>

ካህናትን በጠራራ ፀሐይ ወግሮ መግደል የሃይማኖታዊ ጥቃቱ የቀጠለው ምዕራፍ ነው!

ካህናትን በጠራራ ፀሐይ ወግሮ መግደል የሃይማኖታዊ ጥቃቱ የቀጠለው ምዕራፍ ነው!

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን የሃይማኖት አባቶችን ይቅርና ታላቅን አለማክበር የሚያሳፍር ምናልባትም ከባሕላዊ እሴትነቱ ባለፈ ሃይማኖታዊ ይዘቱ የሚጎላ እሴታችን የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲሀ ግን የሃይማኖት አባቶችን ማዋረድ፣ ድብደባ መፈጸም አልፎም አስነዋሪ በሆነ ኹኔታ ወግሮና በአሰቃቂ ኹኔታ መግደል እየተለመደ መጥቷል። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በጸጥታ አካላት ጭምር ሲፈጸሙ የሚታዩ ሲሆን ድርጊቱ ትናንት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመው መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ብሎም ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ከፍ ወዳለ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያሳይ እና እውቅና ተሰጥቶት ወደለየለት ጭፍጨፋ አደገ ወይ? የሚያስብል ግፍ ሆኖ አግኝተነዋል።

መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፉሪ አካባቢ ቀሲስ ዓባይ መለሰ የተባሉ ካህን ቅዳሴ ጨርሰው ወደ ቤታቸው በመሄድ ላይ እያሉ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል። ይህንን አስነዋሪ ድርጊት ለማጋለጥ በሰዓቱ የነበረውን ኹኔታ በምስልና ቪዲዮ ለማስረጃ ለመያዝ የሞከሩ ሰዎች ቢኖሩም በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ሞባይል በመሰብሰብ የቀረጹትን ምስልና የቪዲዮ ማስረጃ እንዳጠፉባቸው ታማኝ ምንጮች ዘግበውታል። ጉዳዩ ቀደም ብሎ ከፍ ባለ ዛቻና ማስፈራሪያ የታጀበ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን በዚህ ኹኔታ ግን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ያደርጉታል የሚል እምነት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡ 

ፓርቲያችን ድርጊቱን የፈጸሙት አካላት ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ መረጃ እንዳይደርስ ያደረጉ አካላት እኩል የድርጊቱ አባሪና ተባባሪ በመሆናቸው ይዘገይ እንደሆነ እንጂ ከሕግ ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሥርዓት መር የሆነውና ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገው ጥቃትና ጭፍጨፋ በአስቸኳይ እንዲቆም ያገባኛል የሚል አካል ኹሉ እንዲረባረብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም ፓርቲያችን ድርጊቱን በጽኑ እያወገዘ በአሰቃቂ ኹኔታ ለተገደሉት አባት እርፍተ ነፍስን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ደግሞ መጽናናትን ይመኛል።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

እናት ፓርቲ

መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic