>

ዲያስፓራው በጠ/ሚር አብይ አህመድ ተከዳ ወይስ ''ተሸውደ'' ወይስ ጠ/ሚሩ ተከዱ?

ዲያስፓራው በጠ/ሚር አብይ አህመድ ተከዳ ወይስ ”ተሸውደ”  ወይስ ጠ/ሚሩ ተከዱ?

ፊልጶስ

አስራ አምስት  የሚሆኑ የዲያስፓራ (በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮያዊያን)  የተለያዩ ማህበራት  በዚህ ወር ላይ በ/ም-አብይ ፤ የብልጽግና አገዛዝ ላይ ተስፋ መቁረጣቸውንና መከዳታቸውን በሚመለከት ደብዳቤ ጽፈዋል። ከዚህ ላይ  ጠ/ሚ ደግሞ   በዲያስፓራው  መከዳታቸውን  በቃለ-አቀባያቸው በኩል ለማሳወቅ ሞክረዋል። ታዲያ መከዳትና መከዳታድቱ ወይም ”መሸወዱ” እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በዲያስፓራው በኩል አሁንም   ለአገራችን መፈተሄ  እንዲያመጡ የተጠየቁት ”ካሃዲውንና ተስፋ የቆርጡባቸውን” ጠ/ሚ አብይ ናቸው።

 እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ዲያስፓራ ይሁን ሌላው  ለኢትዮጵያዊያን ቁምናል የሚልው አካል፤ ከመከዳት ይልቅ ”ኢትዮጵዊነት” በሚባል ምላስ መሸውዱን ነው  መቀበል ያቃታው። ዲያስፓራው  በእውነት በጠ/ ሚ አብይ ”ተክደናል” ብሎ የሚያምን ከሆነ፤ ወደፊትም የከዳል፤ ወይም  ስለ ኢትዮጵያ ፓለቲካ ያለው ግንዛቤ ትክክል አልመሆኑ ብቻ ሳይሆን   ትላንትም ሆነ ዛሬ ያሉትን የገዥዎቻችንን ባህሪና ማንነት ጥንቅቆ ካለማወቅ  ወይም ተናቦ በአንድነት ለመታገል  አቅም  ከማጣት  የመነጨ ይመስላል።

በ’ለፋት ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ለስልጣን የሚያበቃው የፓለቲካ ቀመር፤ ክህደት፣ ማስመሰል፣ ውሸት፣ መንደርተኝነት፣ ሴራና በህዝብ ደም መነገድ ነው። ጠ/ ሚ አብይ አህመደም ወደ መመበሩ ለመድረስም ሆነ ላለፋት ዓምስት ዓመታታ  ከብልጽግና  አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ጋር የፈጸሙት ሃቅ  ይህው ነው።

ሌላው  አሳዛኝ ነገር ደግሞ  ለአንድ አገር ሰላምም ሆነ እድገት የመሪዎች አስፈላጊነት ባይካድም፤   እንደ ኢትዮጵያ ያለ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለሚያስተናግድ፣ ህዝባዊ ተቋማት ያልገነባ አገር ፤ ኃላፊነቱን ለአንድ ግለሰብ መሥጠት ወይም መደገፈና ተስፋ ማድረግ  የሚያመጣው ውጤት አሁን ያለችውን የተጎሳቆለች ኢትዮጵያን ፣በመንደር የተከፋፈለች ፣ ተጠያቂነት የለሌበት፤ ያደረሰው ሁሉ የሚያዛት ደካማ አገር፤ በኖሮ ውድነትና በርሃብ  እንደ ቅጠል የሚረግፍ ፤ ወቶ መገባት የማይችል ህዝብ   ነው።

በምዕራቡ ዓለም የሚኖረው ዲያስፓራ ደግሞ ለአንድ አገር ህዝብ ወሳኙ፤ የግልሰቦች ሥልጣን ሳይሆን የህዝብ ትቋማት መሆናቸውንና አስፈላጊነትነታችውን ጠንቅቆ ማወቅ ነበረበት። በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋም አለ ከተባለም የጎሳ ህገ-መንግስትና እሱን የሚያስፈጽም ኃይል ነው።

አሁን የበለጥ ልብን ደሚያደማው ደግሞ ካለፈው ስቃይ፣ የገዥዎቻችን እሥስታዊ ማንነት  ያለመማራችንና በኢትዮጵያ ምድር ህዝብን ለመታደግ የሚስችል እውነተኛ የህዝብ ፓለቲካዊ ድርጅትም ሆነ መሪ አለመኖር ነው፤ አሁንም በትላንትናው የጎሰኝነትና የጥፋት ጎዳና መንጎዳችን  ነው።

—–አየሽ እናታለም! …

የአ’ች እኮ … ውድቀትሽ ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው

ከውድቀትሽ ለማትረፍ የሚደረግ ጥረት አለመኖሩ ነው

ዓለምን አስደምሞ፣ እጅግ አድርጎ የሚያስገርመው።—–

ለዚህ ይመሰላል አቶ ገሪማ መታፈሪያ ፤

”ሁሉ በሽተኛ፣ ሁሉ ‘ራሴን ባይ

በአገሬ  ደህና ሰው ላይገኝ ነወይ?” ያሉት።

 ወያኔ-ኢህዴግን አስወግዶ፤ ጠ/ሚ አብይ አህመደን ወደ ስላጣን ያመጣው ትግል ምን ይመሰል ነበር ? ብለን  ለግንዛቤ ያህል እንየው።

ወያኔን ወደ መቀሌ እንዲፈረጥጥ ያደረገው ትግል ፤ ወያኔ ”በጋራ ጠላትነት” ይፈረጅ እንጂ፤ ትግሉን ያካሂዱት ወይም ይመሩት የነበሩት የፓለቲካ ቡድኖችና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎች  ዓላማቸው ወይም ግባቸው በርግጥም ”እሳትና ጭድ ” ነበር።  ይህን ለመረዳት አሁን ያለውን የወቅቱን  የአገራችንን የፓለቲካ አሰላለፍ  ማየት በቂ ነው።

ከወያኔ ከአዲስ አበባ መሸኘት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የኋላ – ኋላ ሶስት  ጎራዎች በገሃድ ወጡ፤

አንደኛው/   የወያኔን የበላይነትና  በነሱ ጎሳዎች ላይ ያለው የፈላጭ ቆራጭነት  የታገሉ፤ ነገር ግን ህገ -መንግሥቱንም ሆነ የጎሳ ክልላዊ አስተዳደሩን  የሚቀበሉ ፤ ካስፈለገም  አንቀጽ 39 ተጠቅመው ለመገንጠል  የሚሹ ሲሆኑ በውጭም ሆነ በአገር ወስጥ የተደራጁ ከኦዲድ ጋር አበረው ይሰሩ የነበሩት የኦሮሞ ብሄርተኞች ለጥገናዊ ለውጥ የሚታገሉ፣  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት የፈርጁ ነበሩ።

ሁለተኛው/   የወያኔ ህገ-መንግስትና  የጎሳ ክልል አይደለም፤  አመለካከቱም መወገድ እንዳለበት የሚሰብኩና የጎሳ ፓለቲካ በአገሪቱ እንዲጠፋ የሚፈልጉ፡  በዜግነት ፓለቲካ  የሚያምኑ፣ በኢትዮጵያ አንደነትና ሰንደቅ ዓላማ የማይደራደሩ ስር-ነቀል ለውጥ  ለማምጣትና ”ኢትዮጵያ የሁላችንም -ለሁላችንም እኩል ናት” ብለው ቃለ የገቡና ሥልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ነበሩ።

ሶስተኛው/ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅመው ሥልጣን ለመያዝ፤ የሚጠቀም ከሆነ ኢትዮጵያዊ ወይም ጎሳዊ ፓለቲካ የሚያራምዱ፡ መርህ አልባ ፤ ከአገርና ከህዝብ በላይ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ  በአገር ወስጥም ሆነ በውጭ የሚታገሉ ‘ፓለቲካዊ አካል፡ ከሞቀው ጋር ዘፋኝ’ ነበሩ።

ከወያኔ በኋላ የትግሉ ውጤትም  ስንመለከትው የኢህአዲግ ክንፍ የሆነው ኦህዲድ፤ ከጎሳ ፓለቲካ አራማጆችና ከጥቅመኞች ጋር   በመሆን  የለውጡ ቁንጮና አሸናፊ ለመሆነ በቃ።

በርግጥ  ቤተመንግስቱን የተቆጣጠረው ኦህዲድ ከውስጥም ሆነ በውጭ መፈረካከስ ቢደርስበትም፤  ዛሬ  የወያኔን መንገድ ተከትሎና ስሙን ወደ ብልጽግና ቀይሮ፣ ብአዲንን  የጋሪ ፈረስ አድርጎ፣  ለስር- ነቀል ለውጥ እንታገላልለን ያሉትንና  ጥቅመኞችን  በአጃቢነት አስከትሎ፤ በጠ/ ሚ አብይ አህመድ አማካኝነት ኢትዮጵያዊነት እየተሰበከ፤ በተግባር ግን በኦሮማማ  የበላይነትና በፍጹም ተረኝነት  የኢትዮጵያ ህዝብ የቁም ስቅሉን እያየና እየተገዛ ይገኛል።  

ጠ/ሚ አብይ አህመድና ፓርቲቸው የወያኔን ጡጦ እየጠቡ ቢያድጉም፤ ከወያኔ ውድቀት የተማረቱ ነገር ቢኖር ፤ በአደበት ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውነት እየሰበኩ፤ በተግባር ግን ያደጉበትን የጎሳ ፓለቲካ መተግበር ነበር። ያደርጉትም ይህው ነው።  አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ገዥዎች ብንመለከት ሁሉም የጎስ ፓለቲካ አራማጆችና በኢትዮጵያዊነት ጠላቻ የሰከሩ ለመሆናቸው ያለፈ ታሪካቸውን መመርመርና አሁን በተግባር የሚያደርጉትን በተለይም አዲስ አበባ ላይ  ገና የሥልጣን ኮርቻውን ከመፈናጠታቸው የሚፈጸመው ግፍና ዲሞግራፊ የመቀየር እየን ያወጣ ተግባራቸው በቂ ነበር።

ዲያስፓራውም ይሁን  ሌላው አካል ይህን ሁሉ ሳያግናዝብ ነው ዛሬ በ/ ጠ አብይ ተከዳን የሚለው። መከዳት ሳይሆን በነሱ ቋንቋ ”ቁማሩን ”  በድጋሜ በልተውታል።

ከወያኔ ጋር የተደረገው ጦርነትም ሆነ አሁን ተደረስበት የተባለው ሰላምም  ቢሆን የጠ/ሚ አብይ አገዛዝ የሚከተለው መንገድን  ግልጽ አድርጎታ ፤ ይኽውም በወያኔና በኦነጋዊ -ብልጽግና  ድሮም ሆነ አሁን   በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት  ላይ ያላቸው ዓላማና ግብ አንድ መሆኑን አስመስክረዋል።  የጋራ ጠላታቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው። ህግ-መንግሥታቸውና የጎሳ ክልላቸው  አይነኬና በጋራ የሚታገሉለትና የሚሞቱለት ነው። ስለዚህም አሁን በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ በልተውና አሳርደው  ”እከክልኝ፣ ልከከልህ”  ቢሉ ካለፈው ማንነታቸው ተምረን ልንዘናጋ ባልተገባ ነበር። ግን መጽሃፍ እንደሚለው፤

”—እናያለን ግን አናስታውልም

እንሰማለን ግን አናዳምጥም===”

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የምንገኝ ዜጎችም ሆን ድርጅቶች ደብዳቤ በመጽፍም ሆነ መግለጫ በማውጣት ጠብ የሚል ነገር የለም። እንደ  ግለስብም፣ እንድ ድርጅትም ፤ በአጠቃላይ እንደ ሰው ራሳችን እንጠይቅ።

ለምን ? እንዴት ? ብለን እንጠይቅ።በጎሳ የተደራጁ ቡድኖች  እንዴት በዚች ታላቅ አገር ላይ እንዲህ እንዲፈነጩና የህዝቡንም መከራ እንዲያበዙበት ፈቀድን??

በኔ እምነት ለዚህ ተጠያቂዎች እኛ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! የምንል  በመሆናችን ከምንግዜውም የበለጠ ኃላፊነት መውሰድ አለብን። ከስሜታዊ ነት እንውጣና አገራችንና ህዝባችን የተደቀነበትን  የህልውና አደጋ በቅጡ  እንገንዘብ።  በየግዜው በሚወረውርልን አጀንዳ እየተባላን የአገራችን ስቃይ እናራዝመው።እነሱ አገርና ህዝብ ለማፍራስ ተድራጅተው ሲሳካላቸው፤ እኛስ ‘’በደምና በአጥንት ለተገነባችው አገርና ወገናችን እንዴት መደራጅትና በአንደንት መቆም ያቅተናል?’’ ብለን ራሳችን እንጠይቅ።

አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚወክልና ጎሰኞችን የሚገዳደር   አንድም ጠንካራ ድርጅት የለም።  ካለፈው ተምረን ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ አገናዝበን በየ’ለንበት ቦታ ሁሉ ፤  ሁለትም ሶስትም  በመሆን፤ መነሻችንም ሆነ መድራሻችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አድርገን እንደራጅ! ከተድራጀንና ከታገልን ለድል የማንበቃበት ምክንያት የለም።

ወያኔዎች የሚፈነጩብንና ያን ሁሉ እልቂት ፈጽመው ወደ ቤተ-መንግሥት የሚያኮበኩቡት ስለተደራጁና ስለታገሉ ነው። ኦነጋዊያን ቤተ-መንግሥቱን ተቆጣጥረው የሚፈነጩብን ስለ ተደራጁ ስለ ታገሉ ነው። ይህን ሃቅ መቀበል አለብን። በተለይ በዚህ ሰዓት ተደራጅቶ በአንደንት ለህልውና ከመታገል ውጭስ ምን አማራጭ አለን?

አዶልፍ ኤችማን የናዚ ጀኒራል ነበር፤ ከጦርነቶ በኋላ ራሱን ደብቆ በአርጀንቲና ሲኖር፤ የአይሁድ ጋዜጠኛ ለፍርድ ለማቀርብ ይፈለገው ነበርና  ከዓመታት በኋላ አገኘው። አይሁዳዊ ጋዜጠኛ ለኢንችሚን ያቀረበለት ጥያቄ ”ምን ዓይነት አመለካከት ቢኖራችሁ ነው ጀርመን  ዓለምን  መግዛት ይችላል  ብላችሁ የተነሳችሁት?” የሚል ነበር።

ኢችሚን ተረጋግቶ” መጀመሪያ ላይ  ዓለምን ለመግዛት የሚስችሉን ነገሮች ነበሩን፤ በኋላ ግን እነዚያ ዓለምን ለመግዛት የሚያስችሉን ነገሮች መፈረካከስ ጀመሩ፤ ስለዚህም ተሸነፍን።” አለው።

”እነዚያ የተፈረካከሱ  ለመሸነፋችሁ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?” ሲል አይሁዳዊ ጋዜጠኛ ጠየውቀ።

”መደራጀት፡ የዓላማ ጽናትና ዲስፕሊን ናቸው” አለው።

አዎ! እኛም ከተደራጀን፣ የዓላማ ጽናት እና ዲሲፕሊን ካለን ፤ አሁን ከተደቀነበን የህልውና አደጋ በድል አድራጊነት በመወጣት ፤ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን  የማንታደግበት ምንም ምክንያት የለም። እናም እንደራጅ! የዓላማ ጽናትና ዲሲፕሊን ይኑረን!

 ትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

ፊልጶስ

መጋቢት / 2015

E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic