>

ለአምሓራ ማህበረሰባችን ሊሆን የሚገባው የወደፊት እርምጃ እና አማራጭ ሊሆን የሚችል የትግል ስልት (ብርሃኑ ድንቁ)

ለአምሓራ ማህበረሰባችን ሊሆን የሚገባው የወደፊት እርምጃ እና አማራጭ ሊሆን የሚችል የትግል ስልት

ብርሃኑ ድንቁ

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአምሓራ ላይ እየደረሰ ባለው ግፍና ሰቆቃ  ምክንያት በአለም ላይ ያለው አምሓራ  በአብዛኛው መደራጀት በመጀመሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካሄድ የተለየ መልክ እየያዘ ነው። ይሄ ከበፊቱ በተለየ ፍጥነት እየተካሄ ያለው መደራጀት የአምሓራው ትግል ጉልበቱ  ከመውተርተር ተቀይሮ ጠንከር እያለና የመፈርጠም ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ይህም ለማህበረሰባችን የመደማመጥና  የአስተሳሰብ ውህደት እየፈጠረለት ለመሆኑ ብዙ ማለት ይቻላል። በተጨማሪም እንደ ማህበረሰብ  ችግሮቻችን  ተሰሚነትን እያገኙና ተጽእኖ  መፍጠር መጀመራቸው በገዥው የብልጽግና ፓርቲ  የመካከለኛውና የበታች መስመር አባላትን በድርጅታቸው ላይ ጥያቄ እንዲጠይቁና ግልጽ አቋም  የመያዝ አዝማሚያ መፈጠሩን በዋናነት  እንደ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። መደራጀትና በየአቅጣጫው መሰባሰቡ ማህበረሰባችንን  በሚገባ  ጠላቶቹን መለየት እንዲችል እና በመጠኑም ቢሆን  መረዳዳት እንዲችል  እረድቶታል።

በተቃራኒው ሲታይ ደሞ የአምሓራ መደራጀት በጠላቶቹ ላይ ባመጣው ድንጋጤ ምክንያት በተለያየ ጎራ ውስጥ ተወሽቀው የነበሩትን ጠላቶቹን እያሰባሰባቸው እንደሆነ እያየን ነው። ለምሳሌ፤ በተለያየ ጎራ ተሰልፎ የነበረው የኦሮሙማ ግሩፕ አምሓራ እየመጣልህ ነውና የኦሮሚያን ብልጽግና ይዘን ነፍጠኛውን ማጥፋት አለብን እያለ ነው ፣ በተጨማሪም ይሄ የኦሮሙማ ግሩፕ ወያኔን መልሶ አደራጅቶ አምሓራውን እንዲወጋለት ይፈልጋል፣ ሌላኛው ጎራ የአስተሳሰብ ድህነት የሚያጠቃውና ስግብግብ የሆነው ስብስብ የአምሓራው አክራሪ በስፋት እየተንቀሳቀስ ነውና አብይ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ የሚለው ነው፣ ይሄ አልበቃ ብሎ የአምሓራ መደራጀት አሜሪካንና አጋር የምእራቡ ዓለምን  ስላስደነገጠ የአምሓራ ጦር የዘር ማፅዳት ወንጀል ፈጽሟል በሚል ሰበብ ቅስምን ሰብሮ  በቀጣይ ህይወቱ አንገት አስደፍቶና ተበትኖ እንዲኖር ከወዲሁ ሥራቸውን ጀምረዋል። ታዲያ ይሄ ሁሉ የሚያሳየን የአምሓራው የጭቆናና ግፍ ተቃውሞ የትግል ስልት መደራጀትና እነኝህ ስብስቦች በጋራ መደማመጥና አብሮ የመስራት ፍላጎት መጎልበት  ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን የሚረጋግጥ ሆኖ እናገኘዋለን።

ወደፊት ምን ይደረግ ለሚለው መልስ፤

1/ ይሄ አሁን የተጀመረው መደራጀት በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ በስፋትና በጥራት መቀጠል አለበት

2/ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ የተደራጁ የአምሓራ ድርጅቶች ተባብረው አንድ ወጥ የሆነ ሁሉንም በአንድ ሊመራ የሚችል አለም አቀፍ የአምሓራ ማህበር ማቋቋም አለባቸው

3/ ይሄ የአምሓራ እንቅስቃሴ እንደ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እየሞተ ጀግንነት የሚያስተምር ወይም እንደ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት ያለ ከስርቤት አልወጣም እያለ ህያው ሆኖ ጀግንነት የሚያስተምር በርከት ያሉና አርኣያ የሚሆኑ ጀግኖችን አምጦ መውለድ አማራጭ የሌለው እውነታ ነውና ማህበረሰቡ አበክሮ መስራት አለበት ። 

4/ አምሓራ በመሆናቸው ብቻ መፈናቀል ወይም ቤተሰቦቻቸውን በግፍ ግድያ ላጡ ሰዎች በተገቢው መጠን ዕርዳታ ማረጉን መቀጠል እንዲሁም ፋኖ ሆነው ወይም የልዩ ሃይል አባል ሆነው ለተጎዱት አለያም በሞት ለተለዩን ቤተሰቦች እርዳታውን በሰፊው ማዳረስ።

5/የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለ ጠንካራ ቅስቀሳ ውጤት ስለማይኖረው የሚዲያ መኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም ስለዚህ ጠንካራ የሚዲያ ተቋም በፍጥነት ማቋቋም ግድ ይላል።

6/ ፋኖን በስፋትና በጥራት ማደራጀት ዋና ዋና ስራዎች ሲሆኑ

በተጨማሪ አምሓራው ለምን እንደተደራጀ በትግስትና በአክብሮት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሳይታክቱ ማስረዳት ይጠይቃል። እንዲሁም አምሓራውን እንወክላለን እያሉ አላስፈላጊ ነገር የሚናገሩና መስመር የለቀቁ ቡድኖችን አፍ ማዘጋት ያስፈልጋል። እንዲያም ሲል ከኛ ጋር አብረው ለመስራት የሚፈልጉ ካሉ ማሳተፍ ያስፈልጋል።

ሌላኛውና ችላ መባል የሌለብት ጉዳይ ደሞ ከአለም አቀፍ ህብረተስብም ጋር ሆነ ከጎረቤት ሃገሮች ጋር አላማችንንና የአደረጃጀታችንን ጥልቅ ሃሳብ አስረድቶ አጋር ማረግ የሁላችንም ግዴታ መሆን አለብት ። በዚህ ላይ በጥልቅ መሰራት ያለበት በተከባበረ ሁኔታ እንዴት ከኤርትራ ውንድሞቻችን ጋር አብረን መስራት እንዳለብን ማሳመንን ይጠይቃል።
ከላይ የተጠቀሱትን የትግል ግቦችንና ሌሎችንም ይጠቅማሉ፣ ለጥሩ ውጤት ሊያበቁን የሚያስችሉ ስልቶች ተካተውበት ወደፊት ለተፈለገው ግብና ፍሬው ያማረ ውጤት እንድንደርስና በቀጣይም ጎልብተን ወደ ማህበራዊ ለውጥና  ወቅቱ የዋጀው ልዕልና እንዲሁም ጥሩ የእድገት ደረጃ እንድንደርስ በጋራ ተባብረን እንስራ በማለት በትህትና እጠይቃለሁ። የአጭርና ረዥም እቅዶችን በጋራ ተልምን በጋራ ብንረባረብ ለውጤት የምንደርስበትን ጊዜ በእጅጉ ስለሚያቀላጥፈው አሁንም ተባብረን እንስራ እላለሁ።

Filed in: Amharic