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያን ካዋረዳት ኢሕአዴግ ከተባለው የአጋንንት ቡድን ጥሩ መሪዎች አሉ ብሎ የሚደሰኩር ወሬኛ የምንሰማበት ጊዜ አይደለም፡፡ 

ከእንግዲህ ወዲህ ይሄ ነውረኛ ተሳስቶ እውነትም ቢያወራ እንኳን ማንም ኢትዮጵያዊ ጆሮውን ሊያውሰው አይገባም፡፡ ወገኖቼ! የአገዛዙንና ግብር አበሮቹን ሸፍጥና ማጭበርበርያን በማዳመጥ የሚመጣ ማናቸውም ተጨማሪ ስሕተትን ኢትዮጵያችን በጭራሽ መሸከም አትችልም፡፡ እስኪታክተን ብንጮኽ አድማጭ አጥተን በድኑ ብአዴን እንኳን ብዙዎችን አታሏል፤ አነኁልሏል፡፡ የቅስና ሥልጣነ ክህነት ቢኖረኝ ኖሮ ሕዝቡን ጭምር እገዝት ነበር፡፡ አባቶቻችን ይህንን ምድር የሚያንቀጠቅጥ ታላቅ ሥልጣን (ሕዝባችን ለአገዛዙ እንዳይታዘዝ/እንዳይገዛ የማውገዝ) ለመቼና በምን ምክንያት እንዳቆዩት እነሱና ፈጣሪ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ለጊዜው በእኔ ዐቅም ማድረግ የምችለው ይህን መልእክት የምታነቡ ሁሉ በሚመቻችሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ሁሉ ለሌላው ወገናችሁ እንድታስተላልፉ ስለምትወዷት ኢትዮጵያ ብዬ እማፀናችኋለሁ፡፡ 

Filed in: Amharic