>

ከእንግዲህ ምን ቀረን? ማንንስ ምክንያት ማድረግ እንችላለን? ምንስ ነው የምንጠብቀው?

ከእንግዲህ ምን ቀረን?  ማንንስ ምክንያት ማድረግ እንችላለን? ምንስ ነው የምንጠብቀው?

ፊልጶስ


”የክፉዎች ጥንካሬ በአንድ ላይ መቆመ መቻላቸው ነው።” ይባላል።

እናም ”–ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ድረስም ቢሆን እንወርዳለን።”’ ብለው የማሉትና በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ”ኦሮሚያን” እንመሰርታለን።” ያሉ ቡድኖች፤ ኢትዮጵያዊያንን በበቂ ሁኔታ ደማቸውን አፍሠን፡ አጥንታቸውን አድቅቀን፣ ቅስማቸውን ሰብረን፤ ሃይማኖታቸን አርክሰን፣ ማንነታቸውን አጥፍተን  ከእግራችን ሥር እድርግናቸዋል። ኢትዮጵያን ያለ ሰው እስቀርተናታል፤ በእጃችን መዳፍ ውስጥ ገብታለች፤ በፈለገነው ስዓት የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን። ብለው ሲያምኑ ፤ በአድነት ቆሙ።

እንደሚባለውም—-”—-ጦርነት በፓለቲከኞ ይጀመራል። ቱጃሮች ጥይት፣ ጠመንጃና ምግብ ያቀብላሉ። ድሆች ልጆቻቸውን ይሰጣሉ።

ጦርነቱ ሲጠናቀቅ፣ ከጦርነቱ የተረፈውን ጥይትና ጠመንጃ ፓለቲከኞቹ  ይሰበሰቡና ስልጣናቸውን ያጠናክሩበታል፤ ቱጃሮች  ለጦርነቱ ያዋጡትን ከህዝብ ካዝና ከነወለዱ ይወስዱና ሃብት በሃብት ይሆንሉ።ድሆች ግን ልጆቻቸውን  በየመቃብሩ  ሥፍራ እየፈለጉ እያነቡ ይኖራሉ።—–”

ለ’ኛ ለኢትዮጵያዊያን ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው፤ ፤ድሆች ልጆቻቸውን  በየመቃብሩ  ሥፍራ እየፈለጉ እያነቡ  እንዲኖሩ እንኳን ኢትዮጵያዊያኖች  አልተፈቀደላቸውም።  እነሱም እንዲጠፍ እንጅ።

ትዲያ እንግዲህ  እንደ ሀገርና እንደ ዜጋ ከአሁን በኋላ መቀጠል እንችላለን ወይ? የሚለው ነው። ምክንያቱም ቤተ መንግሥቱን የተቆጣተሩት ጠላቶቻችን በራሳቸው ኃይል ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ ጠላቶቻችንም እየታገዙ የመጨረሻ

ግባቸውና እንደ ማለዳ ጸሃይ የሚናፍቁት ኢትዮጵያ የምትባል ሃገርና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ ከምድረ ገጽ እንዲጠፈ  ነው።  

ወያኔና ኦነጋዊ ብልጽግና ድሮም ሆነ ዛሬ፣ ወደፊትም አንድ ናቸው።  ኦነጋዊ-ብልጽግና ያለ ወያኔ ፤ወያኔ ያለ ኦነጋዊ- ብልጽግና በኢትዮጵያ ምድር ላይ እድሜ’ቸው አጭር  ነው። ስለዚህም ሚሎኖችን አስጨርሰው፤ማንም ተጠያቂ ሳይሆን፣ ወላጆችን ያለ ጧሪ፤ ለጆችን ያለ ወላጆች አስቀርተው፤ የአገርን ኢኮኖሚ አድርቀውና ግጠው፣ በህዝብ መሃከል ጥላቻንና ብቀላን ዘርተው፤ቁስላችን ሳይደርቅ፣ እንባችን ሳንጠርግ፣ ነፍስ ይማር ሳንባባልና  ከተፈናቀልንበት ሳንመለስ፣ ” የሰላም ስምምነት አደረግን”  ብለው ፣ ግን ስምምነቱም ገና በቋት ላይ እያለ፤ እነሱ በደም በታጠበ እጃቸው፣ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ በጥላቻ በሰከረ እዕምሯቸው ሽር-ጉድ በማለት  ላይ ይገኛሉ።

ታዲያ እኛ  ከእንግዲህ ምን ቀረን?  ማንንስ ምክንያት ማድረግ እንችላለን? ምንስ ነው የምንጠብቀው?

”ሰው የገዛ ወዳጁም፤ ጠላቱም ራሱ ነው።” እንደሚባለው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ  በተልይም ከአሁን በኃላ  ለህልውናችን መጥፋትም ሆነ ለደረሰብንና ለሚደርስብን ግፍና በደል ሁሉ ኃላፊነቱ የኛ  የራሳችን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። አሁን  በገሃድ የገዥዎቻን ”ሜካፕ” ለቋል፤ ”ማስካቸው” ወልቋል። እና  ከአሁን በኃላ ታግለንና እያታግለን ህልውናችን ራሳችን ከማስከበር ውጭ በማን ልናሳብብና ምክንያት ልናደርግ እንችላለን? በእውነቱ ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ በአገራችን ያለቀው ህዝብ ብዛት፤ ተደራጅቶ ቢታገል እጀግ በጣም ባነሰ መስዋትነት ህልውናውን ባሰከበራና አገሩንም በታደገ ነበር።

እንግዲህ ምርጫው የኛ ነው፤  በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንገኝ ዜጎች ከመንደርተኝነት፣ ”ከፊስ ቡክ”’ትግልና ከመግለጫ ጋጋታ በመውጣት መሬት ላይ የወረደ አደረጃጀት በመመስረት ከታገልን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማንታደግበት ምንም ምክንያት የለም።  ለዚህም ነው  

”ጅብ ከሚበላህ በልተህው ተቀደስ።”  የሚባለው።  

አሁንም ማወቅ ያለብን ወያኔና ኦነጋዊ ብልጽግና ህዝብ አንቅሮ የተፋቸው በመሆናቸው፤ ከአሁን በኋላ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደማይታረቁ መታወቅ አለበት። ችግሩ ህዝብ የሚያደራጀውና የሚመራው ጽኑ ዓላማና መርህ ያለው ኃይል በማጣቱ ነው ለ”ቀን ጅቦች” የተጋለጠው።   በዚች ሰዓት እንኳን  ከሆዳቸው አልፈው የማያስቡት “ተቃዎሚ” ተብየዎች ህዝብን አደራጅቶ የአገርን ህልውና ከመታደግ ይልቅ “ሸንጎ” ውስጥ ተዘፍዝፈው አብረው እያቦኩ   እንደ ጲላጦስ “ከደሙ ንፁህ ነን” ለማለት ይከጅላሉ።

አሁንም ከታሪክ እንማር። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመታደግና ኢትዮጵያን  የሁላችን  ለመድረግ እንችላለን። ለዚህ ግን  ትግላችን የመኖርና ያለመኖር መሆኑንና ጎሰኞች  አገርንና ህዝብን ይዘው መጥፋት የመጨረሻ ዕጣቸው የምሆኑን ሃቅ  መቀበልና ፤ ጄን ቻርፕ ”ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ” በተሰኘው መጸሃፋ እንደሚመክረን፤  መራራ ቢሆንም አውነታውን መጋፈጥ  እንዳለብን እንገንዘብ። ይኽውም፤

1/ ጭቁን ህዝብ  ለትግል ያለውን  ቁርጠኝነት ፣ በራስ መተማመን፣ ሁኔታና ችግሮችን የመቋቋም ብቃቶችን ማጠናከር።

2/ ማህበራዊ ስብስቦችንና ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር።

3/ ጠንካራ የሆኑ የአገር ውስጥ የተቃውሞ ኃይሎችን መፍጠር፡

4/ ነጻ ለማውጣት የሚያስችል ስልት የተሞላበት መረሃ-ግብርና እቅድ መንደፍ፤ ይኽንም በዘዴ በተግባር መተርጎም።

ከዚህም በተጨማሪ  እንደ እኛ ላለ፤ ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ውጭ፡ በጎሳ ቡድኖች በየቀኑ  በማንነቱ እየተገደልና እየተፈናቀለ የህልውና ጥያቄ ተደቅኖበት ለሚገዛና ለመተጋለ ለቆረጠ ህዝብ ፤  የአይርላንዱ ተወላጁ ቻርልስ  ስትዋርት እንዲህ ይለናል፤

”መንግሥት  እንደሌለ ማመን የግድ ይላል። በራሳችሁ ውሳኔና ቆራጥነት ላይ ብቻ ነው መተማመን ያለባችሁ። በአንድነት በመቆም ራሳችሁን እርዱ፤ በመካከላችሁ ደካሞች ካሉ አበረታቷቸው። ራሳችሁን አስተባብሩ፤ ራሳችሁን አደራጁ፤ ታሸንፋላችሁም። ይህ እንዲሆን እስከአልተነሳችሁ ድራስ፣ እስከዚያች ግዜ ድራስ የነጻነት ጥያቄው አይመለስም፤ አይሳካም።—–”

ስለዚህም   በቆራጥነትና በራስ በመተማመን ተደራጅተን በመታገል፤ ራሳችንም  ሆነ  አገራችን  ከጎሰኞችና ከጸረ- ኢትዮጵያዊያን ነጻ እናውጣ። በምድራችን ላይ በልመና ወይም በገዥዎች ፈቃድ የተገኘ ነጻነትም ሆነ እንድነት የለምና። ለዚህም ነው “በነጻነት ተንገላቶ የኖረ ህይወቱ የጀግና ሞቱ የሰማእት ነው። በባርነት ደልቶት የኖረ ኑሮው የአሳማ ሞቱ የውሻ ነው::” የሚባለው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

ፊልጶስ

Email:Philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic